ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ትዳር የብቸኝነት ሕይወት ሳይሆን በኢየሱስ የሚደገፍ እና የሚመራ መሆኑን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ ለሰኔ ወር እንዲሆን በቪዲዮ በኩል ባስተላለፉት ሃሳባቸው ለጋብቻ በመዘጋጀት ላይ ለሚገኙት ወጣቶች መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል። ፍቅር እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ለመገናኘት ያቀደው እና የተመኘው መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ትዳር አንዳንድ ጊዜ ችግር ያለበት ረጅም የሕይወት ጉዞ ቢሆንም፣ የትዳት ሕይወትን ለሚኖሩት አስደሳች እና መልካም መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። አክለውም ትዳር የብቸኝነት ሕይወት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚደገፍ እና የሚመራ መሆኑን ለሰኔ ወር እንዲሆን በማለት በላኩት የጸሎት ሃሳብ ገልጸዋል። ቅዱስነትቻው የጋብቻን ውበት በማስረዳት የላኩትን መልዕክት ይፋ ያደረገው በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት መሆኑ ታውቋል።

የጋብቻ ሕይወት ጥሪ ነው
ማኅበራዊ ሕይወት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በሚገኝበት ባሁኑ ዘመን ወጣቶች ስለ ጋብቻ ማሰብ ከባድ መስሎ ቢታይም፣ ችግሮች መቸም ቢሆን የማይጠፉ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባ፣ በዓለማችን ውስጥ የተዛመተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝም በጋብቻ መካከል ከሚያጋጥሙ ችግሮች አንዱ መሆኑ ተስተውሏል። ጋብቻ የማኅበራዊ ሕይወት መሠረት ብቻ ሳይሆን ከልብ ውስጥ የሚፈልቅ፣ ተገንዝበን፣ አምነን እና ፈቅደን የምናደርገው የሕይወት ውሳኔ እንዲሁም ከጥሪዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ቅድመ ዝግጅትን የሚጠይቅ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

እግዚአብሔር ፍቅርን ካዘጋጀልን በኋላ የእኛ ድርሻ መታከል እንዳለበት እንደሚፈልግ ቅዱስነታቸው ገልጸው በመሆኑም ፍቅርን ሌሎች ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል። ለጋብቻ ሕይወት በዝግጅት ላይ ያሉትን ወጣቶች በጸሎት ልንደግፋቸው እንደሚገባ አሳስበው ክርስቲያናዊ ሕይወታቸው በፍቅር፣ በቸርነት፣ በታማኝነት እና በትዕግስት የተገነባ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የቤተሰብ ልዩ ዓመት
ለሰኔ ወር እንዲሆን የቀረበው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጸሎት ሃሳብ፣ ከመጋቢት ወር 2013 ዓ. ም. ጀምሮ በመታሰብ ላይ በሚገኝ የቤተሰብ ዓመት ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጸሎት ሃሳብ “ቤተሰባዊ ፍቅር በጥሪ የታገዘ የቅድስና ጉዞ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን የቤተሰብ ዓመት ያማከለ ሲሆን “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” የሚለው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት እንዲሁም “ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትም አድርጉ” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያን እና በታኅሳስ ወር 2014 ዓ. ም የሚገባደደውን የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተላከ መልዕክት መሆኑ ታውቋል።

የጋብቻ ቁጥር ቀንሶ ፍቺ መበራከት
ከር. ሊ. ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት ጋር ይፋ የሆነው ጽሑፍ፣ በዘመናች ውስጥ የጋብቻ ሕይወት የደረሰበትን ደረጃ የገለጸ ሲሆን፣ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እ. አ. አ ከ1972 ዓ. ም ወዲህ የጋብቻ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን፣ በተለይም በአሜሪካ ውስጥ የጋብቻ ቁጥር እጅግ ዝቅ ማለቱን አስታውቆ በተጨማሪም ለጋብቻ የሚዘጋጁበት ዕድሜ ከፍ ማለቱን ገልጿል። በሁሉም አገሮች ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር መጨመሩን ጥናቱ አመልክቶ ፍቺን የሚጠይቁት ሰዎች ቁጥር መጨመሩን አመልክቷል።

የጋብቻ ሕይወት በቂ ዝግጅት እና እገዛ ያስፈልገዋል
ጓደኛሞች ለሠርግ በዓላቸው ብቻ መዘጋጀት ሳይሆን፣ የጋብቻ ሕይወት ጥሪ መሆኑን ማስረዳት አስፈላጊ መሆኑን በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ አስረድተዋል። ወ/ሮ ገብርኤላ አክለውም ወጣቶችን ለጋብቻ ሕይወት ማዘጋጀት ከምስጢረ ጥምቀት መጀመር እንዳለበት ገልጸው፣ ወጣቶችን ለጋብቻ ሕይወት ማብቃት ቤተሰባዊ ሃላፊነት ጥሪ መሆኑንም አስረድተዋል። ለጋብቻ ሕይወት ብዙም ዋጋ በማይሰጥበት ዘመን፣ የምስጢሩን ታላቅነት እና ከጥሪዎች መካከል አንዱ መሆኑን ማስገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን፣ መንፈሳዊ እሴቱ ከፍተኛ መሆኑን፣ የቅድስና መንገድ መሆኑን፣ በጋብቻ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስን ይዞ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን ለውጣቶች ማስረዳት እንደሚያስፈልግ፣ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ አስረድተዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ ወጣቶችን ለጋብቻ ሕይወት ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የጋብቻ ሕይወት ከእግዚአብሔር የሚመጣ ጥሪ በመሆኑን ወጣቶች ለጥሪው ምላሽ መስጠት እንዲችሉ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ዕገዛ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ጋብቻን ለመፈጸም እና ቤተሰብን ለመመስረት የሚደረግ ውሳኔ የጥልቅ አስተንትኖ ውጤት መሆኑን ክቡር አባ ፍሬደሪክ ገልጸው፣ የጋብቻ ሕይወት መሪ እና አጋዥ፣ የፍቅር አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስረድተዋል።
 

02 June 2021, 14:58