ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቤተክርስቲያን ቤተሰብን በንቃት እንድታዳምጥ ጥሪ አቀረቡ። ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቤተክርስቲያን ቤተሰብን በንቃት እንድታዳምጥ ጥሪ አቀረቡ። 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቤተክርስቲያን ቤተሰብን በንቃት እንድታዳምጥ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትላንት በሰኔ 02/2013 ዓ.ም በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት ቤተክርስቲያን ቤተሰብን በንቃት እንድታዳምጥ እና በሐዋርያዊ ተግባራቷ ውስጥ ቤተሰብን ተሳታፊ እንድታደርግ ጥሪ ማቅረባቸው ተገለጸ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላቲን ቋንቋ “Amoris Laetitia” በአማርኛው የፍቅር ደስታ በሚል አርእስት እርሳቸው ከዚህ ቀደም ያፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ላይ ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ለተሳታፊዎች በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት የሃይማኖት አባቶችን ፣ ባለትዳሮችን እና ቤተሰቦችን በስብከተ ወንጌል ተልእኮ ያሳተፈ ትብብር አስፈላጊነትን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ በላቲን ቋንቋ “Amoris Laetitia” የፍቅር ደስታ በሚል አርዕስት እርሳቸው እ.አ.አ በመጋቢት 2016 ዓ.ም ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ አምስኛ አመት ረቡዕ እለት ሰኔ 02/2013 ዓ.ም በተዘከረበት ወቅት ይህ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ተግባራዊ የሚሆንበት ስልት ለመቅረጽ ታስቦ የምዕመናንን፣ የቤተስበን እና ሕይወትን በተመለከተ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የሚከናወኑትን ተግባራት በበላይነት በሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ቅዱስነታቸው ለተሳታፊዎች ንግግር አድርገዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቪዲዮ መልእክት እንዳመለከቱት መድረኩ በቅድስት መንበር ፣ በጳጳስት ምክር ቤት ጉባሄ፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የምያስተባብሩ መንፈሳዊ ማሕበራት እና በቤተሰብ ማህበራት መካከል የተጠናከረ ግንኙነት እንዲኖር በላቲን ቋንቋ “Amoris Laetitia” የፍቅር ደስታ የተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ አስመልክቶ የቤተሰብ ዓመት መከበር እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የውይይት ጊዜን የሚወክል መሆኑን የገለፁት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በታህሳስ 27/2020 ዓ.ም ላይ በቫቲካን የመላከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት ለአንድ አመት የሚቆይ የቤተሰብ ቀን እንዲከበር መወሰናቸው ይታወሳል።

ይህ የሆነበት ምክንያት መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን ፣ ለቀሳውስት እና ለምእመናን አንድ ላይ ሆነው የቤተሰብን ተጨባጭ ፍላጎቶች ለማዳመጥ እና የሐዋርያዊ ማሳሰቢያውን ጭብጥ ሐሳብ ለማደስ የሚያስፈልጉትን ሂደቶች ለማከናወን እርስ በእርስ እንዲተባበሩ አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ያደርጋቸዋል በሚል ሕሳቤ እንደ ሆነ ገልጸዋል።

ከሰኔ 02 እስከ ሰኔ 5/2013 ዓ.ም በበይነ መረብ አማካይነት እየተካሄደ በሚገኘው ስብሰባ ላይ ከተለያዩ አገራት የጳጳሳት ጉባሄ ምክር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ቤተሰብን የተመለከቱ ማሕበራት የተውጣጡ 60 ተወካዮች እና ከ 30 በላይ ዓለም አቀፍ የመንፈሳዊ ንቅናቄዎች ተወካዮች በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ እንደ ሚገኝ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። ተሰብሳቢዎቹ “የፍቅር ደስታ ከሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ጋር የት እንቆማለን” በሚል መሪ ቃል ስብሰባቸውን እያከናወኑ እንደ ሚገኝ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ተግባራዊ የሚሆንበትን ስልቶች ይቀይሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቤተሰብ ላይ ቤተክርስቲያን ያላትን አስተውሎ በድጋሚ ማነቃቃት

