ፈልግ

እ. አ. አ 2119 በሜጁጎሪ ከተማ የተካሄደ የውጣቶች ፌስቲቫል እ. አ. አ 2119 በሜጁጎሪ ከተማ የተካሄደ የውጣቶች ፌስቲቫል 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ወጣቶች ኢየሱስን ለመከተል ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል አሉ

በቦስኒያ ሄርዞጎቪና ውስጥ በምትገኝ ሜጁጎሪ ከተማ ከእሑድ ሐምሌ 25 - 30/2013 ዓ. ም ድረስ በዓመታዊ የጸሎት ጉባኤ ላይ ለሚገኙት ወጣቶች ቅዱስነታቸው በላኩት መልዕክት፣ የእመቤታችንን ምሳሌ በመከተል፣ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፈቃድ በማስገዛት፣ በሙሉ እምነት ከእግዚአብሔር በሚሰጥ እውነተኛ የደስታ ስጦታ በመታገዝ፣ ከክፉ ልማዶች ሁሉ ነጻ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማቴ. 19፡16-22 ፣ በማር. 10፡17-22 እና በሉቃ. 18፡18-23 አንድ ወጣት ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ያቀረበው ጥያቄ ዘንድሮ በሜጁጎሪ ከተማ ከሐምሌ 25-30/2013 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ላለው ዓመታዊ የጸሎት ጉባኤ መሪ ቃል ሆኖ መመረጡ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ይህን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ መሠረት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በማቴ. 19፡21 ላይ ኢየሱስም “መጥተህ ተከተለኝ” ያለውን በማስታወስ፣ ኢየሱስ ዘወትር እንደሚወደን እና ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚጋብዘን መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ መልዕክታቸው ጋር በዓመታዊው የጸሎት ጉባኤ ላይ ለተገኙት ወጣቶች በሙሉ ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል።

ከኢየሱስ ጋር ለመገናኘት ዕድልን የሚያገኙበት

ለአንድ ሳምንት በሚቆይ የጸሎት ጉባኤ ወጣቶቹ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገናኙበትን ዕድል ማግኘታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ከሁሉም በላይ ሕያው ቃሉን የሚሰሙበት፣ ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት፣ የምስጋና እና የውዳሴ ጸሎትን የሚያቀርቡበት እና የምሕረት ጸጋን የሚቀበሉበት መልካም አጋጣሚ ነው ብለው፣ ይህም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለሚያደርጉት ጉዞ ኃይል እና ብርታት የሚሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ይህ ወጣት ማን መሆኑን በስም ባናውቅም ከእግዚአብሔር ነፍሳት መካከል አንዱ እና በጸሎት ጉባኤ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሚሳተፉ ወጣቶች በሙሉ አርማቸው ይሆናል ብለዋል።  

ወጣቱ እውነተኛ ደስታን እንዲፈልግ በሚገፋፋ እና ዕረፍትን በሚነሳ ስሜት መቀስቀሱን ቅዱስነታቸው አስታውሰው በዚህ ስሜት በመነሳሳት፣ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ሊያቀርበው ሥልጣን ወዳለው፣ ተዓማኒ እና አስተማማኝ ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ መምጣቱን አስታውሰዋል። የዘላለም ሕይወት፣ መልካም የሆነው ሁሉ በራስ ጥንካሬ ብቻ የሚገኝ ቋሳዊ ድል አለመሆኑን፣ ነገር ግን ወጣቶች በሕይታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳዩት መንፈሳዊ የዕድገት ደረጃዎች የሚያገኙት ጸጋ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለወጣቶቹ በላኩት መልዕክታቸው አስረድተዋል።

ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚወስዱ እርምጃዎች - ባልንጀራን መውደድ

ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ከሚወስዱ እርምጃዎች መካከል የመጀመሪያው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፣ ባልንጀራን በተጨባጭ መውደድ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ደግሞ ትእዛዛቱን ለማክበር ያህል  ብቻ የሚደረግ ሳይሆን፣ በነጻ የሚሰጥ ሙሉ ፍቅር መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣቱ በልቡ ሙሉ ፍላጎት እንዳለው ቢገነዘብም፣ በሌላ ወገን በደካማ ጎኑ፣ ከብዙ ቁሳዊ ሃብቶች ጋር የተቆራኘ መሆኑን መገንዘቡን አስረድተዋል። ስለዚህ እንደ ሁለተኛ እርምጃ፣ ለባልንጀራ የሚሰጥ ፍቅር ስለሚገባው ሳይሆን በነጻ ፍላጎት በስጦታ የሚሰጥ መሆን አለበት ብለዋል።   

