ፈልግ

የእንግሊዝ ከተማ በሆነችው ፕሊማውዝ ውስጥ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት የእንግሊዝ ከተማ በሆነችው ፕሊማውዝ ውስጥ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ክፉን ነገር በመልካም ማሸነፍ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ምዕራብ የእንግሊዝ ከተማ በሆነችው ፕሊማውዝ ውስጥ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡትን በማስታወስ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው አደጋው የደረሰባቸውን በሙሉ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። በአደጋው የሞቱትን በጸሎት ለማስታወስ በፕሊማውዝ ከተማ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ቦኒፈስ ካቴድራል ትናንት ነሐሴ 12/2013 ዓ. ም የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለከተማው ጳጳስ ለብጹዕ አቡነ ማርክ ኦ ቱል በላኩት መልዕክት በጸሎት የሚተባበሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለሞቱት ሰዎች ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ፍቅራዊ ምሕረቱን፣ ጉዳት ለደረሰባቸውም መለኮታዊ ፈውስን፣ በሐዘን ላይ ለሚገኙት ቤተሰቦች ሁሉ መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።

በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ በብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በኩል በተላከው የቴሌግራም መልዕክታቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ሁከትን አስወግደን፣ ክፉን ነገር በመልካም ለማሸነፍ እግዚአብሔር ኃይልን እና ብርታትን” ይስጠን ብለዋል።   

በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ፣ በፕሊማውዝ ከተማ ያለፈው ዓርብ ነሐሴ 7/2013 ዓ. ም. አንድ መሣሪያ ታጣቂ ግለሰብ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ፣ ቀጥሎም ሕዝብ በሚበዛበት አካባቢ በከፈተው ጥቃት አምስት ሰዎችን ገድሎ ነፍሱንም ማጥፋቱ ታውቋል። ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ በከተማው “ኢንሰል” ተብሎ የሚታወቅ በማኅበረሰብ መካከል ጥላቻን የሚያስፋፋ አሸባሪ ቡድን አባል መሆኑ ታውቋል። 

19 August 2021, 16:27