የስብሰባውን ጭብጥ ሐሳብ በመልእክታቸው የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ከአዲሱ የወንጌል ስርጭት አንፃር ለቤተሰብ የሚደርገውን ሐዋርያዊ እንክብካቤ እና ዓላማዎች ላይ ውጤታማ የሆነ የቤተ-ክርስቲያን ግንዛቤን ለማነቃቃት የታሰበ ነው” ብለዋል።

የተጠየቀው ምክር የፍቅር ደስታ በተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት “በጋብቻ እና በቤተሰብ ላይ የተደረገው ጥልቅ የሆነ ሲኖዶስ ነፀብራቅ ፍሬ በመሆኑ እንደዚሁ በአተገባበሩ እና በተልዕኮ መለወጥ ሂደት ውስጥ ትዕግስት ይጠይቃል” ብለዋል።

ከዚህ አንፃር መድረኩ “በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ መሆን መቻል ያለበት ከሲኖዶሱ መንገድ ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብር ፣ ኃላፊነት መጋራት ፣ የመረዳት ችሎታ እና ለቤተሰብ ቅርብ የመሆን ፍላጎት” ማሳየት ይጠይቃል ብለዋል።

በስብከተ ወንጌል ውስጥ ቤተሰብን ማሳተፍ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በቤተክርስቲያኒቱ ተልዕኮ ውስጥ ቤተክርስቲያን እና አገልጋዮቿ ቤተሰብን በንቃት እንዲያዳምጡ እና እንደ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ቤተሰብን ተሳታፊ ማደረግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በተለይም በወረርሽኙ ምክንያት በተከሰቱት ችግሮች መካከል “የቤተሰብን ህይወት እና የቅርብ ህብረት እና ፍቅር ” በቤተሰብ ውስጥ ጸንቶ ይኖሩ ዘንድ በጋራ አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የእግዚአብሔርን ፍቅር ለቤተሰብ እና ለወጣቶች ማምጣት እንደ ሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው “እኛ ራሳችን የቤተሰብ እገዛ ፣ ተጨባጭ የሕይወት ልምዳቸውን እና የኅብረት ልምዳቸውን እንፈልጋለን። ከቀሳውስት ጎን ለጎን የትዳር አጋሮች ያስፈልጉናል ፣ ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ለመራመድ ፣ ደካማ የሆኑትን ለመርዳት ፣ በችግሮችም እንኳ ቢሆን ፣ ክርስቶስ በሁሉም የትኛውም ሁኔታ ውስጥ ርህራሄን ፣ ትዕግሥትን እና ተስፋን ለመስጠት ክርስቶስ በምስጢረ ተክሊል ውስጥ በመገኘት ሕይወት እንደ ሚሰጥ ማስተማር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ ሰዎች “የወንጌል አገልግሎት ወኪሎች” መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ከሰዎች እውነተኛ ችግሮች ጋር ሳይገናኙ የንድፈ ሀሳብ መልዕክቶችን ብቻ መተለም አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጸው እንዲሁም የቅዱስ ወንጌል ስርጭት እና ሐዋርያዊ ተግባራት ለቀሳውስት እና ለልሂቃን ብቻ የተተወ ተግባር እንዳልሆነ ቅዱስነታቸው አክለው ገለጸዋል።

ለተልእኮው የጋራ ሃላፊነት መቀበል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ጋብቻ ፣ እንደ ክህነት ሁሉ የእግዚአብሔርን ህዝብ ለማነጽ የሚያገለግል ሲሆን በቤተክርስቲያኗ የሕነጻ ትምህርት ውስጥ ለትዳር አጋሮች ልዩ ተልእኮ ይሰጣቸዋል” ብለዋል።

ስለሆነም ቤተሰቡ ክርስቶስ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ በባለትዳሮች መካከል መገኘትን የሚገልጽ እና እንዲሁም በወላጆች እና በልጆች መካከል የሚሰራበት ‘የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ምልክት ነው’ ያሉት ቅዱስነታቸው  “በቤተሰብ ውስጥ ያለው የፍቅር ተሞክሮ ለቤተክርስቲያኗ ሕይወት የማያቋርጥ የጥንካሬ ምንጭ ነው” ስለዚህ በምስጢረ ተክሊል መሠረት “እያንዳንዱ ቤተሰብ ለቤተክርስቲያኑ መልካም ውጤት ያስገኛል” ብለዋል።

