ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ቁርባን የሚያስፈልገው በመንገድ ላይ የደከሙና የተራቡትን ለመመገብ ነው አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በግንቦት 29/2013 ዓ.ም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋ እና ክቡር ደም የሚታወስበት የቅዱስ ቁርባን አመታዊ በዓል ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእርሳቸው መሪነት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ስረዓት የተከናወነ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ቅዱስ ቁርባን የሚያስፈልገው በሕይወት መንገድ ላይ የደከሙና የተራቡትን ለመመገብ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ኢየሱስ የፋሲካን እራት የሚያከብሩበትን ስፍራ እንዲያዘጋጁ ደቀ መዛሙርቱን ላከ። እነሱ ራሳቸው “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ዝግጅት እንድናደርግ ትፈልጋለህ?” (ማርቆስ 14፡12)  ብለው ጠይቀውታል። በቅዱስ ቁርባን እንጀራ ውስጥ የጌታን መገኘት እያሰብን እና እርሱን ስናመልክ እኛም የት ፣ በምን “ቦታ” ውስጥ የጌታን ፋሲካ ማዘጋጀት እንደምንፈልግ መጠየቅ አለብን። እግዚአብሔር የእኛ እንግዳ ሆኖ መጥቶ ልያርፍባቸው የሚፈልግባቸው በሕይወታችን ውስጥ ያሉ “ስፍራዎች” ምንድናቸው? አሁን ከሰማነው ቅዱስ ወንጌል ሶስት ምስሎችን በማንፀባረቅ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እፈልጋለሁ (ማርቆስ 14፡12-16 ፣ 22-26)።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከእዚህ በታች ያለውን የማጫወቻ ቁልፍ ይጫኑ!

የመጀመሪያው አንድ የውሃ ማሰሮ የተሸከመ ሰው ነው (ማርቆስ 14፡13)። ይህ አንደ አላስፈላጊ ዝርዝር ሊመስል ይችላል። ሆኖም ያ ስም-አልባው ሰው ደቀመዛሙርቱን በኋላ የላይኛው ክፍል ወደ ተባለ ስፍራ የሚያመጣ መሪ ሆነ። የውሃ ማሰሮው እርሱን ለይተው የሚያሳይ ምልክት ነው። ጥማታችንን ለማርካት እና ታድሶን ለማምጣት ሁል ጊዜ የውሃ ምንጭ የምንፈልግ ስለተጠማው ስለ ሰብአዊ ቤተሰባችን እንድናስብ የሚያደርግ ምልክት ነው። ሁላችንም በህይወት ውስጥ በእጃችን የውሃ ማሰሮ ይዘን እንጓዛለን: - ፍቅርን ፣ ደስታን ፣ የበለጠ ሰብአዊ በሆነ ዓለም ውስጥ የተሟላ ሕይወት ለማግኘት እንጠማለን። ይህንን ጥማት ለማርካት የዓለማዊ ነገሮች ውሃ አይጠቅምም። የኛ የጠለቀ ጥማት ፣ እግዚአብሔር ብቻ የሚያረካው ጥማት ነውና።

እስቲ ይህንን ምስል እና ምንን እንደሚያመለክት በአጭሩ እንመርምር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የፋሲካ እራት የውሃ ማሰሮ የተሸከመ ሰው በሚያሳየቻው ቦታ እንዲያዘጋጁ ይልካቸዋል። የቅዱስ ቁርባንን በዓል ለማክበር በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጥማት ማወቅ ፣ ለእርሱ ያለንን ፍላጎት ማስተዋል ፣ መገኘቱን እና ፍቅሩን መመኘት ፣ ብቻችንን መሄድ እንደማንችል መገንዘብ ያስፈልገናል ፣ ነገር ግን የዘላለም ሕይወት ምግብ እና መጠጥ በጉዞዋችን ውስጥ ያስፈልገናል። በአሁኑ ጊዜ የሚታየው አሳዛኝ ሁኔታ ይህ ጥማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እና እየደበዘዘ መሄዱን ነው። ስለ እግዚአብሔር የሚነሱ ጥያቄዎች በሁኑ ወቅት እየቀረቡ አይደሉም፣ ለእግዚአብሔር ያለን ፍላጎት እየቀነሰ መጥቷል፣ እግዚአብሔርን የሚሹ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥር እየቀነሱ መጥተዋል። እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲህ እኛን አይስበንም፣ ምክንያቱም እኛ ለእርሱ ያለንን ጥልቅ ጥማት እውቅና ስላልሰጠነው። ሆኖም እንደ ሳምራዊቷ ሴት የውሃ ማሰሮ ዕቃ ያለው ወንድ ወይም ሴት ባለበት ቦታ ሁሉ (ዮሐ. 4፡5-30) - እዚያ ጌታ አዲስ ሕይወትን እንደሚሰጥ፣ ሕልማችንን እና ምኞታችንን እውን እንድናደርግ ራሱን መግለጥ ይችላል፣ የተረጋገጠ ተስፋ ፣ ለምድራዊ ጉዞአችን ትርጉም እና መመሪያ ለመስጠት አፍቃሪ ሆነን መኖር እንችል ዘንድ ይረዳናል። የውሃ ማሰሮ የተሸከመው ሰው ደቀመዛሙርቱን ኢየሱስ ቅዱስ ቁርባንን ወደ ሚመሰርትበት ክፍል ይዞዋቸው አመራ። የእግዚአብሔር ጥማታችን ወደ መሠዊያው ያመጣናል። ያ ጥማት በማይኖርበት ቦታ ሁሉ፣ ክብረ በዓሎቻችን ደረቅ እና ሕይወት አልባ ይሆናሉ። እንደ ቤተክርስቲያን የተለመደው ትንሽ ቡድን የቅዱስ ቁርባንን በዓል ለማክበር መገናኘቱ በቂ አይደለም፣ ወደ ከተማ መውጣት ፣ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት እና የእግዚአብሔርን ጥማት እና የወንጌልን ፍላጎት እንዴት እንደሚገነዘቡ እና እንደሚያድሱ መማር ያስፈልገናል።

