ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ በዓለም አቀፉ የቤተሰብ ፌስቲቫል ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ሊካሄድ የታቀደውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል በማስመልከት ዓርብ ሰኔ 25/2013 ዓ. ም መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በቪዲዮ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት በሚቀጥለው ዓመት ከሰኔ 15-19/2014 ዓ. ም. በሮም ከተማ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል የሚዘጋጅ መሆኑን አስታውቀው ይህን ፌስቲቫል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶችም በአካባቢያቸው ዝግጅት በማድረግ ምዕመናንን ማሳተፍ የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ወደ ሮም መምጣት የማይችሉ ቤተሰቦችን ለማሳተፍ ተብሎ የታቀደ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መጭው ዓመት ለአሥረኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል በዓለም ዙሪያ የሚገኝ መላውን ካቶሊካዊ ቤተሰብ ለማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ዕቅዶችን የያዘ መሆኑ ታውቋል። ሮም ከተማ የሚቀጥለውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል የምታስተናግድ ይሁን እንጂ ፌስቲቫሉ በዓለም ዙሪያ በሁሉም ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ በታላቅ መንፈሳዊነት የሚከበር መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስታውቀው፣ አጋጣሚው ባለትዳሮች እና የቤተሰብ አባላት ከሐዋርያዊ አባቶች ጋር ሆነው በቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ላይ የሚወያዩበት መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑን ሐዋርያዊ አባቶች የፌስቲቫሉን መርሃ ግብር በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ቤተሰቦች ጋር በመመልከት ከፌስቲቫሉ አስቀድሞ ባሉት ጊዜያት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

ቤተሰባዊ ፍቅር

ከሰኔ 15 - 19/2014 ዓ. ም ሊካሄድ የታቀደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል ዋና ሃሳብ የቤተሰባዊ ሕይወት ለቅድስና የሚያበቃ መለኮታዊ ጥሪ እና ከቤተሰባዊ ፍቅርም ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው መሆኑን ለመግለጽ መሆኑ ታውቋል። ይህን ታላቅ የቤተሰብ ፌስቲቫል ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከሮም ሀገረ ስብከት በመተባበር ሲሆን፣ በዋናነት “የቤተሰብ ፍቅር” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ስድስተኛ ዓመት እና “ደስ ይበላችሁ! ሐሴትም አድርጉ” የሚለው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አራተኛ ዓመት ለማስተወስ መሆኑ ታውቋል። የቤተሰብ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሉ ሌላው ዓላማ “ደስ ይበላችሁ! ሐሴትም አድርጉ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ እንደተገለጸው ለቅድስና መጠራታችንን በመረዳት በደስታ አብሮ ለመኖር የሚያግዝ የ “ቤተሰብ ፍቅር” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን በድጋሚ ለመመልከት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የቤተሰብ ፍቅር” ከሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቀጥለው ባቀረቡት አስተንትኖ፣ የቤተሰባዊ ፍቅር ስጦታ ብዙ እውነተኛ እና ተጨባጭ የሕይወት ልምዶች ያሉት መሆኑን ገልጸው ስጦታው ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ቤተሰብ በእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ በመሆኑ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ እሴቶችን ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባዎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዓመትን እ. አ. አ በ1994 ዓ. ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በተመሳሳይ ዓመት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቤተሰብ ዓመትን በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በማስተዋወቅ የመጀመሪያው የቤተሰብ ፌስቲቫል “ቤተሰብ-የፍቅር ሥልጣኔ መሠረት” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከጥቅምት 8 - 9/1994 ዓ. ም በጣሊያን ሮም ከተማ ውስጥ በድምቀት መከበሩ ይታወሳል።

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “ቤተሰብ-የእግዚአብሔር ስጦታ እና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ የሰው ልጅ ተስፋ” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከጥቅምት 4 – 5/1997 ዓ. ም በብራዚል ሪዮ ዲ ጀኔይሮ ከተማ፣

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “ልጆች ፣ የቤተሰብ እና የኅብረተሰብ ብርሃን” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከጥቅምት 14 – 15/2000 የኢዮቤልዩ ዓመት በጣሊያን ሮም ከተማ፣

አራተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “ክርስቲያናዊ ቤተሰብ-የሦስተኛው ሚሊኒየም ጥሩ ዜና” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከጥር 25 – 26/2003 ዓ. ም በፊሊፒን ማኒላ ከተማ፣

አምስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “በቤተሰብ ውስጥ እምነትን ማስተላለፍ” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከሐምሌ 8 – 9/2006 ዓ. ም በስፔን ቫሌንሲያ ከተማ፣

ስድስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “ቤተሰብ - የሰብዓዊ እና ክርስቲያናዊ እሴቶች መፍለቂያ” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከጥር 17 – 18/2009 ዓ. ም በሜክሲኮ ከተማ፣

ሰባተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “ቤተሰብ - ሥራ እና በዓል” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከሰኔ 2 – 3/2012 ዓ. ም በጣሊያን ሚላኖ ከተማ፣

ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “የእኛ ተልዕኮ ፍቅር፣ የቤተሰብ ሕይወትም እያበበ ይኖራል” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከመስከረም 26 – 27/2015 ዓ. ም በአሜሪካ ውስጥ ፊላዴልፊያ ከተማ፣

ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “የቤተሰብ ወንጌል - የዓለም ደስታ” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከነሐሴ 22 - 26/2018 ዓ. ም በአይርላንድ ዳብሊን ከተማ፣

በሚቀጥለው ዓመት የሚከበረው አሥረኛው አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል “ቤተሰባዊ ፍቅር - ጥሪ እና የቅድስና መንገድ” በሚል ርዕሥ እ. አ. አ ከሰኔ 22 - 26/2022 ዓ. ም. በጣሊያን ሮም ከተማ ሊከበር ዝግጅት እየተደረገበት መሆኑ ታውቋል።

03 July 2021, 14:57