በዚህ እይታ ለተልእኮው የጋራ ሃላፊነት ባለትዳሮች እና የተሾሙ አገልጋዮች በተለይም ጳጳሳት በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት እንክብካቤ ማድረግ እና መተባበርን ይጠይቃል ያሉ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም “እኛ ቀሳውስት መንፈስ ቅዱስ ሕሊናችንን እንዲያበራ መፍቀድ አለብን፣ ስለሆነም ይህ የመዳን አዋጅ ብዙውን ጊዜ ለማወጅ ዝግጁ የሆኑ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በሂደቱ ውስጥ መሳተፍ ያልቻሉ ባልና ሚስቶች በሂደቱ ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን” ቅዱስነታቸው በንግግራቸው አውስተዋል።  “እንደ ተባዕታይ እና አንስታይ በልዩነታቸው እና በአንድነታቸው ላይ ተመስርተን የቤተሰብን ጥምረት ለማጉላት በመጣር የቅዱስ ትዕዛዛት እና የጋብቻ ሥነ-ሥርዓቶችም በቤተሰብ ደረጃ እንደመገንባታቸው ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው ” ብለዋል።

አዲስ እይታ በሐዋርያዊ ማሳሰቢያው ላይ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለተሳታፊዎቹ አክለው እንደ ገለጹት “አዲስ እይታ” እንዲመለከቱ የስብሰባውን ተሳታፊዎች የጋበዙ ሲሆን “በውስጣቸው ከተዘረዘሩት የሐዋርያዊ እንክብካቤ ተግባራት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉድዮች መካከል ከእያንዳንዱ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ተጨባጭ ፍላጎቶች ጋር የሚስማሙ እና በፈጠራ ተግባራት የታጀበ እና ለተግባራዊነቱም ሚስዮንዊ የሆነ ቅንዓት ” ያስፈልጋል ብለዋል።

በላቲን ቋንቋ Evangelii gaudium  በማርኛው “በወንጌል የሚገኝ ደስታ” በሚለው ጳጳሳዊ መልእክት የፕሮግራም እሴት እና አሁንም በላቲን ቋንቋ “Amoris Laetitia” የፍቅር ደስታ በተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ውስጥ እንደ ተገለጸው ለቤተሰብ የሚደረገው ሐዋርያዊ እንክብካቤ በተገለጸው ተጨባጭ የሐዋርያዊ እንክብካቤ አገልግሎት መርሃ ግብር መነሻነት ሁሉም ህብረተሰብ በሚስዮናዊነት ጎዳና ለመጓዝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምዕመናን በተለይም ባለትዳሮች እና የቤተሰብ ምስረታ ላይ ልዩ ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል ፣ ምክንያቱም የቤተክርስቲያናቸው ቃልኪዳን አስፈላጊነት እና ባለትዳሮች እና ቤተሰብ የመሆን ተልእኮ በተሻለ እንዲገነዘቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስ አባታችን በመቀጠል ቤተክርስቲያኗ በቤተሰብ ውስጥ ያለውን አንዳንድ ተግዳሮቶች ለመፍታት ይቻል ዘንድ የታደሰ ሐዋርያዊ የሆነ ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑን አክለው የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም “የጋብቻ ዝግጅት ፣ ወጣት ባለትዳሮች በሐዋርያዊ አገልግሎት ማጀብ ፣ ትምህርት ማስተማር ፣ ለአረጋውያን ትኩረት መስጠት ፣ ለቆሰሉት ቤተሰቦች ወይም በአዲሱ ህብረት ውስጥ ክርስቲያናዊ ልምድን ሙሉ በሙሉ ለመኖር የሚፈልጉ ”ሰዎችን በመንፈሳዊነት መርዳት ይኖርብናል ብለዋል።

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ተናገሩት ስብሰባው ሀሳቦችን እና የሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ልምዶች ለመካፈል እንዲሁም የዘመኑ ምልክቶችን ተመልክተን ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ረገድ በጣም ውጤታማ በሆነ መንገድ የቤተሰብን ወንጌል ለማወጅ የሚረዳ ትስስር እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት የገለጹ ሲሆን በመጨረሻም የስብሰባው ተካፋዮች ለእርሳቸው ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ ካደረጉ በኋላ የመድረኩ ተሳታፊዎች ለእመቤታችን እና ለቅዱስ ዮሴፍ አማላጅነት አደራ እሰጣለሁ በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

09 June 2021, 11:47