ሁለተኛው የወንጌል ምስል የላይኛው ክፍል ነው (ማርቆስ 14፡ 15)። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ይህ ክፍል እንግዳ ተቀባይ በሆነ ሰው ቤት ውስጥ ነበር የተከናወነው። አባት ፕሪሞ ማዝዞላሪ ​​ስለዚያ ሰው ሲናገር “አንድ ስም አልባ የሆነ ሰው ይኸውላችሁ፣ የቤቱ ባለቤት የነበረ ሰው ለኢየሱስን በጣም ጥሩ የሚባለውን ክፍል ይሰጠዋል፣ እርሱ ለኢየሱስ ያለውን የተሻለ ክፍል ይሰጣል፣ በታላቁ ቅዱስ ቁርባን ዙሪያ ያለው ነገር ሁሉ ታላቅ መሆን አለበት ለእዚህም ነው ለኢየሱስ ያለውን የተሻለውን ክፍል የሰጠው። ታላቅ ልብ ፣ ታላላቅ ቃላት እና ታላላቅ ድርጊቶች ” በማለት ስለእዚያ ስም አልባ ሰው ተናግረው ነበር።

ለትንሽ እንጀራ አንድ ትልቅ ክፍል። እግዚአብሔር ራሱን እንደቁራሽ እንጀራ ትንሽ ያደርጋል። ለዚያ ነው በትክክል እሱን ለማወቅ ፣ ለማምለክ እና ለመቀበል እንድንችል ታላቅ ልብ የምያስፈልገን። የእግዚአብሔር መገኘት በጣም ትሁት ፣ የተደበቀ እና ብዙውን ጊዜ የማይታይ ስለሆነ ፣ የእርሱን መኖር ለመለየት ፣ ዝግጁ ፣ ንቁ እና ተቀባይ የሆነ ልብ ያስፈልገናል። ልባችን እንደ አንድ ትልቅ ክፍል ከመሆን ይልቅ ከባለፈው ጊዜ ያሸጋገርናቸው ነገሮችን በድብቅ አስቀምጠን የምንጠብቅበት ቁም ሣጥን ፣ ወይም ደግሞ ከረጅም ጊዜ በፊት ሕልማችንን እና ጉጉታችንን ያከማቸንበት ሰገነት ከሆነ፣ ወይም በእኛ ችግሮች እና ተስፋ መቁረጦች የተሞላ ከሆነ፣ ያኔ የእግዚአብሔርን ዝምታ እና በስውር በእኛ ውስጥ መገኘቱን  መገንዘብ የማይቻል ይሆናል። አንድ ትልቅ ክፍል ያስፈልገናል። ልባችንን ማስፋት አለብን።ከራሳችን ትንሽ ከተዘጋው ቦታ ወጥተን ወደ ትልቁ ክፍል ማለትም ወደ አስደናቂው እና ወደ ማምለኪያው ሰፊ ስፍራ መግባት አለብን። ስግደት-በቅዱስ ቁርባን ፊት ለፊት እኛ ሊኖረን የሚገባው ባህሪይ ነው። ቤተክርስቲያንም ትልቅ ክፍል መሆን አለባት እንጂ ትንሽ እና የተዘጋ ክበብ መሆን የለባትም፣ ነገር ግን ሁሉንም ለመቀበል ክፍት የሆነች፣ ሁሉንም የማሕበረሰብ ክፍል የምትቀበል መሆን ይኖርባታል። እስቲ ይህንን ጥያቄ እራሳችንን እንጠይቅ-አንድ የተጎዳ፣ ስህተት የሠራ ፣ በሕይወት ውስጥ የተሳሳተ ሰው ሲቀርብ፣ ቤተክርስቲያኗ ይህንን ሰው ለመቀበል እና ሐዘኑን ወደ ደስታ ለመቀየር የሚያስችል እና የሚረዳ ከክርስቶስ ጋር መገናኘት ይችል ዘንድ የሚጋብዝ ሰፊ ክፍል አላት ወይ? ቅዱስ ቁርባን የሚያስፈልገው በመንገድ ላይ የደከሙና የተራቡትን ለመመገብ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ንጹህ እና ፍጹም የሆነ ቤተክርስቲያን ለማንም ቦታ የሌለው ክፍል ነው። በሌላ በኩል በክርስቶስ ዙሪያ የሚሰበሰብ እና የሚያከብሩ በሮቿ የተከፈቱ ቤተክርስቲያን ሁሉም ሰው የሚገባበት ትልቅ ክፍል ናት።

