ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ጋር  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ጋር  

ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፣ “በአውሮፓ ውስጥ የስደተኞችን ስቃይ ማየት ያማል” ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኔ 4/2013 ዓ. ም የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋቸውል። ቅዱስነታቸው በአውሮፓ ኅብረት አገሮች ውስጥ የመወያያ ርዕሥ ሆኖ የቆየው የስደተኞች ጉዳይን ከጉባኤው ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል። በዚህ ወቅት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፣ ስደተኞችን በአውሮፓ ውስጥ ኑሮአቸውን እንዲመሰርቱ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጸው፣ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ኦቨርቤክ የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በመጥቀስ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያን ስደተኞችን እንዲሁ በሜዳ የማትጥላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለማችን የታየው አስከፊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስደትን በማባባሱ ምክንያት ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚደረጉ የባሕር ላይ ጉዞ መጨመሩን ከሰኔ 2/2013 ዓ. ም ጅምሮ ሲካሄድ የቆየው የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በጉባኤያቸው ማጠቃለያ ላይ አስታውቀዋል።

“ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአውሮፓ ወዳጅ ናቸው”

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ከመገናኘታቸው በተጨማሪ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና በቅድስት መንበር የልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች ሃላፊ ብጹዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ባደረጉት ውይይት ደስ መሰኘታቸውን ገልጸዋል። አክለውም ቅዱስነታቸው አውሮፓን በሚገባ እንደሚያውቁት እና የአውሮፓ ወዳጅም መሆናቸውን አስረድተው፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን” የሚሉ ሁለቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖች በቤልጂየም ብራስልስ ከተማ በሚገኝ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ውስጥ በስፋት የሚነገር መሆኑንም አስታውሰዋል።

ስደተኞች ኑሮአቸውን በአውሮፓ እንዲመሰርቱ ማድረግ ይቻላል

ስፔን እና ዴንማርክን ጨምሮ በዓለማችን ውስጥ በዜና የተሰራጨው የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ የመወያያ ርዕሠ ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአውሮፓ ኅብረት አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ቋሚ ኮሚቴ አባላት አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ገልጸው፣ የበርካታ አገሮችን በር በማንኳኳት ላይ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መከራ ፈጽሞ መርሳት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል። የአውሮፓ ኅብረት ከስደት ጋር  የተገናኙ ፖለቲካዊ ርዕሠ ጉዳዮችን በስፋት የሚወያይ መሆኑን ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ተናግረው፣ ቢሆንም በአውሮፓ ውስጥ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ማልታ እና ግሪክ ብቻ ስደተኞችን ተቀብለው እንዲያስተናግዱ መደረጉ አውሮፓን የሚያሳፍር መሆኑን አስረድተዋል። አገራቸው ሉክስንቡርግ በርካታ ሰደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እያስተናገደች መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፣ በቅርቡ ከሶርያ እና ከኩዌት የመጡ ሁለት ክርስቲያን እና ሙስሊም ጥገኝነት ጠያዊ ቤተሰቦችን መቀበሏን ገልጸው ቤተክርስቲያን ለእነዚህ ቤተሰቦች የሚያስፈልገውን ወጪ በሙሉ የሸፈነችላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከአገራቸው የሚሰደዱት ቤተሰቦች እንደ ሌሎች ሰላማዊ፣ ደስተኛ እና የተረጋጋ ሕይወት ሲኖሩ መመልከት የሚያስደስት መሆኑን ገልጸው፣ ይህን ዕድል ያላገኙ በቁጥር በርካታ ቤተሰቦች መኖራቸውን ማስተውል ያስፈልጋል ብለዋል።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙ መማር ያስፈልጋል

“ልባችንን ክፍት አድረገን መጠበቅ ያስፈልጋል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፣ አንድነትን፣ መረዳዳትን እና ማኅበራዊ ግንኙነታችንን ካላሳደግን ስብዕናችን ውርደት እንደሚያጋጥመው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለው ስቃይ መማር  ያስፈልጋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም በአውሮፓ ውስጥ ዕርዳታን የሚለምኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መኖራቸውን መርሳት የለብንም ብለው፣ እነዚህን ችግረኞች መርዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሜዲቴራኒያን ባሕር፣ ትልቁ መቃብር

የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ፍራንስ ዮሴፍ ኦቨርቤክ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ሰዎች ከመሰደድ ይልቅ በአገራቸው ሆነው የሚታገዙበትን መንገድ ቤተክርስቲያን መፈለግ ይኖርባታል ብለው፣ በሜዲቴራኒያ ባሕር ውስጥ ሞተው የሚቀሩ በርካታ ከማሊ እና በሊቢያ በኩል የሚመጡ ስደተኞችን አስታውሰዋል። መፍትሄ ካልተገኘለት ችግሩ በሁለት እና በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም በመቶ ዓመታት ውስጥም የሚፈታ አለመሆኑን አስረድተዋል። 

ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ ያስፈልጋል

በጨለማው የናዚዎች ሥርዓት ዘመን አይሁዳዊያን ተቀብለው የሚያስተናግዷቸውን አጥተው ለከፍተኛ መከራ መዳረጋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ፍራንስ ዮሴፍ ኦቨርቤክ፣ ይህን የመሰለ መከራ ፈጽሞ በዓለማችን እንዳይደገም አሳስበው፣ የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአውሮፓ ኅብረት አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ፣ የአውሮፓ አገራት ስደተኞችን በክብር ተቀብለው ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አክለውም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስደተኞች የሚገኙበትን ሁኔታ በሚገባ እንደሚያውቁ፣ ጥያቄዎቻቸውም ምን እንደሆኑ፣ ስደተኞች በአውሮፓ ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን የሚያጋጥማቸውን ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ፣ ለዕለታዊ ሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን እንዴት ማቅረብ እንደሚገባ ተገንዝበዋል ብለዋል።

በችግር ላይ ለሚገኙ አገሮች የሚደረግ የቤተክርስቲያን ዕርዳታ

ቤተክርስቲያን እንደ መሆናችን የተቸገረን ለመርዳት ተጠርተናል ያሉት ብጹዕ አቡነ ፍራንስ ዮሴፍ ኦቨርቤክ፣ በዚህ ፍቅር ተነሳስተን የጀርመን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በዓለማችን ውስጥ በችግር ውስጥ ለሚገኙ አገራት፣ ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ላጋጠማት ቨነዙዌላ፣ ከመንግሥት ጋር በመተባበር የመድኃኒት ዕርዳታ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።   

12 June 2021, 16:34