ፈልግ

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ ምዕዳን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ ምዕዳን 

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ ምዕዳን ዕጽዋዕትን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ሕይወትንም የሚመለከት መሆኑ ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የአርጄንቲና ዩኒቨርሲቲዎች አንድነት ከነሐሴ 26-29/2013 ዓ. ም. “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት በማድረግ ለሚያካሂዱት ጉባኤ መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው በላኩት መልዕክት፣ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ማኅበራዊ ግንዛቤ እንደሚኖረው እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችንም የሚደረግ እንክብካቤ እንደሚጨምር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ዓላማ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን በአረንጓዴ ተክል ማልማት ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች  መካከል ማኅበራዊ ግንዛቤ እንዲያድግ የሚያግዝ ማኅበራዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑን አስረድተው፣ የጉባኤው ተካፋዮች “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጥልቀት እና ስፋት በመገንዘብ ጠቃሚ ሃሳቦችን እንደሚያቀርቡ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። አክለውም ለጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከው፣ በጸሎታቸውም እንዲያታውሷቸው አደራ ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እ. አ. አ 2015 ዓ. ም በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት ባሰተላለፉት መልዕክት፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ቃለ ምዕዳናቸው በርካታ ማኅበራዊ ርዕሠ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። በዚህ ቃለ ምዕዳን ውስጥ ከቁ. 15 ጀምሮ የተቀመጠው መልዕክት “የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ” የታከለበት መሆኑን ይገልጻል። ቀጥሎም በቁ. 19 ላይ የተቀመጠው መልዕክትም “እውነተኛ ሥነ ምህዳራዊ አካሄድ ሁል ጊዜ ማኅበራዊ አቀራረብ ያለው ካልሆነ የጋራ መኖሪያ ምድራችን ስቃይ እና የድሆችን ጩኸት መስማት አንችልም” በማለት ይገልጻል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ሐምሌ 21/2021 ዓ. ም የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ አካዳሚ “በዘመናዊ ባርነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የከተሞች ቁርጠኝነት” በሚል ርዕሥ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረግ እንክብካቤን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። ሰብዓዊ ፍጥረትን ከመኖሪያ አካባቢያችን ነጥሎ መመልከት የማይቻል መሆኑን የተመለከተው ጳጳሳዊ አካዳሚው፣ ሥነ-ምህዳር ሰብዓዊ ፍጠረትንም የሚያካትት መሆኑ አመልክቷል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ የሰውን ልጅ ከሚኖርበት አካባቢ ነጥሎ መመልከት የማይቻል መሆኑን ገልጸው፣ ሁለቱ እርስ በእርስ የሚተጋገዙ መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለውም የሰው ልጅ በሚኖርበት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ለመኖሪያ አካባቢ የሚደረገውን ጥበቃ እና እንክብካቤ መርሳት እንደማይቻል አስረድተው፣ ለመኖሪያ አካባቢ የሚደረግ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሕዝቦችን የሚያስተባብር የጋራ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ 2016 ዓ. ም ለኢየሱሳዊያን ማኅበር አባላት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ስለ ምድራችን ዕጽዋዕት ብቻ የሚናገር ሳይሆን የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወትንም የሚመለከት፣ ማኅበራዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። ለተፈጥሮ የሚደረግ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሲጎድል የቅድሚያ ተጠቂዎች በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ እና ከማኅበራዊ ሕይወት የተገለሉ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በማኅበረሰብ መካከል ያለውንም የኑሮ አለመመጣጠን እና መገለልን የሚመለከት መሆኑን አስታውሰው፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማኅበራዊ ሕይወት ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።    

በሰው ልጅ ሕይወት እና በጋራ መኖሪያ ምድራች ላይ የመጣውን ፈተና ለመቋቋም እና ሥነ-ምህዳራዊ ግንዛቤን ለማግኘት የሚያግዝ ዓለም አቀፍ ውይይት በአርጄንቲና ዩኒቨርሲቲዎች አንድነት፣ በአርጄንቲና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ምክር ቤት እና በአርጄንቲና ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መካከል በመጭው መስከረም ወር የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

የአርጄንቲና ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ እና የሳይንስ ጥናት ማዕከል በጋራ ያዘጋጁት ጉባኤ ዘላቂነት ያለውን ሁለ ገብ ዕድገት ለማምጣት የሚያግዝ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችን የወደ ፊት ዕድል ለመወሰን የሚያግዙ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህን ዓላማ መሠረት በማድረግ የሚወያየው የዩኒቨርሲቲዎች አንድነት ጉባኤ፣ በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ ሰፋ ያለ የውይይት መድረክን በማመቻቸት በአህጉሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን በበላይነት በማሳተፍ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ ለሚታዩ ለውጦች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ያቀደ መሆኑ ታውቋል። ይህን ዓላማ ለማሳካት 40 የሚያህሉ ዩኒቨርሲቲዎች እና ውስብስብነት ያለባችውን ሥነ-ምሕዳራዊ ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችሉ አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያካፍሉ ከ 130 የሚበልጡ ባለሙያዎች የሚሰበሰቡ መሆኑ ታውቋል። ባለሙያዎቹ እርስ በእርስ በመተባበር የሥነ-ምሕዳር ችግሮችን ለይተው ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን በማቅረብ ተግባራዊ የሚሆኑ እርምጃዎችን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ተነሳሽነቱ በመንግሥት፣ በግል ዘርፍ፣ በሕዝባዊ ተቋማት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በሕግ ዘርፍ፣ በትምህርት እና ባሕል ማዕከላት፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እና በሕዝባዊ ማኅበራት ውስጥ የተሰማሩ ባለሥልጣት ውሳኔ ሰጪ አካላትን የሚመለከት መሆኑ ታውቋል። የጉባኤው ውይይት አራት ጭብጦችን ያካተተ ሲሆን እነርሱም የግል ሰብዓዊ ክብርን፣ ወንድማማችነትን እና ባህል፣ የአካባቢ ጥበቃን እና የሰው ልጅ ማኅበራዊ ልማት የሚሉ ሲሆን እያንዳንዱ የጉባኤው እንቅስቃሴ በበይነ መረብ አማካይነት ለሌችም ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል።

25 August 2021, 16:39