ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ጋር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ጋር  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምስራቅ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሕያው የእምነት እሴቶቿን እንድትንከባከብ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል ሰላምታ ተለዋውጠዋል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የምስራቅ ቤተክርስቲያን ሥርዓት አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምስራቃዊ የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚያካትቱ እና “ሕያው ድንጋዮች” የሆኑ እሴቶችን እንድትንከባከብ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ድርጅቶች 94ኛ ዙር ጉባኤያቸውን ማካሄዳቸው ታውቋል። አራት ቀናት የቆየ ጉባኤያቸውን ሐሙስ ሰኔ 17/2013 ዓ. ም የፈጸሙት የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ድርጅቶች ጉባኤያቸውን ባጠቃለሉበት ዕለት በቫቲካን ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ባተላለፉት ምልዕክት አባላቱ በአካል ተገናኝተው ለመወያየት በመቻላቸው የተሰማቸውን እርካታ ገልጸዋል። ቀጥለውም እርስ በርስ ተገናኝቶ መወያየት እና መመካከር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው በችግር እና መከራ ውስጥ ከሚገኝ ዓለማችን በተለይም ዕርዳታ በሚቀርብበት አገር የምትገኝ ቤተክርስቲያን ጥያቄ በማድመጥ ውጤታማ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በቅርቡ በኢራቅ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ያገኙትን መልካም ልምድ አስታውሰዋል።

የሊባኖስ ቀውስ

ለጉባኤው ተካፋዮች ባቀረቡት መልዕክት መካከል ሁለቱን አገራት እነርሱም ኤርትራን እና ሊባኖስን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እ. አ. አ ነሐሴ 4/2020 ዓ. ም. በቤሩት የባሕር ወደብ የተከሰተው ከባድ አደጋ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል። ቤይሩትን ለመርዳት ለተደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ሰኔ 24/2013 ዓ. ም በሊባኖስ የሚካሂዱትን ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራው በጸሎት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

‘ሰው የማይታይባቸው የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች’

በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች ለሚያደርጉት ጥረት የቸርነት እጃቸውን ለዘረጉ የመላው ዓለም ምዕመናንን ቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም ለቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የተሰበሰበው የዕርዳታ መጠን በግማሽ መቀነሱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህ የሆነበት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቤተክርስትያና ተዘግተው በመቆየታቸው እና ወረርሽኙ ባስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። ባሁኑ ጊዜ ‘ሰው የማይታይባቸውን የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች’ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረግ መንፈስዊ ጉዞ መቋረጡን ገልጸው፣ መንፈሳዊ ተጓዦቹ ወይም ነጋዲያን ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚጓዙት የእምነት ጥንካሬን ለማግኘት እና የአካባቢውን ነዋሪ ለማገዝ መሆኑን አስታውሰው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን ይህን የቸርነት ተግባር መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሰላም መሣሪያ

የጉባኤውን የመወያያ ርዕሠ ጉዳይ ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጸሎታችን የምናስታውሳቸው እና ወደ ሰላም ጎዳና እንደሚመለሱ ተስፋ ያደረግንባቸው ሁለቱ አገራት እነርሱም እስራኤል እና ፍልስጤም እግዚአብሔር ለኖኅ እንደ ምልክት ያሳየውን የሰላም ቀስት አስታውሰው በሕዝቦቻቸው መካከል ሰላም እንዲመጣ፣ በሁለቱም አገሮች ውስጥ ጥፋትን፣ ሞትን እና ፍርሃትን የሚያስከትል ጦርነት እንዲቆም ሁለቱም ወገኖች ቅን ፍላጎት እንደሚያሳዩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።  

የሶርያ ሕዝብ ስቃይ

በሶርያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ያስታወሱ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ዕርዳታን በመለመን ላይ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ያም ሆኖ ግን የሕዝቡ ስቃይ የመሪዎችን ልብ የነካው አይመስልም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ለሆኑንት ለብጹዕ ካርዲናል ማሪዮ ዘናሪ እና በስብሰባው ላይ ለተገኙት ለሊባኖስ ፣ ለኢራቅ ፣ ለኢትዮጵያ ፣ ለአርሜኒያ እና ለጆርጂያ ጳጳሳት ተወካዮች ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የወንጌል ሕይወት እርሾ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ጋር ያደረጉትን ቆይታ ከመፈጸማቸው በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ትግራይ ክልል የሚታየውን የሕዝብ መከራ አስታውሰው፣ መከራው ወደ አጎራባች አገር ኤርትራም ሊተርፍ ይችላል ብለዋል። የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች በጆርጂያ እና በአርሜኒያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን የወንጌል ሕይወት እርሾ እንዲሆኑ ለሚያደርጉት እገዛ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ለጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ሰጥተዋል። 

24 June 2021, 16:22