ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የእግዚአብሔርን ዕርዳታ ዘወትር በእምነት መለመን ያስፈልጋል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ሰኔ 13/2013 ዓ. ም በላቲን ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ከማር. 4፡ 35-41 ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ የማድረግ ኃይልን በሚገልጽ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀረቡት ስብከታቸው፣ ማዕበልን እና ነፋስን በዕለታዊ ኑሯችን ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች ጋር በማነፃፀር፣ በማይደክም የእምነት ጸጋ በመታገዝ ሳንሰለች የኢየሱስ ክርቶስን ዕርዳታ እንድንጠይቅ አሳስበው፣ ኢየሱስ ሊረዳን ከጎናችን ቆሞ የሚጠብቀን መሆኑን አረጋግጠውልናል። ክቡርና እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ሰኔ 13/2013 ዓ. ም ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታችን መካከል ከማር. 4፡35-41 ተወስዶ የተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል  አድምጠናል። በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዕበሉን በኃይሉ ጸጥ ማድረጉን ሰምተናል። ደቀ መዛሙርቱ ተሳፍረው ሲጓዙበት የነበረው ጀልባ በብርቱ አውሎ ነፋስ ስለተመታ በሐይቁ ውስጥ የሚሰጥሙ መስሏቸው እጅግ ፈርተው ነበር። በዚህን ጊዜ ኢየሱስ በጀልባው በኋለኛው ክፍል ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ፍርሃት ስለያዛቸው ወደ እርሱ ቀርበው “መምህር ሆይ! ስንጠፋ ዝም ትላልህን?” አሉት።

ብዙን ጊዜ እኛም ብንሆን በሕይወታችን ፈተና እና ችግር ሲያጋጥመን፣ ተስፋ አድርገን በምኞት የጀመርነው እቅዳችን ሲሰናከልብን፣ በጭንቀት ውስጥ ስንገኝ፣ በሕይወታችን ውስጥ ውድቀት ሲያጋጥመን፣ ሥራ በማጣት ይሁን ወይም በሌሎች የተለያዩ ችግሮች ወደ ፊት መጓዝ ሲያቅተን ወይም ቤተሰቦቻችን ሆነ እኛ በማንድን በሽታ ተይዘን በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ስንገኝ፣ ወይም በሌሎች ችግሮች ውስጥ ሆነን፣ ኢየሱስ ሆይ! በችግር ውስጥ ስገኝ ለምን አትደርስልኝም በማለት ወደ ኢየሱስ ጮሄናል።

ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት እንደተጨነቁ ሁሉ እኛም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነን በፍርሃት የተጨነቅንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ በጀልባው በኋለኛው ክፍል ተኝቶ የነበረ ቢሆንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ ነበር። የሚሆነውን ነገር ሁሉ ይጋራቸው ነበር። ብርቱ አውሎ ነፋስ ተነስቶ ጀልባዋን ሲመታት፣ ደቀ መዛሙርቱም ደንግጠው ሲጮሁ፣ በሌላ ወገን ኢየሱስ ተረጋግቶ መተኛቱን ስንመለከት  ይገርመን ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜ እና በሁሉ ስፍራ ከእኛ ጋር አለ። የእኛን ጩሄት፣ የእኛን ጥያቄ ይጠብቃል። በችግሮቻችን ውስጥ እርሱን እንድናሳትፍ እና እንድናስገባ ይፈልጋል።

የእርሱ ማቀላፋት ይበልጥ እንድንነቃ ያደርገናል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሰው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። እግዚአብሔርን ማመን ብቻውን በቂ አይደለም። እርሱ አለ ብሎ መቀመጥ በቂ እንዳልሆነ እንረዳለን። ከእርሱ ጋር መኖር ይጠበቅብናል። ከእርሱ ጋር ሆነን ድምጻችንን ወደ ላይ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ሳንሰለች ጸሎታችንን ወደ እርሱ ማቅረብ ያስፈልጋል። ጌታ ሆይ አድነኝ በማለት ወደ እርሱ መጮህ ያስፈልጋል። ዛሬ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በመሆኑ የደቀ መዛሙርቱ ድንጋጤ እና ጩሄት አንድ ነገር እንዳስታውስ አድርጎኛል። በትላልቅ ጀልባዎች ተሳፍረው የሜዲቴራኒያን ባሕር ሲያቋርጡ የነበሩ ስደተኞች አደጋ ባጋጠማቸው ጊዜ “አድኑን” እያሉ የነፍስ አድን ዕርዳታን ሲለምኑ ተመልክቻለሁ። እኛም በሕይወታችን ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። በዚህ ጊዜ ታዲያ “ጌታ ሆይ እርዳን!”፣ “ጌታ ሆይ አድነን!” ብለን ጸሎታችንን እና ጩሄታችንን ወደ እርሱ እናቀርባለን።

