ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኬልቄዶኒያው ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ አማኑኤል የተመራ ልኡካን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኬልቄዶኒያው ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ አማኑኤል የተመራ ልኡካን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል።  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ "ለኅብረታችን እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን በጋራ እናስወግድ"።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኬልቄዶኒያው ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ አማኑኤል የተመራ ልኡካን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። ልኡካኑ ወደ ሮም የመጡት ዓመታዊውን የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ክብረ በዓልን በጋራ ለማክበር መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለልኡካኑ ባደረጉት ንግግር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጥፋት እና መከራ ያስከተለ ቢሆንም በታመመ ዓለም ውስጥ ጤናማ ሆኖ ለመኖር ትምህርት ያገኘንበት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለልኡካኑ ባደረጉት ንግግር የቆዩ ችግሮቻችንን ለመፍታት ጊዜው አሁን ባይሆንም መንፈስ ቅዱስ አግዞን በአንድነት እንዳንጓዝ እንቅፋት የሚሆኑንን የቆዩ ችግሮቻችንን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል። ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመጣብን መከራ እንደ መቅሰፍት ብንመለከተውም አንድነታችንን ለማሳደግ የጀመርናቸውን ጥረቶች አጠናክረን የምንቀጥልበት፣ እንዲሁም ወደ ፊት ማድረግ የሌለብንን ነገር ላለማድረግ መወሰን የምንችልበት አጋጣሚ ነው ብለው፣ ከኦርቶዶክስ ወንድሞቻችን ጋር ወደ ሙሉ አንድነትን ለመድረስ የጀመርነውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።  እ. አ. አ በየዓመቱ ሰኔ 29 በሮም የሚከበረውን የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ክብረ በዓልን በጋራ ማክበር እንደዚሁም እ. አ. አ በየዓመቱ ኅዳር 30 በኢስታምቡል የሚከበረውን የቅዱስ እንድሪያስ ዓመታዊ ክብረ በዓልን በአንድነት ማክበር ለጥረታችን እገዛን ያደርጋል ብለዋል።   ሁለት አማራጮች መኖራቸውን ለቆንስጣንጥንያው ልኡካን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የራስ ደህንነት እና ዕድል ብቻ በመፈልግ ራስን ለሌሎች ክፍት ሳያደርጉ መቅረት፣ ካልሆነ ደግሞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶን ለመቋቋም በመዘጋጀት እና ራስን ለሌሎች ክፍት በማድረግ፣ እግዚአብሔር በሚሰጠን የጸጋ ፍሬዎች በመታገዝ አንድነትን ለማምጣት ጥረት ማድረግ ነው ብለዋል።

 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ የሙከራ ጊዜ ነው

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመጣብንን የሙከራ ጊዜ ሳንጠቀምበት ማሳለፉ ተገቢ አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ያለፈው አንድ ዓመት ተኩል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት የተደረገብት መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ ጊዜ ዓለማችን በሕመም ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ማንም ሰው ራሱን ለይቶ በጤና ለመኖር የማይችል መሆኑን በመረዳት ለሌላው ትሑት እና ቸር ለመሆን የሚያስችል ትምህርት የቀሰምንበት ዓመት መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ወደ ቀድሞ ጤናማ ጊዜ ለመመለስ ያለው ምኞት ትልቅ መሆኑን አስታውሰው፣ ዛሬም ቢሆን በውሸት የደህንነት ተስፋ በመመራት፣ ትርፍን ብቻ ለመሰብሰብ ባለው የግል ጥቅም ፍለጋ ላይ በመሆን በዓለማችን የሚታየውን ኢፍትሃዊነት፣ የድሆችን ጩሄት እና የጋራ መኖሪያ ምድራችን ስቃይ ወደ ጎን ሲደረግ ይታያል ብለዋል።    