ከቅዱስ ወንጌሉ የመጨረሻው ምስል የኢየሱስን እንጀራ ሲቆርስ የሚያሳይ ነው። ይህ የቅዱስ ቁርባን ምልክት የእጅ ሥራ የላቀ ውጤት ነው። ወደ አዲስ ሕይወት እንደገና ለመወለድ እንድንችል የእምነታችን ልዩ ምልክት እና እራሱን የሚያቀርበውን ጌታ የምናገኝበት ቦታ ነው። ይህ የእጅ ምልክትም እኛን ይፈታተናል። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ጠቦቶች ተሰውተው ለአምላክ ቀርበዋል። አሁን ኢየሱስ ለእኛ ሕይወት ሊሰጠን ፈልጎ ራሱን እየሰዋ በግ ነው። በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የፍቅር አምላክን እናሰላስላለን እና እናመልካለን። ጌታ ማንንም የማይቆርስ፣ ነገር ግን ራሱ እንዲቆረስ የሚፈቅድ ነው። ጌታ ምንም ዓይነት መስዋዕት እንድናቀርብለት የሚተይቀን ሳይሆን ነገር ግን ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀርብልናል። የቅዱስ ቁርባንን በዓል በማክበር እና በመለማመድ እኛም በዚህ ፍቅር እንድንካፈል ተጠርተናል። ልባችንን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የተዘጋ ከሆነ እሁድ ዕለት እንጀራ መቁረስ አንችልም። ለተራቡ ሰዎች እንጀራ ካልሰጠን ያን እንጀራ መብላት አንችልም። የተቸገሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስቃይ እስካልተጋራን ድረስ ያንን እንጀራ መጋራት አንችልም። በመጨረሻም የቅዱስ ቁርባን በዓል አከባበር ዋናው ነጥብ ፍቅር ብቻ ሆኖ ይቀራል። አሁን እንኳን እያከበርነው የሚገኘው የቅዱስ ቁርባን ክብረ በዓል እራሳችንን እንድንለወጥ እና ለሌሎች እንደ እንጀራ ሆነን እንድንቆረስ እስከምንፈቅድ ድረስ ዓለምን እየለወጠ ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ዛሬ “የጌታን እራት ለማዘጋጀት” ወዴት መሄድ አለብን? ከቅዱስ ቁርባን ምስጢር ጋር የሚደረግ ውህደት የክርስቶስ አካል በዓል መገለጫ ለጊዜው ብቻ ልናከናውነው የምንችለው ውህደት ሳይሆን ወደ ውጭ ወጥተን ኢየሱስን ለሌሎች ለማድረስ የተጠራን መሆናችንን ያስታውሰናል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለምናገኛቸው ሰዎች ክርስቶስን በማምጣት በቅንዓት ለመውጣት እና ለመግባት ያስችለናል። በእጃችን ላይ የውሃ ማሰሮ ይዘን የምንጓዝ ጥማትን የምትቆርጥ እና ውሃ የምታጠጣ ቤተክርስቲያን እንሁን፣ ሁሉም ወደ ጌታ የሚገቡበት እና የሚገናኙበት ትልቅ እና አቀባበል ማድረግ የምችል ክፍል መሆን እንድንችል ልባችንን በፍቅር ሰፋ እናድርግ። በእኛ በኩል ዓለም የእግዚአብሔርን ፍቅር ታላቅነት እንድያይ የሕይወት እንጀራችን በርኅራኄ እና በመተባበር እንቁረስ። ያኔ ጌታ ይመጣል ፣ እንደገና አንድ ጊዜ ያስደንቀናል ፣ እንደገና ለዓለም የሕይወት ምግብ ይሆናል። እናም በሰማያዊው ግብዣ ላይ ፣ ፊቱን በማሰላሰል እና ማለቂያ የሌለውን ደስታ ለማወቅ እስከምንችልበት ቀን ድረስ እርሱ ሁል ጊዜ እኛን ያረካናል።

06 June 2021, 10:42