ዛሬ እያንዳንዳችን ‘ሕይወታችንን የሚመታ አውሎ ነፋስ የትኛው ነው? በመንፈሳዊ ሕይወታችን ወደ ፊት እንዳንራመድ፣ ለቤተሰባችን ሕይወት እና ለስነ-ልቦናችንም እንቅፋት እየሆነብን የሚያደናቅፈን ማዕበል የቱ ነው’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ችግሮቻችንን በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንንገርለት።  የመከራችን ጊዜ መሸሸጊያ እርሱን እናድርግ፣ ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው። ከማር. 4፡ 35-41 የተወሰደው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ይህን ይነግረናል። በማር. 4፡38 ላይ ‘ደቀ መዛሙርቱ ቀሰቀሱትና መምህር ሆይ! ስንጠፋ ዝም ትላለህን?’ አሉት ይላል። ስለዚህ ኢየሱስ እንድንቀሰቅሰው እና ችግራችንን በሙሉ እንድንነግረው ይፈልጋል። የእምነታችን መነሻ ይህ ነው። ምክንያቱም የመስጠም አደጋን፣ ማንኛውንም ችግር ብቻችን ልንቋቋመው አንችልም። መርከበኞች መንገዳቸውን ለማግኘት ኮከቦችን እንደሚፈልጉት ሁሉ እኛም ኢየሱስን እንፈልጋለን። እምነታችን የሚጀምረው ችግሮቻችንን ለማሸነፍ ብቻችን አቅም እንደሌለን ስናውቅ ነው። የእግዚአብሔር ዕርዳታ እንደሚያስፈልገን ስንገነዘብ ነው። ሊጋርደን የሚሞክረውን ፈተና ስንቋቋም፣ በጸሎታችን እግዚአብሔርን እንዳንጠይቅ የሚያደርግ የውሸት እምነት አሸንፈን ስንግኝ፣ እግዚአብሔር እርሱ በሕይወታችን ድንቅ ነገሮችን አድርጎ ሊያሳየን ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ ተዓምራትን ሊያደርግ የሚችል የጸሎት ኃይል ነው።

ኢየሱስም በደቀ መዛሙርቱ በተለመነ ጊዜ አውሎ ነፋሱን እና ማዕበሉን ጸጥ አደረገ። ከዚህም በኋላ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፥ ‘እንዲህ የምትፈሩት ለምንድን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?’ የማር. 4፡40. ደቀ መዛሙርትም በማዕበሉ ደንግጠው እና ፈርተው ስለነበር ኢየሱስን አይመለከቱም ነበር። ፍርሃት አዕምሮአችንን ወደ ችግራችን እንድናደርግ እንጂ ችግራችንን ወደሚፈታ ወደ ኃያሉ ጌታችን እንድንመለከት አያደርገንም። ለመሆኑ ስንቶቻችን ቀድመን ችግሮቻችንን ለኢየሱስ ከመንገር፣ የእርሱን ዕርዳታ ከመለመን ይልቅ በችግሮቻችን ላይ ብቻ እናተኩራለን? ችግር በበዛበት ሕይወታችን ውስጥ ስንት ጊዜ ኢየሱስን ወደ ጎን አድርገነዋል? ወይም በችግራችን ጊዜ ብቻ ወደ እርሱ እንቀርባለን? ፈጽሞ ሳይደክም ዘወትር የኢየሱስን ዕርዳታ የሚፈልግ የእምነት ጸጋ እንዲበዛልን አጥብቀን መጠየቅ ይኖርብናል። እምነቷን ዘወትር በእግዚአብሔር ላይ ያደረገች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እኛም ዘወትር በእግዚአብሔር ተማምነን የሚያስፈልገንን ሁሉ ከእርሱ ለመቀበል የሚያስችለንን የእምነት ጸጋን እንዳታሰጠን በጸሎት እንማጸናታለን።”  

21 June 2021, 20:55