ፈልግ

የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋዊያን ቀን በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋዊያን ቀን በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ወጣቶች ከአዛውንት እና ከቤተክርስቲያን ጋር አዲስ ጥምረት እንዲፈጥሩ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋዊያን ቀን እንዲከበር በወሰኑት መሠረት ሰኞ ሐምሌ 18/2013 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተከናወነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት የመሩት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ ባቀረቡት ስብከት፣ አያቶች እና አረጋዊያን የማኅበረሰብ ውድ ሃብት በመሆናቸው ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ እና ከአዲሱ ትውልድ ጋር ያላቸው ግንኙነትም ዘወትር ማደግ እና መለምለም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ለተገኙት አረጋዊያን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ እኩለ ቀን ላይ ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት ለአረጋዊያን እና አያቶች ሰላምታ ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ በቅርቡ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ መደበኛውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት ዕረፍት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመጀመሪያ በሆነው ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን እና አያቶች ቀን ባቀረቡት ስብከት በትውልዶች መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት ሦስት ሃሳቦችን የገለጹ ሲሆን እነርሱም ማየት፣ መጋራት እና በክብር ጠብቆ ማቆየት የሚሉ መሆናቸው ታውቋል። በትውልዶች መካከል ወደፊት ሊኖር የሚገባ አዲስ ግንኙነት መኖሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ውድ የሆኑ የሕይወት ሃብቶችን በጋራ መካፈል እንደሚያስፈልግ፣ በጋራ ማለም እና ራስ ወዳድነት እና ብቸኝነትን በመከላከል ለመጭው ትውልድ የሚበጅ መልካም ጊዜን በጋራ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዮሐ. 6:5 ላይ እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውን ተዓምር መሠረት በማድረግ ያቀረቡትን ስብከት ያስታወሱት ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ፣ ኢየሱስ ፊሊጶስን “ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ ከየት መግዛት እንችላለን” ብሎ መጠየቁን አስታው፣ በረሃብ ይሰቃይ የነበረ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጋ ሰው በማየት አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ በማካፈል ከመገበ በኋላ ትርፍራፊው እንዳይባክን ደቀ መዛሙርቱ ሰብስበው በአንድ ሥፍራ በክብር ማስቀመጣቸውን አስታውሰዋል።

ጥንቃቄ የተሞላበት እይታ እንዲኖር ያስፈልጋል

ኢየሱስ እርሱን ሊያገኙት ረጅም መንገድ በመጓዝ ድካም እና ረሃብ የያዘውን ሕዝብ በዓይኑ እንደተመለከተ ወንጌላዊው ዮሐንስ የጻፈውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ለእኛ በመጨነቅ ሕይወትን፣ ፍቅርን እና ደስታን የተራበ ሰውነታችንን በመልካም ነገር እንደሚያጠግብ፣ በዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ምን ያህል እንደሚጨነቅ፣ ድካማችንን እና ወደ ፊት ለመጓዝ ያለን ተስፋ ከፍተኛ መሆኑን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል። አያቶቻችንም በሕጻንነታችን ጊዜ ብዙ በመጨነቅ በጥንቃቄ ይመለከቱን እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ አያቶቻችን በእድገታችን ወቅት ምን እንደሚያጋጥመን፣ ምን እንደሚያሳዝነን እና ምን እንደምንመኝ በማወቅ ለእኛ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ስለገለጹልን አመስግነዋቸዋል።

ችኩል ማህበረሰብ ግድየለሽ ነው

“ከአያቶቻችን እና ከአረጋዊያን ጋር ያለን ግንኙነት ምን እንደሚመስል ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ብዙ ከመቸኮል የተነሳ ለአረጋዊያን እና ለአያቶች ግድ የማይል ማህበረሰብን መመልከት የሚያሳዝናቸው መሆኑን ገልጸው፣ ዛሬ እርስ በእርስ የማይተዋወቅ ማኅበረሰብ፣ ቆም ብሎ አንዱ ሌላውን መመልከት የማይችል ማኅበረሰብ የሚያሳስባቸው መሆኑን አስረድተዋል። አያቶች የእኛ እንክብካቤ እና አለኝታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።              

ያለንን እና ማንነታችንን ማካፈል ያስፈልጋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስብከታቸው ኢየሱስ በአምስት ዳቦ እና በሁለት ዓሣ በቁጥር በርካታ ሕዝብን መመገብ መቻሉን አስታውሰው፣ በአገልግሉ የያዛቸውን አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣዎችን በስጦታ በማቅረብ ከሌሎች ጋር ለመጋራት ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘውን ልጅ አመስግነው፣ ዛሬ በወጣቱ ትውልድ እና በአረጋዊያን መካከል የጋራ ሕይወትን መጋራት እንደሚያስፈልግ አሳስበው በትውልዶች መካከል ያለውን ቅራኔ በማስወገድ መልካም የወደ ፊት ሕይወትን በጋራ ማገንባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ለራስ ብቻ፣ ለግል ጥቅም ብቻ የሚያስብ ማኅበረሰብ መፈጠሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ለጋራ ሕይወት ጥረት የማይደረግ ከሆነ እና ለግል ሕይወት ብቻ የሚጨነቁ ከሆነ በረሃብ የመሞት ዕድል እንደሚያጋጥም አስረድተው፣ ያለንን እና ማንነታችንን ጭምር ለሌሎች ማካፈል ያስፈልጋል እንደሚያሳስብ አሳስበዋል።

ምንም እና ማንም ወደ ውጭ መጣል የለበትም

ከእግዚአብሔር እይታ የሚሰወር ምንም ነገር እንደሌለ የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ከአምስት ሺህ ሰዎች የተረፈው ትርፍራፊ ተሰብስቦ በጥሩ ቦታ እንዲቀመጥ ማድረጉን አስታውሰው፣ ለምግብ ይህን ያህል  ክብር የሚሰጥ ከሆነ ይበልጥ ደግሞ ለሰዎች ክብር እና እንክብካቤ ሊሰጣቸው እንድሚገባ ተናግረው፣ ምንም እና ማንም ከማኅበረሰብ ተለይቶ ወደ ውጭ መጣል እንደሌለበት አሳስበዋል። አያቶች እና አረጋዊያን ከኅብረተሰቡ መካከል መገለል እንደሌለባቸው አሳስበው፣ ማኅበረሰቡን በሃሳብ እና በጥበብ በዘላቂነት ማገዝ የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። አረጋዊያን ያወረሱንን ታሪክ በከንቱ ማጣት እንደማያስፈልግ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው አረጋዊያን ተንከባክበውን እንዳሳደጉን ሁሉ እኛም ውለታቸውን መክፈል፣ ፍላጎታቸውን ማሟላት፣ በዕለታዊ ሕይወት ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ከጎናቸው መኖር ይጠበቅብናል ብለዋል።    

ከአረጋዊያን ጋር የአንድነት ቃል ኪዳን መግባት ያስፈልጋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን እና የአያቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ በመካከላችን ከምናገኛቸውን አያቶች እና አረጋዊያን ጋር ያለንን ግንኙነት በማደስ፣ ብቸኝነት እንዳይሰማቸው በፍቅር በመቅረብ፣ ጊዜያችንን በጋራ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ከእነርሱ የተቀበልናቸውን በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችንም ማስታወስ እንደሚገባ አደራ ብለዋል። 

26 July 2021, 19:04