ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከሚገኝ የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናት ጋር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከሚገኝ የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናት ጋር  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ካህናት አገልጋዮች እንጂ የበላይነት ሊሰማቸው አይገባም አሉ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናትን በቫቲካን በተቀበሉቸው ጊዜ ባደረጉት ንግግር ካህናት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንጂ የበላይነት ህልም ያላቸው እንዳልሆኑ ገልጸው፣ በመካከላቸው የሚታየው ወንድማማችነት፣ ራስ ወዳድነትና ልዩነት በሚንጸባረቅበት በዛሬው ዓለም ውስጥ ምስክርነትን የሚሰጥ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በሮም ከተማ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርታችውን በመከታተል ላይ የሚገኑት የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናት ራሳቸውን ከመነጠል፣ ከሐሜት እና ስም ከማጥፋት ፈተና እንዲርቁ አሳስበው፣ ካህናት ምዕመናንን እንዲመስሉ፣ ከምዕመናኑ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዘመኑን እውነታ ለመረዳት ከግለኝነት አቋም መውጣት እንደሚያስፈልግ የተነገሩት ቅዱስነታቸው፣ ካህናት ራስን ከፍ ለማድረግ ካላቸው ምኞት ወጥተው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት፣ የወንድማማችነት እና የአንድነት መገድን ለመገንባት የሚመኙ መሆን አለባቸው ብለዋል። በዕለታዊ ሕይወታቸው ራስን ከማስቀደም ይልቅ እግዚአብሔርን እና የሚያገለግሉትን ሕዝብ ማስቀደም፣ በአሉ ባልታ ወሬም መደናገር እንደሌለባቸው አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ መጋቢት 28/2013 ዓ. ም. ለካህናት ባቀረቡት የሕማማት ሳምንት ስብከታቸው፣ “የበጎች እረኛ በጎቹን መሽተት” እዳለበት፣ ይህም ማለት  የቤተክርስቲያን መሪዎች ምዕመናኑ መምሰል፣ ከምዕመናኑ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ ለተቀበሏቸው የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናት ባደረጉት ንግግር፣ በጋራ በሚኖሩበት ቤት የሚያሳዩት አንድነት እና መተባበር ለሌሎች ትልቅ ምስክርነት ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ ራስ ወዳድነት እና ልዩነት ላጠቃው ዓላማችን የአብሮነት ተስፋ የሚታይበት ነው ብለዋል።

ራስን የማግለል እና ሌሎችን የመተቸት ፈተና

በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙት ፈተናዎች ብዙ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ ወገናዊነት፣ ስም ማጥፋት፣ ራስን ከፍ ማድረግ እና አዋቂ ነኝ ብሎ የማሰብ ፈተናዎች እንደሆኑ ገልጸው፣ ከማኅበራዊ ሕይወት ራሳቸውን የሚነጥሉ፣ የአንድነት እና የጋራ ሕይወት የማይኖሩ፣ ካኅናትንም ጨምሮ ማለት ነው፣ ስም በማጥፋት ፈተና ውስጥ እንደሚወድቁ ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔርን ምሕረት መመልከት፣ እርሱን ማሰብ እንደሚገባ አሳስበው፣ እርስ በእርስ በእንግድነት መቀባበል ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ ነው ብለዋል።

ቅዱስ ዮሴፍ የታማኝነትን ምሳሌ ነው

በሮም ከተማ ለሚገኙ የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናት ቅዱስ ዮሴፍን እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ ቅዱስ ዮሴፍ ታማኝ፣ ርህሩህ አባት እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስቀደመ ሰው መሆኑን አስረድተው፣ የቅዱስ ዮሴፍን ምሳሌ በመከተል ራስን በስጦታ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚገባ እና በእርሱ መታመን እንደሚገባ አሳስበዋል። በደከመን ጊዜ የእግዚአብሔር ዕርዳታ እንደሚደርሰን እንገነዘባለን፣ ካኅናት ምንም ያህል ጠንካሮች ቢሆኑ፣ ድክመታቸውን በማወቅ የእግዚአብሔርን ዕርዳታ የማይጠይቁ ከሆነ ወደ ውድቀት ሊሄድ እንደሚችል አስረድተው፣ ካህን ሰው እንደ መሆኑ ለፈተና የተጋለጠ፣ ነገር ግን በቅዱስ ወንጌል ብርሃን በመመራት፣ የእግዚአብሔርን የማዳን ተስፋ ለራሱ እና ለሌሎች ልብ ያስተላልፋል ብለዋል።

“እረኞች በጎቻቸውን ይሸታሉ”

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ሉዊጂ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካህናት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ትምህርታቸውን ጨርሰው ለወንጌል አገልግሎት ወደ መጡበት አካባቢ በሚመለሱበት ጊዜ፣ ከትምህርት ቤት የቀሰሙትን ንድፈ ሃሳብ በተግባር ለመተርጎም ከመነሳት አስቀድመው የሚያገለግሉትን ሕዝብ በሚገባ ማወቅ እና እነርሱን መምሰል ይገባል ብለዋል። “ካህነትን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ነጥሎ መመልከት አይቻልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ክህነት፣ በጥምቀት ጸጋ አማካይነት የእግዚአብሔር ታማኝ እና ቅዱስ ሕዝብ ፍሬ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ብለዋል።

ራስን ከፍ ከማድረግ ህልሞች መራቅ

ካህናት ይህን በመገንዘብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰጣቸው ኃይል በመታገዝ፣ ፍርሃትን በማስወገድ፣ በደስታ እና በምስጋና በመሞላት፣ ራስን ከፍ ለማድረግ ካላቸው ምኞት ወጥተው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት፣ የወንድማማችነት እና የአንድነት መገድን ለመገንባት የሚመኙ መሆን አለባቸው ብለዋል። የክህነት አገልግሎትን በብዙ መንገዶች ማከናወን ይቻላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ካህን በልዩ ልዩ ዕውቀቶች የተሞላ እና በተግባር መፈጸም የሚችል ቢሆንም በጣልቃው ከሁሉ የሚበልጥ አዋቂው እግዚአብሔር እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለው፣ እግዚአብሔር ዳዊትን “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ የሚለውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ለረጅም ጊዜ ያህል በትርጉም ሥራ ሲያግዟቸው ለቆዩት ለክቡር አባ ዣን ለንዱሲስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። 

08 June 2021, 16:13