ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብሔራዊ የአረጋውያን ሠራተኞች ማህበር አባል ጋር ሲነጋገሩ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብሔራዊ የአረጋውያን ሠራተኞች ማህበር አባል ጋር ሲነጋገሩ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ አረጋዊያን የወጣቶች የወደ ፊት ሕይወት ተስፋ መሆናቸውን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአረጋዊን ላይ የሚደርስ በደል ለማስቀረት በሚል ዓላማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላስተባበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን መልዕክት ልከዋል። በአረጋዊያን ላይ የሚደርስ በደል በተለይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት መበራከቱ ታውቋል። በአረጋዊያን ላይ የሚደርስ በደሉ የገንዘብ ብቻ ስይሆን ተገቢውን እንክብካቤ አለመስጠትን ጭምር ያካትታል ተብሏል። በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ውስጥ የአረጋዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ አስተባባር የሆኑት ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ በአረጋዊያን ላይ ለሚፈጸም በደል ዋና ምክንያቱ የአረጋዊያን ተንከባካቢን አጥተው ብቻቸውን ሲለሚቀሩ መሆኑ አስረድተው፣ አረጋዊያንን ቀርቦ ማገዝ እና ከጎናቸው መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቲዊተር ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ባስተላለፉት መልዕት “ለአረጋዊያን ክብር በማይሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ የወጣቶች የወደ ፊት ተስፋ የጨለመ ይሆናል” ብለዋል። በአረጋዊን ላይ የሚፈጸም በደልን ለማስቀረት በሚል ዓላማ ሰኔ 8/2013 ዓ. ም ዓለም አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ተከብሯል። ዕለቱን ያስተባበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በዓለማችን ወስጥ የኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ከተዛመተ ወዲህ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ተብለው በወጡ ደንቦች ምክንያት አቅመ ደካማ አረጋዊያንን ያለ ረዳት እንዲቀሩ በማድረግ ችግሩን ከፍ ማድረጉ ተነግሯል።

ብቸኝነት ለችግር ያጋልጣል  

በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የአረጋዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ አስተባባሪ ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አረጋዊያንን ያለ ረዳት በማስቀረት ለችግር የዳረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ ብቻቸው በሚቀሩበት ጊዜ ለተለያዩ ችግሮች የሚጋለጡ መሆኑንም አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አረጋዊያን ያለ ረዳት መቅረት እንደሌለባቸው በመልዕክታቸው ብዙን ጊዜ ማሳሰባቸውን ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ አስታውሰው፣ ለአረጋዊያን ሊሰጥ የሚገባውን ክብር በሚቀንስ ባሕል ውስጥ አረጋዊያን ለተለያዩ በደል እና ጉዳት የሚዳረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።  

“እያንዳንዱ አረጋዊ ቅድመ አያታችን ነው”

በአሜሪካ ውስጥ ዕድሜአቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው አዛውንት ባለፉት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወራት ውስጥ የተለያዩ በደሎች እንደደረሰባቸው ሲነገር፣ ይህም የበደሉን ቀማሾች ቁጥር ወደ 84 ከመቶ ከፍ ማድረጉ ታውቋል። በተለይም የገንዘብ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ አስታውሰው፣ አረጋዊያን በቤተሰብ አባላት በኩል ጥበቃ እና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል። ይህን ማድረግ የቤተሰብ ሃላፊነት መሆኑን አስረድተው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አዛውንት ሁልጊዜ በቤተሰብ መካከል ሆነው አስፈላጊው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ማለታቸውን አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ሐምሌ 19/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕምናን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ካቀረቡት ጸሎት በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በመካከላችን የሚገኙ አረጋዊያንን እንደ አያቶቻችን ተመልክተን ቤተሰባዊ ፍቅር እና እንክብካቤን መስጠት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ አስታውሰዋል።

ሐምሌ 18 ዓለም አቀፍ የአረጋዊን ቀን

ሐምሌ 18 በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን የሚከበርበት ቀን እንዲሆን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መወሰናቸው ታውቋል። ዕለቱ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ክርስቲያኖች ዘንድ ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና መታሰቢያ ቀን መሆኑ ታውቋል። በዚሁ ዕለት በበርካታ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን ከአያቶቻቸው እና አረጋዊያን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚካፈሉበት ዕለት እንደሚሆን ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ ገልጸው፣ ዕለቱ ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶችን ጨምሮ በልዩ ልዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን በቁምስናቸው ወይም በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ከሚገኙ አረጋዊያን ጋር ሆነው ምስጋናቸውን ወደ ፈጣሪያቸው የሚያቀርቡበት፣ አንድነታቸውን እና ኅብረታቸውን የሚገልጹበት እንዲሆን በማለት፣ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጥሪ ማቅረቡን፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የአረጋዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ አስተባባሪ ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሸልዞ ተናግረዋል።    

16 June 2021, 14:24