ፈልግ

በፈረንሳይ አገር የሚገኘው ሞንፎርታኒ በመባል የሚታወቀው ሚስዮናዊ ማሕበር አለቃ የነበሩት አባ ኦሊቪየር እኝህ ነበሩ! በፈረንሳይ አገር የሚገኘው ሞንፎርታኒ በመባል የሚታወቀው ሚስዮናዊ ማሕበር አለቃ የነበሩት አባ ኦሊቪየር እኝህ ነበሩ! 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በአባ ኦሊቪየር ግድያ እጅግ ማዘናቸውን ገለጹ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 05/2013 ዓ.ም ረብዕ እለት ከቫቲካን ሆነው የሚያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካጠቃለሉ በኋላ በቅርቡ በነሐሴ 03/2013 ዓ.ም የ60 አመት እድሜ ያላቸው እና በፈረንሳይ አገር የሚገኘው ሞንፎርታኒ በመባል የሚታወቀው ሚስዮናዊ ማሕበር አለቃ የነበሩት አባ ኦሊቪየር በፈረንሣይ በቬንዲ ክልል ውስጥ አንድ የአእምሮ በሽተኛ እርሳቸው ባላሰቡት ሰዓት ጥቃት ፈጽሞ ስለገደላቸው በሁኔታው እጅግ ማዘናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመልእክታቸው የሚከተለውን ብለዋል “የአባ ኦሊቪየር ማየርን ግድያ ስሰማ እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት። በቬንቴኔ በቅዱስ ላውረንት-ሱር ሴቭሬ ለሚገኘው የሞንፎርቲኒ ሚሲዮናዊ ማህበረሰብ አባላት፣ ለቤተሰቦቻቸው እና በፈረንሣይ አገር ለሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በሙሉ ሐዘኔን እገልጻለሁ፣ በዚህ የሐዘን ወቅት ለእናንተ ያለኝን ቅርበት ለመግለጽ እወዳሉ፣ በጸሎት ከእናንተ ጋር ነኝ፣ ሐዋርያዊ ቡራኬዬ ይድረሳችሁ” ማለታቸው ተገልጿል።

እነዚህ ቀደም ሲል የገለጽናቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሕሮ ካገባደዱ በኋላ በአባ ኦሊቪየር ግድያ የተነሳ ሐዘናቸውን የገለጹበት ቃላት ሲሆኑ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 03/2013 ላይ ነበር በአእምሮ ሕመም ሲሰቃይ የነበረው የሩዋንዳ ተወላጅ አማኑኤል አባይሰንጋ በድንገት ግድያውን የፈጸመው፣ ይህ ሰው ከአንድ ዓመት በፊት በፈረንሳይ አገር የሚገኘውን የናንትስ ካቴድራል ላይ እሳት ለመለኮስ ሙከራ አድርጎ የነበረ ሲሆን በዚህ ተግባሩ የተነሳ በፖሊስ ክትትል ሲደረግበት የቆየ ሰው ነበር፣ ይህ ሰው ነው እንግዲህ አባት ኦሊቪየር ማየርን የገደለው።

ይህ ተግባር ከማንኛውም ዓይነት የአሸባሪዎች ዓላማ ጋር የተገናኘ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማጣራት አሁንም ቢሆን ምርመራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፣ እናም የነፍሰ ገዳዩን የስነ -አዕምሮ ሁኔታ እና የሐይማኖት ሰው የነበሩት አባ ኦሊቪየር ሞት ጋር የሚገናኝ ነገር ካለ በመጣራት ላይ ነው፣ ይህ ድንገተኛ እውነታ የመላውን የሟች ሚሲዮናዊ ማሕበር አባላትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናንን ጭምር ታላቅ ሀዘን የፈጠረ አጋጣሚ ነው።

የፈረንሳይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባሄ ፕሬዝዳንት ሞንሰንጎር ደ ሞልንስ -ቢውፎርት ስለሁኔታው እና ሰለ አባ ኦሊቪየር አሟሟት በተናገሩበት ወቅት “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰዎችን በሙሉ ተቀብለው በማገልገላቸው የተነሳ እስከመጨረሻው የክርስቶስ አገልጋይ ነበሩ” በማለት ስለሟች ካህኑ አባ ኦሊቪየር ተናግረዋል። አክለውም  ፈረንሳውያን ጳጳሳት ጸሎታቸውን ለሟችን ቤተሰቦች፣ ለሞንፎርታኒ ሚስዮናዊ ማሕበር አባላት እንደ ሚያቀርቡ ያረጋገጡ ሲሆን የሮኤን ጳጳስ ዶሚኒክ ሌብሩን በበኩላቸው ሁኔታውን በተመለከተ እንደተናገሩት ሁኔታው ኢየሱስ ያስተማረን ጸሎት ውስጥ “አባታችን” እና “ከክፉ አድነን” የሚሉትን የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ቃላትን ያስታውሳል፣ በየቀኑ ሟቹ ካህን አጽንዖት የሰጡበት ቃል ነው፣ ክርስቲያኑ ይህንን ጸሎት በእየለቱ ይደግማል፣ ከዚያም እግዚአብሔር ለሁሉም ሰዎች በሚፈልገው በወንድማማችነት ውስጥ ተስፋን ያገኛል። በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ሁሉ “በዙሪያው እና በእሱ ውስጥ ያለውን ሁከት ሁሉ ለመዋጋት ይፈልጋል” በማለት ስለአባ ኦሊቪየር መናገራቸው ተገልጿል። አክለውም የአባ ኦሊቪየር የጦር መሣሪያዎች የነበሩት “ፍትህ ፣ ሰላም እና ይቅርታ” እንደ ነበሩ ያስታወሱት የሉዚዮን ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሞንዚነር ፍራንሷ ጃኮሊን አባ ኦሊቪየር በሕይወት እያሉ በእምነት ብቻ ትርጉም ስላለው አሳዛኝ ሁኔታ ሲናገሩ “ዘሩ ካልሞተ በስተቀር ብቻውን ይቀራል፣ ከሞተ ግን ብዙ ፍሬ ያፈራል” በማለት አብዝተው ይናገሩ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ግድያውን የተመለከተ ዜና በመላው ፈረንሳይ ከተሰማ በኋላ የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዣን ካክስቴክስ የተሰማቸውን ሐዘን እና ብስጭት ለመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መግለጻቸው ይታወሳል።

11 August 2021, 11:05