ፈልግ

በላይቤሪያ የኢቮላ ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ወቅት በላይቤሪያ የኢቮላ ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ወቅት 

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተላከ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎች ዕርዳታ ወደ ላይቤሪያ መድረሱ ተነገረ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተጠቁ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ለሆነች ላይቤሪያ ያደረጉት የተለያዩ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ዕርዳታ መድረሱን የላቤሪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አባ ዴኒስ ኒመነ ገልጸው፣ “የቅዱስነታቸው ዕርዳታ ለላይቤሪያ ሕዝብ ያላቸውን ወዳጅነት የሚገልጽ በመሆኑ፣ ለተደረገልን የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ምስጋናችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ እና በቂ የሕክምና መስጫ መሣሪያ ለሚያንሳቸው በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ዕርዳታን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። በአፍሪካ ውስጥ በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን በላይ መድረሱ ሲነገር፣ በዓለማችን ውስጥ በወረርሽኙ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአራት ሚሊዮን በላይ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ 34,000 ለተያዙባት እና 900 ሰዎች ለሞቱባት ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ኤስዋቲኒ፣ ነሐሴ 5/2013 ዓ. ም በርካታ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎችን እና የወረርሽኙ መከላከያ ቁሳቁሶችን መላካቸው ይታወሳል። ዕርዳታውን የተቀበሉት የማንዚኒ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሉዊስ ደ ሌዎን፣ “አገራችን በከፍተኛ ችግር ውስጥ በምትገኝበት ወቅት የተላከ ዕርዳታ ነው” በማለት ቅዱስነታቸውን ማመስገናቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለደቡብ አፍሪካ አገር ኤስዋቲኒ ከላኩት ዕርዳታ ቀጥለው፣ 5. 500 የቫይሬሱ ተጠቂዎች ለሚገኙባት እና 245 ሰዎች ለሞቱባት የምዕራብ አፍሪካ አገር ላይቤሪያ፣ ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በዋና ከተማዋ ሞኖሮቪያ ለሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሆስፒታል መላካቸው ታውቋል። ከቅዱስነታቸው የተላኩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ነሐሴ 19/2013 ዓ. ም የተቀበሉት በላይቤሪያ የቅድስት መንበር እንደራሴ እና ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዳጎቤርቶ ካምፖስ ሳላስ እና የላይቤሪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ ዴኒስ ኒማነ መሆናቸው ታውቋል።

የማያቋርጥ ኅብረት

ክቡር አባ ዴኒስ ኒማነ ለቅዱስነታቸው በላኩት የምስጋና መልዕክት፣ ወረርሽኙ ወደ ላይቤሪያ በገባበት በ2011 ዓ. ም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላይቤሪያን ለማገዝ የ40 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸዋን አስታውሰዋል። የአሁኑ ዕርዳታቸውም ቅዱስነታቸው ከላይቤሪያ ሕዝብ ጋር የማያቋርጥ ኅብረት እንዳላቸው የሚገልጽ ነው ብለዋል። በሌላ ወገን በላይቤሪያ ውስጥ ሁለተኛውን ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ያገኙት ሰዎች ቁጥር፣ ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ መካከል 0.6ብ በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል።

በላይቤሪያ ውስጥ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሚተዳደሩ የጤና ተቋማት ቁጥር 22 መሆናቸው ሲታወቅ፣ በአገሪቱ በአገልግሎቱ የሚታወቅ እና በቅዱስ ዮሐንስ እግዝዕነ ማኅበር አባላት የሚመራ የቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል መሆኑ ታውቋል። እ. አ. አ በ2014 ዓ. ም. በአገሪቱ የተከሰተውን የኢቮላ ወረርሽኝን በቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል ውስጥ የሕክምና አገልግሎታቸውን ሲሰጡ የነበሩ ገዳማውያን እና ዓለማዊያን ባለሞያዎች መሆናቸውን፣ ክቡር አባ ዴኒስ ኒማነ አስታውሰዋል። ሆስፒታሉ ከዚያን ጊዜ አንስቶ አገልግሎቱን እና የሰው ኃይልን ለማሳደግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የጤና ባለሞያዎችን ለማዘጋጀት እና በሰዎች ጤና ላይ የሚደርሱ ድንገተኛ ችግሮችን ለማሸነፍ እና ተቋሙን በበቂ ሁኔታ ለማደራጀት ብዙ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ክቡር አባ ዴኒስ አስረድተዋል። በላይቤሪያ የምትገኝ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን በአገሪቱ የሚካሄደውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት መርሃ ግብርን በመደገፍ፣ ምዕመናን የታዘዙትን የክትባት መጠን እንዲወስዱ በማበረታታት ላይ መሆኗን፣ የላይቤሪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ ዴኒስ ኒማነ አስታውቀዋል።

31 August 2021, 16:31