ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታወቁ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከመስከረም 2 - 5/2014 ዓ. ም ድረስ በስሎቫኪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህን ዜና ባበሰሩ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡት የስሎቫኪያ ምዕመናን ደስታቸውን በጭብጨባ ሲገልጹ ታይተዋል። እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም ጠዋት ላይ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የሚመሩ መሆኑን ገልጸዋል። ወደ ስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በመልካም እንዲፈጸም ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያግዟቸው ጠይቀው፣ ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መሳካት ሰፊ ዝግጅት እና የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ቀጥለውም ከሮም ከተማ፣ በጣሊያን ውስጥ ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ለመጡት ምዕመናን፣ ለውጭ አገራት መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ሀገር ጎብኚዎች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት የስሎቫኪያ ምዕመናን እና በአደባባዩ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው መልካም ዕለተ ሰንበትን ከተመኙላቸው በኋላ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

05 July 2021, 20:15