ፈልግ

ር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከሕግ ታራሚዎች ጋር ር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከሕግ ታራሚዎች ጋር 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሕግ ታራሚዎችን ማጽናናት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ከሕግ ታራሚዎች ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል። ሥነ ሥርዓቱን በማስመልከት ለሕግ ታራሚዎቹ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኙ ክቡር አባ ሞሬኖ ቨርሶላቶ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገገለጹት ቅዱስነታቸው ከሕግ ታራሚዎች ጋር ሆነው በኅብረት መጸለያቸው እና ማጽናናቸው ቤተክርስቲያን በእናትነት ፍቅር ወደ ሁሉ የዓለም ክፍል ለመድረስ መዘጋጀቷን ይገልጻል ብለዋል። አክለውም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ብዙ ሰዎች ያለ ተንከባካቢ መቅረታቸውን አስረድተው ይህም የብዙዎችን ሕይወት ችግር ውስጥ መጣሉን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከተማ ውስጥ ሬቢቢያ በሚባል አካባቢ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ሐዋርያዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኙት አባ ሞሬኖ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቅዱስነታቸው የሕግ ታራሚዎችን ወደ ቫቲካን መጥራታቸው ለታራሚዎቹ ትልቅ ስጦታ ነው ብለው በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙዎችን እየጎዳ ባለባት ባሁኑ ወቅት ትልቅ መጽናናት እና ብርታት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ክቡር አባ ሞሬኖ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከማኅበረሰቡ ተገልለው በብቸኝነት ሕይወት፣ በችግር እና በሐዘን ለሚገኙት በሙሉ በሚያሳዩት ቸርነት፣ በዘወትር ፍቅራቸው እና ትህትናቸው፣ በቫቲካን ተቀብለውን ሲያስተናግዱን የሕግ ታራሚዎች የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። አባ ሞሬኖ አክለውም ቅዱስነታቸው የወሕኒ ቤት ሕይወት ምን እንደሚመስል እና ለሕግ ታራሚዎች የሚሰጡት ክብር ከፍተኛ መሆኑን እናውቃለን ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሕግ ታራሚዎች ሕይወት ከባድ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ቢሆንም ከሕይወት ክፍል አንዱ በመሆኑ በትዕግስት ተቀብሎ መኖር እንደሚያስፈልግ መምከራቸውን ክቡር አባ ሞሬኖ ገልጸዋል። በሮም ከተማ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ለሕግ ታራሚዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኙት ክቡር አባ ሞሬኖ፣ ቅዱስነታቸው በሌሎች አገሮች ከእነዚህም መካከል በአርጄንቲና ቦይኔስ አይረስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ከምኖሩት የሕግ ታራሚዎች ጋር በየጊዜ በስልክ በመገናኘት የሚያጽናኑ እና የሚያበረታቱ መሆኑን አስታውሰዋል። በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ ማረሚያ ቤት የሚኖሩ ታራሚዎችም በየምንቱ እሑድ በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸው ቅዱስነታቸውን የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ከእያንዳንዱ የሕግ ታራሚ ጋራ እጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጣቸው እና በፍቅር ልብ ተቀብለው ማነጋገራቸውን የገለጹት ክቡር አባ ሞሬኖ፣ ይህ የቅዱስነታቸው ምሳሌ ቤተክርስቲያን ዛሬ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር በእናታዊ ፍቅር ተገናኝታ ለማጽናናት እና ለማበረታታት የተነሳች መሆኑን ያመላክታል ብለዋል። የቅዱስነታቸውን ምሳሌ እያንዳንዱ የሕግ ታራሚ ከልብ የተረዳው መሆኑንም ክቡር አባ ሞሬኖ ገልጸዋል።

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት አስፈላጊ ነገር መነፈጋቸውን ያስታወሱት ክቡር አባ ሞሬኖ አስታውሰው፣ የባለቤት፣ የልጅ፣ የወዳጅ እና የጓደኛ ፍቅር እና አለኝታ መጉደሉን አስረድተው፣ የሕግ ታራሚዎቹ ከቤተስብ አባላት እና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የስልክ ጥሪ ግንኙነት የሚያደርጉ ቢሆንም ፊት ለፊት መተያየትን፣ በአካል መገናኘትን የሚያህል የለም ብለዋል። ይህ መጉደሉ በርካታ የሕግ ታራሚዎችን እያስጨነቀ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በማረሚያ ቤቶች በመገኘት ለሕግ ታራሚዎች ቀጣይነት ያለውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማቅረብ በተለይም በከባዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፣ ሐዋርያዊ አገልጋዮቹ የሕግ ታራሚዎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት፣ መልዕክቶቻቸውን፣ ሃሳቦቻቸውን እና ምኞታቸውን እንዲለዋወጡ ማገዝ፣ ቅዱስ ቃሉን በማካፈል መጽናናትን እና ብርታትን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ይህ ካልሆነ የሕግ ታራሚዎች ከማኅበረሰቡ መካከል ሙሉ በሙሉ እንደተገለሉ ቆጥረው ጭንቀት የሚሰማቸው መሆኑን በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ለሕግ ታራሚዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙት ክቡር አባ ሞሬኖ ቨርሶላቶ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። 

22 June 2021, 16:50