በማቴ. 19፡21 ላይ “ፍጹም መሆን ብትፈልግ ያለህን ሽጠህ ገንዘቡን ለድሃ ስጥ፤ በሰማይ ሃብት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተልኝ” ማለቱን እና ራሱ እንዳደረገው ሁሉ፣ ወጣቱም ስለ ወደ ፊት ሕይወቱ ሳይጨነቅ፣ ምድራዊ ሃብቱን ሁሉ አሳልፎ እንዲሰጥ መጠየቁን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ይህን በማድረግ ከሰዎች ዘንድ ክብርን ከመጠበቅ ይልቅ በጥሪ ላይ ተጨማሪ ብስለትን በማሳየት ለባልንጀራ ሙሉ ፍቅርን በነጻ መስጠት እንደሚያስፈልግ ኢየሱስ መናገሩን ገልጸው፣ ወጣቱ ልብን ከሚከብድ እና ፍቅርን ከሚያደናቅፍ ነገር እንዲላቀቅ ኢየሱስ መጠየቁንም አስታውሰዋል።

የክፉ ነገር ተገዥዎች አንሁን

ልብ በምድራዊ ሃብት የተጨናነቀ ከሆነ ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀራ የምንሰጠው ትርጉም አይኖረንም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ከመጠን ያለፈ ሃብት እና ምኞት ደስታን በማሳጣት ፍቅር ይቀንሳል ብለው፣ “መጥተህም ተከተልኝ” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ለወጣቱ ያቀረበው ጥሪ እና የእርሱ ደቀ መዝሙርነት በውጫዊ ገጽታ እርሱን መምሰል ሳይሆን፣ ለጥሪው በምንሰጠው ምላሽ፣ በቅዱስ ወንጌል ላይ እንደተገለጸው፣ ሙሉ ሕይወትን እና ደስታን የምናገኝበት፣ ከብዙ ወንድሞች፣ እህቶች፣ እናቶች፣ አባቶች እና ልጆች ጋር የምንገናኝበት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።     

ደስተኛ ለመሆን እራስን ለክርስቶስ መስጠት

ወጣቱ ራሱን ከዓለማዊ ሃብት በማላቀቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመተባበር፣ ከእርሱ ጋር በመጓዝ እውነተኛ ደስታን ለማገኘት አለመድፈሩ የሚያሳዝን መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በሜጂጎሪ በጸሎት ጉባኤ ላይ የሚገኙት ወጣቶች ከኢየሱስ ጋር በመጓዝ ቃሉን በማድመጥ ራሳቸውን በእምነት ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ፣ በአጓጊ እና ሃሰተኛ ዓለማዊ ሃብት ከመሳብ ይልቅ ነጻ በሚያደርግ እውነተኛ ፍቅር በመሸነፍ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ተቀብለው ለጥሪው መልስ እንዲሰጡ አደራ ብለዋል።     

ማርያምን የሕይወታችን ምሳሌ እናድርጋት

በሜጂጎር በሚካሄድ ላይ ባለው የጸሎት ጉባኤ ላይ የተገኙትን ወጣቶችን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ የሰጡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ከእርሷ ዘንድ ኃይልን በማግኘት፣ ራሷን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አሳልፋ በመስጠት ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም እንዳመጣች ሁሉ፣ በሕይወታችን ስር ነቀል ለውጥን በማምጣት ሌሎችን ለማገልገል የሚያስችለንን ኃይል እንድታማልድልን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። እንደ ማርያም ለሌሎች ትኩረትን እንድንሰጥ አሳስበው፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በመመራት ይህን በእምነት የምንፈጽም ከሆነ በምናገኘው ደስታ እርግጠኞች መሆን እንችላለን ብለዋል።   

03 August 2021, 16:24