በሚቀረውና በሚያልፈው ነገር ላይ ማስተንተን ያስፈልጋል

ዛሬ ላይ ክርስቲያኖች ራሳቸውን በሚገባ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄ አለ ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከዚህ በፊት ምንም እንዳልሆነ በመቁጠር እንዳላየ እና እንዳልሰማ መኖር ወይስ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶን ለመቋቋም መዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል። ያጋጠሙን እንቅፋቶች ፍርድን እንድንሰጥባቸው ያስገድዱናል ያሉት ቅዱስነታቸው አንድ ገበሬ እህሉን ከገለባው ለይቶ እንደሚያወጣ ሁሉ ፍርዳችንም በመልካም እና በመጥፎ ነገር መካከል ያለውን ልዩነት መለየትን ያመለክታል ብለው፣ ያጋጠመን ቀውስ በሚቀረውና በሚያልፈው ነገር ላይ ማስተንተን እንዳለብን ያስገድደናል ብለዋል።

ክርስቲያኖች በመካከላቸው ሙሉ አንድነትን ለማምጣት በሚተጉበት ጊዜ ከሥር መሰረቱ በመጀመር ምን ማድረግ እንዳለብን፣ እንዴት ወደ ፊት መጓዝ እንዳለብን ማሰብ እና ማስተንተን ያስፈልጋል ብለዋል። አስተንትኖአችንም ለጋራ ጉዞ እንቅፋት በመሆን የቆዩ ችግሮቻችንን ይዘን መጓዝ ወይስ ልዩነትን ለማስወገድ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል በሚለው ላይ መሆን አለበት ብለዋል። ቅዱስነታቸው ምክራቸውን ሲለግሱ እንደተናገሩት በቤተክርስቲያኖቻችን መካከል በተሠሩ አዲስ የአንድነት ጎዳና ላይ ለመጓዝ የምንመኘውን ምኞታችንን እውን በማድረግ አንዱ በሌላው ጉዳይ የጋራ ሃላፊነትን መውሰድ ይኖርብናል ብለዋል።

ልዩነቶችን በውይይት እና በበጎ ሥራ ማሸንፍ

በካቶሊክ እና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚታየውን ልዩነት ማቃለል የሚቻለው በጋራ ውይይት ነው ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጋራ ውይይታችን በቸርነት እና በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ብለው፣ ለፍቅር የምንገዛ ከሆንን ፍቅርን የሚሰጠን እግዚአብሔር በልዩነት ላይ መግባባትን የሚያመጣ መንፈስ ቅዱስን በመላክ ለወንድማማችነት ሕይወት መንገድን ይከፍትልናል ብለዋል።  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ኅዳር 30/2020 ዓ. ም በተከበረው የቅዱስ እንድሪያስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ አንደኛ ጋር በአንድ መነበረ ታቦት በጋራ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ ይህም ሁለቱን አብያት ክርስቲያናትን ወደ ሙሉ አንድነት ከሚመሩ መንገዶች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

የኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር በመወያየት ላይ ናቸው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኬልቄዶኒያው ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ አማኑኤል ለተመራው ልኡካን ባደረጉት ንግግር ለሙሉ አንድነት የሚደረገው የጋራ ውይይት ከሌሎች አብያት ክርስቲያናት ጋርም ይኖራል ብለው ይህም ብዙ ምዕመናን በመካከላቸው የበለጠ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ለማሳደግ ያላቸውን ምኞት ለማሳካት የሚደርዳ መሆኑን ገልጸው፣ ያለፉ ስህተቶችን ወደ ጎን በማለት እርቅን እና ሰላምን ለማምጣት የሚያግዝ ብቸኛው መንገድ የጋራ ውይይት ነው ብለዋል። አክለውም የካቶሊክ እና ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ትብብርን በመፍጠር የጋራ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለፓትርያርክ በርተሎሜዎስ የተለከ ሰላምታ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቆንስጣንጥንያውን ልኡካን ጋር በቫቲካን ውስጥ ያደረጉትን ቆይታ ከማጠቃለላቸው በፊት የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓልን ለማክበር ወደ ሮም ለመምጣት ላልቻሉት ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርተሎሜዎስ አንደኛ ወንድማዊ ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል። በዚህ የሰላምታ መልዕክታቸው እንደ እውነተኛ ወንድም እንድሚመለከቷቸው ገልጸው፣ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርተለሜዎስ አንደኛ ጋር ያላቸው ወንድማዊ ግንኙነት ዘወትር ጥልቅ ነው ብለዋል። የቆንስጣንጥንያው ልኡካን ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ከፈጸሙ በኋላ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ከብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ጋርም ተገናኝተዋል።

29 June 2021, 16:43