ፈልግ

በምድራችን ዘላቂ ዕድገት ማምጣት እና ምድራችንን ከጥፋት መከላከል በምድራችን ዘላቂ ዕድገት ማምጣት እና ምድራችንን ከጥፋት መከላከል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ማኅበራዊ ኤኮኖሚ እውነተኛ የዕድገት ጎዳና መሆኑን ገልጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአርጄንቲና ለሚገኝ አንድ ክርስቲያናዊ የንግድ ሥራ ማህበራ አስተባባሪዎች በላኩት መልዕክት፣ ማኅበራዊ ኤኮኖሚ መከተል ያለብን እውነተኛ የዕድገት ጎዳና መሆኑን ገልጸው፣ ተወካዮቹ “ለሰው ልጅ ቅድሚያን የሚሰጥ ካፒታሊዝም” በሚል ርዕስ ባካሄዱት ስብሰባ፣ መዋዕለ ንዋያቸውን በጋራ ጥቅም ላይ ማፍሰስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የክርስቲያናዊ ኢኮኖሚ እና ኅብረተሰ እይታ ከርዕዮተ ዓለማዊ እይታ የተለየ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ክርስቲያናዊ ኢኮኖሚ እና ኅብረተሰ እይታ ከኢየሱስ ክርስቶስ መልእክት የመነጨ መሆኑን አስረድተው፣ የሠራተኛ ማኅበራት ፣ ሥራ ፈጣሪዎችና ሠራተኞችን ጨምሮ ሁሉም ሰው በፍትሐዊ ማህበረሰብ ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ” ጥሪ አቅርበው “መራመድ ያለብን እውነተኛ የዕድገት ጎዳና ማኅበራዊ ኤኮኖሚ ነው” በማለት ገልጸዋል።

አንዳንድ የፋይናንስ ተቋማትን አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ብዙ ትርፍ እንደሚገኝበት ብናስብም ውጤቱ ባዶ መሆኑን አስረድተው፣ ወደ ተጨባጭ ለሁሉ ወደሚተርፍ የኤኮኖሚ ጎዳና መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ተጨባጭ ኤኮኖሚ ሲሉ ከምርት አቅርቦት ጋር አያያዘው ይህም ለሰዎች የሥራ ዕድልን ማመቻቸት፣ ቤተሰብን ማስተዳደር መቻል ፣ አገርን እና መላውን ማኅበረሰብ ማሳደግን የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል።

ኢኮኖሚው ሁል ጊዜ ማህበራዊ ይዘት ሊኖረው እንደሚገባ እና ለሰዎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኃይል አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፣ ምክንያቱም “የሥራ ፈጠራ ሁል ጊዜ የሚመጣው ታች ከሚገኘው ማኅበረሰብ ዘንድ ነው” ብለዋል።

ማኅበራዊ መተማመን ግንባታ

መዋዕለ ንዋይን በጋራ ጥቅም ላይ ማፍሰስ እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ገንዘብን በማይታይ በማይጨበጥ ቦታ ከመደብቅ ይልቅ ትርፍ የሚገኝበት እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል። በመሆኑም መዋዕለ ንዋይን ወይም ገንዘብን እንዴት እና የት ማፍሰስ እንደሚቻል ማወቅ እና ግልጽነት የሚያስፈልገው መሆኑን አስረድተዋል። ትክክለኛ ያልሆኑ ስምምነቶች በማድረግ ገንዘብን ለመደበቅ ከመሞከር ይልቅ ቀስ በቀስ ማኅበራዊ መተማመንን መገንባት እንደሚያስፈልግ አሳስበው ምን ጊዜም ቢሆን ማኅበራዊ መተማመን መጥፋት የለበትም ብለዋል።

ለሰው ልጅ ቅድሚያን የሚሰጥ ካፒታሊዝም

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአርጄንቲና ውስጥ 24ኛ ጉባኤያቸውን ከትናንት ሰኔ 23 እስከ 24/2013 ዓ. ም. ላካሄዱት ክርስቲያናዊ የንግድ ሥራ ማህበራት አስተባባሪዎች በላኩት መልዕክት የካፒታሊዝም ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥ እንዴት ብልጽግናን እና ዕድገትን ለሁሉ ሰው ማምጣት እንደሚገባ አስረድተዋል። ዕድገትን ለማምጣት በሚደረግ የሥራ ጥረት መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኤኮኖሚያዊ ጉዳቶችን ማስከተሉን ገልጸዋል። ክርስቲያናዊ የንግድ ሥራ ማህበራት አስተባባሪዎች በጉባኤያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኝ የሰዎች ኑሮ አለመመጣጠን እና ድህነት መኖሩን ገልጸው ቢሆንም ወቅታዊ ችግሮችን በመጋፈጥ የዛሬን እና የነገን ዕድገት ለማረጋገጥ በርትቶ መሥራት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። 

01 July 2021, 16:14