ፈልግ

ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለደም ለጋሾች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሕይወትን ከሞት ለማትረፍ በሚል ዓላማ ደም በመለገስ የሚተባበሩን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ሰኔ 7፣ ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን እንዲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መደንገጉ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያቀረቡት ምስጋና፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ካቀረቡት ምስጋና ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥው መሆኑን በጣሊያን ብሔራዊ የደም ለጋሾች ማህበር ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ጃንፔሮ ብሪዮላ አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 6/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ካቀረቡት ጸሎት በመቀጠል፣ ሰኔ 7 ቀን ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን መሆኑን በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፣ ደም በመለገስ የበርካቶች ሕይወት ከሞት እንዲተርፍ የሚያደርጉትን አመስግነው፣ ይህን በጎ ተግባራቸውን ሳያቋርጡ እንዲያበረክቱ በማለት አበረታትተዋል።

ለሕሙማን ደም በመስጠት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት ለማትረፍ የሚቻል መሆኑ ይታወቃል። ይህ በጎ ተግባር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የበርካቶችን ሕይወት ከሞት ማትረፉ ይታወቃል። ይህን በመገንዘብ በዓለማችን የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ በሚል ዓላማ በየዓመቱ ሰኔ 7 ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን እንዲከበር መደረጉ ይታወቃል። የዘንድሮን ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀንን ጣሊያን እንድታስተባብር የዓለም ጤና ድርጅት መወሰኑ ታውቋል። ዕለቱ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም በሚገኝ ግዙፍ የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረቢያ አዳራሽ ውስጥ የተከበረ መሆኑ ታውቋል። በጎ ፈቃደኞቹ በሥፍራው ተገኝተው ደም መለገሳቸው ታውቋል። በከተማው መሃል የሚገኝ ኮሎሴዎች የተባለ ታሪካዊ ግንብ በቀይ መብራት እንዲያሸበርቅ ተደርጓል።      

“ደም በመለገስ ነፍስ እንዲዘራ ያድርጉ” የሚለው የዘንድሮ መሪ ቃል፣ ወጣቶችን ለመቀስቀስ የቀረበ መሆኑ ታውቋል። የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ዕለቱን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በዓለማችን በተዛመተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወጣቶች እጅግ ቢጠቁም ወረርሽኙን ለመቋቋም ያላቸውን አቅም ማሳየታቸውን አስታውሰዋል። በዓለማችን ውስጥ ደም ከለገሱት መካከል ከፍተኛ ቁጥርን የያዙት ወጣቶች መሆናቸውን አስታውሰው ይህን በማድረጋቸው የበርካታ ሰዎች ሕይወትን ከሞት ማትረፋቸውን አስረድተዋል። እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም. በጣሊያን ውስጥ ደም የለገሱት ሰዎች ቁጥር 1.626.506 መሆኑ ሲነግር አዲስ ደም ለጋሾች ለጋሾች ቁጥር 355.174 መሆኑ ታውቋል።

ቀላል መስሎ ቢታይም በጣም አስፈላጊ ተግባር ነው

በዓለም ጤና ድርጅት አስተባባሪነት ዓለም አቀፍ የደም ልገሳ ቀን እንዲከበር የተደነገገው እ. አ. አ በ2005 ዓ. ም መሆኑ ሲታወቅ፣ ዕለቱ ሦስት የደም ዓይነቶች መኖራቸውን በምርምር ያወቀው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ካርል ላንድስትሬን የተወለደበት ቀን መሆኑ ታውቋል። ይህን ዓለም አቀፍ ቀን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 6/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ካቀረቡት ጸሎት በመቀጠል አስታውሰው፣ ዕለቱ በሕዝቦች መካከል ግንዛቤን በመፍጠር፣ የሰዎችን ነፍስ ከሞት ለማትረፍ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ መልካም ተግባር ቀላል መስሎ ቢታይም በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

አንድ አትራፊ ያልሆነ ድርጅት እ. አ. አ በ1971 ዓ. ም ባዘጋጀው የማስታወቂያ መልዕክቱ፣ ሰዎች ደም በመለገስ የሰዎችን ሕይወት ከሞት እንዲያተርፉ የሚያሳስብ ግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል። በመጀመሪያው አካባቢ ማስታወቂያው ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቶ የተቋረጠ ቢሆንም አንዳንድ የሕክምና ባለሞያዎች ባደረጉት ጥረት ተመልሶ ተግባራዊ ሊሆን መብቃቱ ይታወሳል። ቀጥሎም የጣሊያን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሌላ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፣ ደም በመለገስ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለማትረፍ የተወሰደው ጥረት ውጤታማ መሆኑ ማኅበረሰቡ እንዲያውቀው መደረጉ ይታወሳል። 

14 June 2021, 16:42