ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሄይቲን በጸሎታቸው አስታውሰው ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደረግላት አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበዋል። በሄይቲ በተከሰተው የምድር መንቀጥቀጥ በበርካታ የሰው ሕይወት ላይ የሞት አደጋ መድረሱን እና በንብረት ላይም ከፍተኛ ጥፋት መድረሱን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ የአደጋው ሰለባ የሆኑትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። አክለውም ከአደጋው ለተረፉት በሙሉ ብርታትን ተመኝተው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአደጋው ለተጠቃች ሄይቲ የዕርዳታ እጁን እንደሚዘረጋ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በሄይቲ ሕዝብ ላይ የደረሰው መከራ እና ስቃይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትብብር እንደሚቃለል ገልጸው፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጠል፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ውጊያ ያሳሰባቸው መሆኑን በመግለጽ በችግር ውስጥ ከሚገኝ የአፍጋኒስታን ሕዝብ ጎን በመሆን በጸሎት የሚደግፉት መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በአፍጋኒስታን ውስጥ እግዚአብሔር ሰላሙን እንዲያወርድ፣ የተለያዩ ወገኖች በጋራ በሚያደርጉት ውይይት በኩል ሰላም እንዲገኝ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። አክለውም በጦርነቱ መክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ሴቶች እና ወንዶች፣ ሕጻናት እና አዛውንት ሰላምን አግኝቶ ወደ መኖሪያው መመለስ የሚችለው በጋራ ውይይት በሚያመጡት ስምምነት መሆኑን አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በአደባባዩ ላይ ለተገኙት የሮም እና አካባቢው ምዕመናን፣ ከተለያዩ አካባቢዎች እና አገሮች ለመጡት ነጋዲያን በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በተለይም ከተለያዩ የጣሊያን ከተሞች ለመጡት ወጣቶች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በመላው ጣሊያን ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም የሚከበረውን ዓመታዊ በዓልን በባሕር ዳርቻዎች በማክበር ላይ ለሚገኙት በሙሉ ሰላምን ተመኝተውላቸዋል። በሥራ ገበታ የሚገኙትን፣ በሕመም ላይ ያሉትን፣ አቅመ ደካማ አረጋዊያንን፣ ስደተኞችን እና በብቸኝነት ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙትን አስታውሰው፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግልማርያም እናታዊ ጥበቃን እና ከለላን በጸሎት ጠይቀዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኙት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን እንዲሁም ምዕመናን በሙሉ፣ በሮም ከተማ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ በመሄድ፣ የሮም ከተማ ሕዝብ የመዳን ተስፋ ወደ ሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል።

በአደባባዩ ለተገኙት ምዕመናን በሙሉ መልካም ዕለተ ሰንበትን ተመኝተው፣ በላቲን የአምልኮ ሥርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ በዓልን ለሚያከብሩት በሙሉ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው ተመኝተውላቸዋል። በመጨረሻም ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ጠይቀው ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን በማስተላለፍ ንግግራቸውን ደምድመዋል።  

16 August 2021, 17:22