ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሕጻን ናሆሚ ጋር ሆነው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሕጻን ናሆሚ ጋር ሆነው፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሰዎች ክፉ ተግባር ተስፋን ቢያጨልምም ጠንክሮ መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሰኔ 1/2013 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ከሕጻን ናሆሚ ጋር ጸሎት ማቅረባቸው ታውቋል። ሕጻን ናሆሚ በጣሊያን የናፖሊ ከተማ ነዋሪ ስትሆን፣ ያለፈው አውሮፓዊያኑ ዓመት 2019 በከተማው አደባባይ በተካሄደ አንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ በተነሳ ተኮሰ ጉዳት የደረሰባት መሆኑ ይታወሳል። ትናንት በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመ ሲሆን በሥነ-ሥርዓት ላይ ከሕጻን ናሆሚ ወላጅ ቤተሰብ ጋር የናፖሊ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ባታሊያም ተገኝተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት “ምንም እንኳን የማፊያ ቡድን ተስፋን ለማጨለም ቢሞክርም በርትቶ ወደ ፊት መጓዝ ይስፈልጋል” በማለት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕጻን ናሆሚ እናት ትናንት በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤተ የተካሄደውን ሥነ-ሥርዓት በማስመልከት ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ልጃቸው ናሆሚ ከሞት ተርፋ በሕይወት መቆየቷ ተስፋን የሚሰጥ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ብርታትን የጨመረላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በልጃቸው የመቁሰል አደጋ ቢያዝኑም በሕይወቷ መትረፏ ተዓምር ነው ብለዋል።

አባ ሚሞ የሰጡት ተስፋ

ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ያጋጠማት ሕጻን ናሆሚ ከሞት መትረፏ ሲነገራቸው ወላጅ ቤተሰቦቿ አንድ ምኞት ብቻ እንደነበራቸው፣ ይህም ከር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር መገናኘት መሆኑን አስረድተዋል። በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙት ሁለቱ የናሆሚ ወላጆች በወቅቱ የናፖሊ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብጹዕ ካርዲናል ክሬሸንሶ ሰፔ ወይም በቀድሞ ስማቸው ከክቡር አባ ሚሞ ጋር ተገናኝተው ልጃቸው ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር የሚገናኙበትን መንገድ ሲያመቻቹ መቆየታቸው ታውቋል። ነገር ግን ከቅዱስነታቸው ጋር የመገናኘት ዕቅዳቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ቢሆንም አባ ሚሞ በሰጡት ተስፋ እና በገቡላቸው ቃል መሠረት ትናንት ሰኔ 1/2013 ዓ. ም እውን መሆኑን የናሆሚ እናት ወ/ሮ ታኒያ ደስታ በተመላበት አንደበት ገልጸዋል።

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር የነበራቸው ቆይታ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የማግኘት ዕድል በቀላሉ የሚገኝ አለመሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ታኒያ፣ ቅዱስነታቸው ከልጃቸው ናሆሚ ጋር “’ሰላም ላንቺ ይሁን’ ጸሎት እና ወደ ‘ጠባቂ መልአክ’ ጸሎታቸውን አብረው ማድረሳቸውን ወ/ሮ ታኒያ ገልጸዋል።

የልጃቸውን ታሪክ ለቅዱስነታቸው ያስረዱት የናሆሚ ወላጆች፣ ያለፉት ሁለት ዓመታት ከባድ እንደነበሩ ገልጸው፣ ልጃቸው ናሆሚ በሚቀጥሉት ጊዜያትም ተከታታይ ሕክምናዎችን የምታደርግ መሆኗን ገልጸዋል። የናሆሚ ወላጆች ለቅዱስነታቸው ስጦታን ያቀረቡላቸው ሲሆን ከቅዱስነታቸውም በኩል ለናሆሚ ወላጆች የመቁጠሪያ ስጦታ ተሰጥቷቸዋል።  

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት

ሕጻን ናሆሚ በናፖሊ አካባቢው በሚንቀሳቀስ አንድ የማፊያ ቡድን በተተኮሰ ጥይት ጉዳት የደረሰባት መሆኑን ወ/ሮ ታኒያ ገልጸው “ናሆሚ በናፖሊ አደባባዩ የተገኘችበት ምክንያት የኮንቲ መንግሥት ያጸደቀው ደንብ ናሆሚን የሚመለከት ማኅበራዊ ርዕሠ ጉዳይ በመሆኑ ነው” ብለዋል። ትናንት ሰኔ 1/2013 ዓ. ም ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት ቅዱስነታቸው ለናሆሚ ቤተሰብ አጭር መልዕክት ማስተላለፋቸውን የገለጹት ወ/ሮ ታኒያ “የማፊያ ቡድን ተስፋ ቢያጨልምም፣ ሰብዓዊ መብትን ቢረግጥም፣ እግዚአብሔር ከልጃችሁ ናሆሚ ጋር በመሆን የዕለት እርምጃዎችዋን በመከታተል ያጠብቃታል” በማለት ቅዱስነታቸው ያጽናኗቸው መሆኑ ገልጸው፣ በሥነ-ሥርዓቱ ፍጻሜ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና ከክቡር አባ ሚሞ ጋር የሕብረት ጸሎት ማድረሳቸውን እና የማስታወሻ ፎቶ መነሳታቸውን የናሆሚ እናት ወ/ሮ ታኒያ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

የልጃቸውን ጤና በተመለከተ አሳሳቢ ጊዜ አልፎ ናሆሚ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኗን የገለጹት ወ/ሮ ታኒያ፣ የነበረችበትን ሁኔታ ሲያስታውሱት እና አሁን ዶክተሮችም ካረጋገጡላት ጋር ሲያወዳድሩት፣ ልጃቸው ናሆሚ በጤናዋ ከፍተኛ ለውጥን ማሳየቷን አስረድተዋል። የደረሰባት የጀርባ አጥንት ጉዳት ጥንቃቄ የታከለበት ተከታታይ የሕክምና ዕርዳታን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተው “እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ይፈውሰናል” በማለት አስረድተዋል። በልጃቸው ላይ ይህን የመሰለ ጉዳት ከፈጸሙት ሰዎች መከከል አንድም ሰው ይቅርታ የጠየቀ አለመኖሩን የናሆሚ እናት ወ/ሮ ታኒያ ገልጸው፣ ነገር ግን ልጃቸው ናሆሚ ያቆሰሏትን እና ለዚህ አደጋ እና ሕመም የዳረጓትን በሙሉ ይቅር እንዳለቻቸው ተናግረው፣ ልጃቸው ሕጻና ናሆሚ “ሁሉን ማፍቀር እንደሚገባ ወላጅ ቤተሰቦቿን ጨምሮ ሁላችንንም አስተንራናለች” ብለዋል።       

09 June 2021, 15:37