ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔር አረጋዊያንን በመላእክቱ በኩል የሚጎበኛቸው መሆኑን ገለጹ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊከበር የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋዊያን ቀንን በማስመልከት ባተላለፉት መልዕክት፣ እግዚአብሔር ዘወትር ከዕድሜ ባለጸጎች ጋር ሆኖ እንደሚረዳቸው እና እነርሱም ጥሪያቸውን በመጠበቅ እና በማክበር እምነትን ለአዲሱ ትውልድ እንዲያስተላልፉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ መጭው ሐምሌ 18/2013 ዓ. ም ለመጀመሪያ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአያቶች ቀንን በማስመልከት ትናንት ሰኔ 14/2013 ዓ. ም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በማቴ. 28:20 ላይ “እነሆ እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚለውን ጥቅስ የበዓሉ መሪ ቃል አድረገው መርጠዋል። ቅዱስነታቸው ለአያቶች እና አረጋዊያን ባስተላለፉት መልዕክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ አስቀድሞ፣ በማቴ. 28:20 ላይ ለሐዋርያቱ “እነሆ እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት የገባላቸው ቃል መኖሩን አስታውሰው፣ በዚህ መሠረት ዛሬ መላዋ ቤተክርስቲያን አረጋዊያንን ብቻቸውን ሳትተው ከጎን በመቆም የምትንከባከባቸው እና የምትወዳቸው መሆኗን ገልጸዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት መላው ዓለማችን በተለይም አረጋዊያን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተጎዳበት ወቅት ሲሆን፣ ባሁኑ ወቅት በቁጥር በርካታ ሰዎች በወረርሽኙ የተጠቁበት፣ ብዙዎች የሚወዷቸውን በሞት የተለዩበት፣ ከማኅበረሰብ ተነጥለው ለብዙ ወራት ብቻቸውን የሆኑበት ወቅት መሆኑን ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው አስረድተዋል። ይህ ጊዜ አስጨናቂ መሆኑን እግዚአብሔር ይረዳዋል ብለው፣ እግዚአብሔር ብቸኝነት ከሚሰማቸው፣ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ብቸኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር እግዚአብሔር መኖሩን አስረድተዋል። ይህን ካስረዱ በኋላ የኢየሱስ ክርስቶስ አያት የሆነውን ቅዱስ ኢያቄምን በማስተወስ፣ ቅዱስ ኢያቄም በዙሪያው ካሉ ሰዎች ተለይቶ ብቸኝነት በተሰማው ጊዜ ከጌታ መልአክ መጽናናትን ያገኘ መሆኑን አስታውሰዋል።

እግዚአብሔር በመላዕክቱ እና በመልዕተኝቹ በኩል ቃሉን ይልካ

በጨለመብን፣ ኑሮ በከበደን እና በብቸኝነት ወቅት መልአክቱን በመላክ እግዚአብሔር የሚያጽናናን መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አስታውሰዋል። የእግዚአብሔር መልአክት አንዳንድ ጊዜ ሕጻናትን በመምሰል፣ የቤተሰብ ወገን በመምሰል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በቅርብ የምናውቃቸው ወዳጆቻችን በመምሰል በዚህ ከባድ ወቅት እንደሚጎበኙን ገልጸው፣ በዚህ ወቅት አንዳችን ለሌላው ምን ያህል ጠቃሚ መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል ብለዋል። እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ አማካይነት መልዕክተኞችን እንደሚልክ አስታውሰው፣ አረጋዊያን በየቀኑ የቅዱስ ወንጌል ምዕራፎችን እንዲያነቡ፣ የዳዊት መዝሙሮችን በመድገም እንዲጸልዩ እና የነቢያትን ትንቢት እንዲያነቡ አደራ ብለዋል። ቅዱሳት መጽሐፍት እግዚአብሔር ለሕይወታችን በመራራት፣ በየሰዓቱ እና በየቀኑ፣ በማንኛውም ወቅት የወይኑን ተክል የሚንከባከቡ ጠባቂ ሠራተኞችን የሚልክ መሆኑን አስረድተዋል።

የአረጋዊያን ጥሪ

በማቴ. 28: 19-20 ላይ የተጻፈውን በማስታወስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን “እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ ፤ በአብ እና በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም እያጠመቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ አስተምሯቸው ፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ማለቱን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ይህ ጥቅስ አረጋዊያን የተጠሩበት ዓላማ እንዳላቸው በሚገባ እንደሚያስረዳ ገልጸው፣ ካለፉት የእምነት አባቶች የተቀበሉትን አደራ በማክበር ጥሪያቸውንም ተገንዝበው እምነትን ለአዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለባቸ አሳስበዋል። በዮሐ. 3:4 ኒቆዲሞስ ኢየሱስን “ታዲያ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?” በማለት የጠየቀውን በማስታወስ አረጋዊያን በአእምሮአቸው ሊመጡ የሚችሉ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም አዲስ ነገር መሥራት እንዲጀምሩ ጠይቀዋል። ለመንፈስ ቅዱስ ልባችንን የምንከፍት ከሆነ እርሱ ወደ ፈለገው አቅጣጭ ሊመራን ይችላል ብለዋል።

ከችግር ውስጥ መውጣት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለው ቀውስ ለመውጣት የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ ከወረርሽኙ ቀውስ ስንወጣ አንድ ዕድል ብቻ መኖሩን ይህም ወደ ክፋ ችግር ውስጥ መግባት፣ ካልሆነ ከችግር ተላቅቀን በአዲስ ምዕራፍ አዲስ ሕይወት መኖር እንችላለን ብለዋል። አንዳችን ለሌላው እናስፈልጋለን ምክንያቱም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን ብለው፣ በዚህ መሠረት አርጋዊያን ወንድማማችነትን እና ማኅበራዊ ወዳጅነትን በመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖን ማበርከት ይችላሉ ብለዋል።

መልካምን መመኘት ታሪክን ማስታወስ እና መጸለይ እንደሚገባ

መልካምን መመኘት ያለፈውን ታሪክ ከማስታወስ ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስረዱት ቅዱስነታቸው ባለፉት ታሪኮች ጦርነት ያስከተለው ሕመም መኖሩን አስታውሰው፣ ከዚህ በተለየ የሰላምን ታላቅ እሴት ወጣት ትውልድን ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ያለ ጠንካራ መሠረት ቤትን መገንባት እንደማይቻል ሁሉ ያለፈውን ታሪክ መዘንጋት አንችልም ብለዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የብጹዕ ሻርል ዴ ፉኩልድ ምሳሌነት ለአረጋዊያን በማስታወስ፣ በብቸኝነት ጊዜም ቢሆን የመላው ዓለም ድሆችን በጸሎት በማስታወስ የሁሉ ወንድም እና እህት መሆን እንደሚቻል ገልጸው፣ ሁላችንም ልባችንን ከፍተን በድሆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ሳንዘነጋ በጸሎታችን ልናስታውሳቸው ይገባል ብለዋል።  

22 June 2021, 16:33