ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወላጅ ቤተሰብን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወላጅ ቤተሰብን ሲቀበሉ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሕጻናት የነገ ቤተሰብ ተስፋዎች መሆናቸውን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስችስ ሰኔ 6/2013 በሕጻናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛን የሚቃወም ዓለም አቀፍ ቀንን ምክንያት በማድረግ መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት የትምህርት እና የጤና ዕድል ተነፍገው በጉልበት ሥራ እንዲሰማሩ መደረጋቸው ታውቋል። ይህም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ ችግሩን የከፋ ማድረጉን የእመቤታችን ቅድስት ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት ማህበር አባል፣ እህት ሩሚታ ቦርጃ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሕጻናት የወደ ፊት ሰብዓዊ ቤተሰብ እድገት ተስፋዎች መሆናቸውን ዘንድሮ በተከበረ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ጸረ ጉልበት ብዝበዛ ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት በሚል ዓላማ ዕለቱ በየዓመቱ እንዲከበር መደንገጉ ታውቋል። እ. አ. አ. በ2021 ዓ. ም. የቀረበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳመለከተው በዓለማችን 160 ሚሊዮን ሕጻናት የልጅነት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከአቅማቸ በላይ የሆኑ ከባድ ሥራዎችን እየሰሩ ለማሳለፍ የሚገደዱ መሆናቸውን አስታውቋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዕለቱን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በርካታ ሰዎች ሕጻናት የልጅነት ጊዜያቸውን በጨዋታ እንዳያሳልፉ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ይህም ሕጻናት ስለ ወደፊት ሕይወታቸው እንዳያሳቡ እና በራስ የመተማመን አቅም እንዳይኖራቸው ያደርጋል ብለዋል። የሕጻናት የወደ ፊት ሕይወት ተስፋ መጨለም የልበትም ብለው፣ ቅዱስነታቸው ዘንድሮ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በሕጻናት ማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ተቋማት ሕጻናትን ከሚደርስባቸው የጉልበት ብዝበዛ እና ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች የሚወጡበትን መንገድ እንዲያመቻቹ በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።       

ለሕጻናት የሚደረግ ማኅበራዊ እንክብካቤ

ሕጻናት የነገ ተስፋዎች ብቻ ሳይሆኑ የዛሬም ጭምር መሆናቸውን እና የማኅበራዊ ሕይወት ስኬት የሚለካው ለሕጻናት በሚያበረክተው አገልግሎት መሆኑን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት ማህበር አባል፣ እህት ሩሚታ ቦርጃ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል። በማኅበራቸው በኩል ለወጣቶች የሚቀርብ ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት እህት ሩሚታ ቦርጃ፣ ለሰዎች የሚቀርብ ማኅበራዊ አገልግሎት ስልጠናን እና የአዕምሮ ለውጥን ያማከለ መሆን እንዳለበት ገልጸው ይህ ካልሆነ በተለይ ሕጻናት ለጉልበት ብዝበዛ እንደሚዳረጉ እና ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት የሚገደዱ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም የሕጻናትን የትምህርት መብት የሚከለክል፣ የሕጻንነት ዕድሜአቸውን በጨዋታ እና በደስታ እንዳሳልፉ የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጸዋል። የአንድ ሰው እድገት ሁሉንም አቅጣጫ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ያስረዱት እህት ሩሚታ ቦርጃ፣ ሕጻናት ለጉልበት ብዝበዛ በሚዳረጉበት ጊዜ በሕጻንነት ዕድሜአቸው ማግኘት ያለባቸውን መብቶች የሚያጡ መሆኑን ገልጸው፣ የሕጻናት የማምረት አቅም የሚለካው በገንዘብ ብቻ እንጂ ሌላውን የዕድገት አቅጣጫን  ያገናዘበ አለመሆኑን አስረድተዋል።      

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት

በዓለማችን ውስጥ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሕጻናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛ በሃያ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያድግ ማድረጉ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባለፈው መስከረም ወር ለተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 75ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሕጻናት ላይ ያስከተለው ቀውስ መዘንጋት የለበትም ብለው፣ ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ መፈላቀላቸውን አስታውሰው፣ ይህም በሕጻናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛ፣ ጾታዊ ጥቃት እንዲጨምር እና የተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ለቤተሰብ የሚደረግ ድጋፍን በተመለከተ

ለሕጻናት የሚደረገውን አገልግሎት አስመልክተው አስተያየታቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የገለጹት እህት ሩሚታ ቦርጃ፣  በበርካታ የዓለማች ክፍሎች ሕጻናት የቤተሰብን ፍቅር እና እገዛን የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ የአገልግሎታቸው ዓላማ ቤተሰብ የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችን ተቋቁመው ለሕጻናት የሚያደርጉትን ድጋፍ ማሳደግ እንዲችሉ ማስቻል መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ቤተሰብ ለሕጻናት የሚያደርገውን ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዲችሉ፣ ችግራቸውን በመረዳት እና ጥያቄአቸውን መመለስ እንደሚያስፈልግ፣ የሕጻናትን የመማር መብት በማክበር በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበትን አጋጣሚዎች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ችግር

የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጥናት ማዕከል ባወጣው ሪፖርት መሠረት ዕድሜአቸው ከ 5-17 የሆናቸው ሕጻናት ከአቅማቸው በላይ በሆኑ የሥራ መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቅሶ፣ ባሁኑ ጊዜ ከ86 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት፣ ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውቋል። በእስያ አህጉር ውስጥ በሚገኙ ደቡብ ምሥራቅ አገራትም ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከአቅማቸው በላይ በሆኑ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ መሆኑን አስታውቆ፣ ይህ ችግር የሚታየው በማደግ ላይ ባሉ ድሃ አገሮች ብቻ ሳይሆን ባደጉ የአውሮፓ አገሮች እና አሜሪካ ውስጥም የሚታይ መሆኑን የጥናት ማዕከሉ ገልጾ፣ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ በቁጥር ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት ከአቅማቸው በላይ በሆኑ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ መሆኑን አስታውቋል።

14 June 2021, 14:31