ፈልግ

የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ቀን ክብረ በዓል በኮንጎ ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ቀን ክብረ በዓል በኮንጎ ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “የምንኩስና ሕይወት በሰላም ፣ በደስታ እና በመግባባት የተሞላ ይሁን!”

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በላቲን አሜሪካዊቷ አገር ኮሎምቢያ ከነሐሴ 7–9/2013 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ የደቡብ አሜሪካ እና ካሬቢያን አገሮች ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት አንድነት ጉባኤ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከሚሰጡ ምስክርነቶች መካከል ከፍተኛ ደስታ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ በተግባር የማይገለጽ ከሆነ እና የአባላትን ቁጥር በማሳደግ ላይ ብቻ ያተኮሩ ከሆነ ፍርሃትን እና የብቸኝነት ስሜትን ሊያሳድግ ይችላል ብለዋል። በመሆኑም የምንኩስና ሕይወት በሰላም ፣ በደስታ እና በመግባባት የተቃኘ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሕብረት ማለት በሁሉም ረገድ አንድ ወጥ መሆን ማለት አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ “ሕብረት ማለት በአንድነት መካከል ያሉ ልዩነቶችን አቻችሎ ወደ ጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ማለት ነው” ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ልዩነቶችን ተገንዝቦ ዋጋን በመስጠት ወደ አንድ ወጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያግዝ መንፈስ ቅዱስ ነው” በማለት፣ ጉባኤያቸውን በአውታረ መረብ አማካይነት በላቲን አሜሪካ አገር ኮሎምቢያ ዓርብ ከነሐሴ 7 – 9/2013 ዓ. ም በማካሄድ ላይ ለሚገኙ የደቡብ አሜሪካ እና ካሬቢያን አገሮች ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት አንድነት ጉባኤ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት አስረድተዋል። “የአገሩን ባሕል ያልተገነዘበ እምነት ትክክለኛ አይደለም” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የምንኩስናን ሕይወት በደስታ ተቀብለው አሁን የሚገኙበትን ተጨባጭ እውነታን በመኖር ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ “ወደ ሰዎች ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ መግባት ማለት ለባሕሎቻቸውም ተገቢውን ክብር መስጠት ማለት ነው” ብለዋል።

ባሕል እና የክርስትና ሕይወት ጋር ማዛመድ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ መንፈስ ቅዱስ በሕዝቦች መካከል ለዘራው እውነት ዋጋን መስጠት እንዲቻል፣ እምነትን ከባሕል ጋር ማዛመድ ባሕልንም በቅዱስ ወንጌል እሴቶች ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። እምነትን ከባሕል ጋር ሳያዛምዱ የሚጓዙት የክርስትና ሕይወት ብሎም የምንኩስና ሕይወት ወደ ተሳሳተ መንገድ የሚመራ መሆኑን አስረድተው፣ ለዚህም ተጠቃሽ ምሳሌ የሚሆነው የአምልኮ ሥርዓቶችን በአግባቡ አለመጠቅም እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጎልቶ የሚታየው “የሰዎች ርዕዮተ ዓለም እንጂ የኑሮ እውነታዎች አለመሆኑን” አስረድተዋል።

የቁጥር መመዘኛነትን ማስቀረት ያስፈልጋል

የምንኩስና ሕይወት አንድነትን፣ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን በማሳደግ ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ በዘመናችን የሚታዩ የኑሮ ፈተናዎችን ለማሸነፍ የሚያግዝ መሆን አለበት ብለው፣ በልዩ ልዩ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ማኅበራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የማኅበራቸውን ደረጃ የሚያጤኑ እና በቁጥር እየቀነሱ መምጣታቸውን የሚያስተውሉ መሆኑን አስታውሰዋል። በብቸኝነት ሕይወት የሚመራ፣ በፍርሃት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ እና ወደ ዝግ ሕይወት የሚመራ የቁጥር እና የብዛት መመዘኛዎችን መተው እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። 

የሰላም ፣ የደስታ እና የተጫዋችነት ስሜት

በተስፋ በመሞላት ከእግዚአብሔር ጋር መጓዝ የሚሰጠውን መልካም ዕድል ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የምንኩስና ሕይወታቸውን የሚጓዙት በሙሉ፣ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ውስጥ ገብተው ቅዱስ ወንጌልን በመመስከር የሕይወት ምስክርነትን እየሰጡ ሌላውን ለመንፈስ ቅዱስ አደራ ሊሰጡ ይገባል ብለዋል። የምንኩስና ሕይወት ከሚገለጹባቸው ልዩ ባህሪያት መካከል የሰላም ፣ የደስታ እና የስምምነት ሕይወት የሚገኙባቸው መሆኑን ያመለከቱት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ የሕይወት ምልክቶች የማይታይባቸው ገዳማዊያን እና ገዳማዊያታ ሁሉን ነገር አክብደው ያዩታል ብለዋል። “ከኢየሱስ ጋር መሆን ደስተኛ መሆን ነው” ብለው፣ በደስታ መሞላት ወደ ቅድስና ሕይወት የማድረስ አቅም አለው” ብለዋል።

የገዳማዊያን እና ገዳናዊያት የጋራ ጉዞ

በደቡብ አሜሪካ እና ካሬቢያን አገሮች ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት አንድነት አስተባባሪነት በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጉባኤ በመካከላቸው ያለውን አንድነት በሚያጠናክሩ የመወያያ ርዕሦች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ታውቋል። አንድነቱም በምድራችን የሚገኙ ድሆች ጩሄት ለማድመጥ የተጠራች የቤተክርስቲያን አቋም የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ በመነኮሳቱ ድረገጽ ላይ የተገለጸው መልዕክት ያስረዳል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሚሰቃይ፣ የማኅበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን በሚታይበት በዛሬው ዓለም ውስጥ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እጅ ለእጅ ተያይዘው በኅብረት ጥሪን ማሳደግ እና ትንቢታዊ ተልዕኮአቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገልጿል።              

14 August 2021, 16:24