ፈልግ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ፓትሪያርኮች እምነትን በመጠበቅ የጋራ ጥቅምን እንዲያሳድጉ አሳሰቡ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሰላም ቀን እና “Rerum Novarum” በግርድፉ ሲተረጎም በጊዜው የወዝ አደርችን ሕይወት የሚመለከቱ “አዳዲስ ጉዳዮች” የሚለው የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ሌዮኔ 13ኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 130ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ፓትሪያርኮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በቅድስት ቤተሰብ ሕይወት በመመራት፣ እምነትን ጠብቃ በማቆየት፣ የጋራ ጥቅምን በሚያሳድግ የወንድማማችነት ትንቢታዊ ቃል መኖር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለቅድስት ቤተሰብ ራስን ማቅረብ ማለት የክርስትና ሕይወት ጥሪን በግል ሆነ በጋራ መገንዘብ ማለት እንደሆነ አስረድተው፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቀደምት ነዋሪነት መብት ለማስከበር መጣር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ቀደምት ሐዋርያት አገር ነዋሪዎች መሆናቸውንም በተግባር መመስከርን ይጠይቃል በማለት እሁድ ሰኔ 20/2013 ዓ. ም ለአገራቱ ብጹዓን ፓትሪያርኮች መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቃል ሥጋ የመሆን ምስጢርን ጠብቆ ማቆየት

ኢየሱስ፣ ማርያም እና ዮሴፍ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚገኙ ፓትሪያርኮች ማንነት እና ተልዕኮ በእርግጥ ይወክላሉ ያሉት ቅዱስነታችስው፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸው ቃል ሥጋ የመሆን ምስጢርን ጠብቆ ከማቆየት በተጨማሪ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሆንን ያካትታል ብለዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ኢየሱስን ክስቶስን ወልዳለች ፣ ቅዱስ ዮሴፍም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈፀም ዝግጁ በመሆን ኢየሱስን ተቀብሎታል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም መወለዱ የትህትና እና የፍቅር ምስጢር የተገለጠበት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ዮሴፍ በጋራ ሆነው ኢየሱስን ተንከባክበው ይዘውት ወደ ግብጽ ያደረጉት ጉዞ የትህትና እና የፍቅር መግለጫ መሆኑን ድስረድተዋል። በዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ ለጥሪያቸው ታማኝ ሆነው በመቆየት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እና ሞት እንዲሁም ትንሳኤን በፋሲካ ዕለት ማለዳ ለማየት ጠብቀዋል ብለዋል።

ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት መጸለይ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሆኑት ፣ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም፣ በግብጽ፣ በአረብ ኤምሬቶች እና በኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ በቀጠናው ለሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ፓትሪያርኮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በሐዋርያዊ ሥልጣን መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ለአገራቱ በመጸለይ እና ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው መሆናቸውን አስታውሰዋል። አክለውም በጦርነት ወስጥ የምትገኘውን ሶርያን እና ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ያጋጠማት ሊባኖስን በጸሎት ለማስተወስ የሐይማኖት መሪዎች ሰኔ 24/2013 ዓ. ም በቫቲካን የሚገናኙ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሁሉ ያልፋል፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘለዓለም ይኖራል።

በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ተጀምሮ ካደገ በኋላ የወደቀውን የሰው ልጅ ሥልጣስኔ ያስተወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከእምነታችን አባት ከሆነው አብርሐም ጀምሮ ለመንገዳችን ብርሃን ሆኖ የመራን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ለዘለዓለም የሚኖር መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም አመጽ፣ ጥላቻ እና ልዩነት የአንድን አገር ሕዝብ እንደሚጎዳ ከተገነዘብን በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል። እነዚህን አገራት ችግር እና መከራ ሲደርስባቸው በእግዚአብሔር ኃይል በመተማመን ዕርዳታውን  በጸሎት መለመን እንጂ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች እና ዘላቂነት የሌላቸው የሰላም ስምምነቶች የሚጠቅሙ አይደሉም ብለዋል። በተመረዙ የጥላቻ ምንጮች ጥማትን ለማርካት ከመሞከር ይልቅ የኮፕት፣ የማሮናይት ፣ የሜልቃይት ፣ የሶርያ፣ የአርሜኒያ ፣ የከለዳውያን እና የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች ባወረሱት የእምነት ባሕል በመመራት ልብን ለመንፈስ ቅዱስ ማስገዛት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የአገራችሁን የጋራ ጥቅም የምታረጋግጡ ናችሁ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ፓትሪያርኮች ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ እንደተነገሩት፣ እንደ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሠረት ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሰብዓዊ ወንድማማችነት ትንቢታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ለአካባቢው ሕዝብ የምድር ጨው መሆን እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

28 June 2021, 15:58