ፈልግ

የመላዋ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ሲኖዶስ ዝግጅት በየአገራቱ የሚጀምር መሆኑ ተነገረ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሦስት ዓመታትን የሚወስድ እና በየሀገረ ስብከቶች፣ በአህጉራት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ጠቅላላ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉባኤን በመጭው መስከረም ወር 2014 ዓ. ም. በጸሎት የሚያስጀምሩት መሆኑ ተገለጸ። በሦስት ዓመታት ውስጥ በሁሉም አገራት በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚካሄዱት የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉባኤዎች ምክክር እና ማስተዋል ያለበት ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. በሮም ውስጥ የሚገባደድ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አንዱ ሌላውን በጽሞና ካዳመጠ በኋላ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚለውን በጋራ ማድመጥ ያስፈልጋል” በማለት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መከተል ያለበትን መንገድ ቅዱሱ አባታችን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መንበረ ስልጣንን በተረከቡበት ወቅት ማሳሰባቸው ይታወሳል። ይህ ምኞታቸው ተግባራዊ እንዲሆን መጭው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላላ ሐዋርያዊ ሲኖዶስ ከሀገረ ስብከት ደረጃ ጀምሮ በአምስቱ አህጉራት ከተካሄደ በኋላ በጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. በቫቲካን አስጥ በሚከሄድ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳስት ሐዋርያዊ ጉባኤ የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል።

ወሳኝ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሂደት

በየአገራቱ የሚገኙ ቤተክርስቲያናት ይህን መንገድ በመከተል ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን በተለይም የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳተፍ እንዲካሄድ በማለት ዓርብ ግንቦት 13/2013 ዓ. ም. ከጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የወጣ መግለጫ አስታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉባኤ በሙላት ሊካሄድ የሚችለው በየአገራቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን እና ጳጳሳዊ ጉባኤዎችን በማሳተፍ መሆኑን የጳጳሳቱ ሲኖዶስ አስታውቋል። 

አንድ አካባቢን ብቻ ያላማከለ ሲኖዶስ

በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወቅት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ያዋቀሩት ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሁሉ አቀፍ ባሕሪውን መቀጠል እንዳለበት የጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መልዕክት ገልጾ፣ የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ የተመሠረተበት ሃምሳኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ምዕመናንን፣ የቤተክርስቲያን አባቶችን እና የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስን የሚያሳትፍ እንዲሆን መመኘታቸውን ካስገነዘበ በኋላ ቀጣዩ የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉባኤ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም አካባቢዎች ደረጃ በደረጃ ያማከለ ሐዋርያዊ ሲኖዶድ እንደሚሆን አስታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በማከልም መጭው መስከረም 29 እና 30/2014 ዓ. ም ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በይፋ የሚያስጀምሩት ጠቅላላ ሐዋርያዊ ሲኖዶስ በአስተንትኖ፣ በጸሎት እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወን መሆኑን አስታውቋል።

በሀገረ ስብከቶች ደረጃ የሚካሄደው ሐዋርያዊ ሲኖዶሱ እሑድ ጥቅምት 7/2014 ዓ. ም. የሚጀምር ሲሆን፣ ጉባኤውን በበላይነት የሚመሩት የዚያው ሀገረ ስብከት መሪ ጳጳስ መሆናቸው ታውቋል። ይህን ለማካሄድ የሚያግዙ የዝግጅት ሰነዶችን እና ቃለ መጠይቆች ከጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ለየሀገረ ስብከቶች የሚላክ መሆኑ ታውቋል። ተመሳሳይ ሰነዶቹ ወደ ቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች፣ ለገዳማዊያን እና ገዳማዊያት የበላይ አለቆች፣ ለዓለም አቀፍ ምዕመናን እንቅስቃሴዎች፣ ለካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲዎች ወይም ለስነ መለኮት ፋኩልቲዎች የሚላክ መሆኑ ታውቋል። እያንዳንዱ የሀገር ስብከት ጳጳስ፣ በሀገር ስብከቶች ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ከጥቅምት ወር አስቀድሞ ማዘጋጀት እንዳለበት የጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በአህጉራት ደረጃ የሚካሄድ ውይይት

በሁለተኛ ደረጃ የሚካሄደው አህጉራዊ ሲኖዶስ ከመስከረም ወር 2014 ዓ. ም. የሚጀምር እና በየካቲት ወር 2015 ዓ. ም. የሚገባደድ መሆኑን የጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ዓላማውም በዋናው የመወያያ ርዕሥ ላይ የጋራ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ከአምስቱም አህጉራት የተሰበሰቡት የውይይት ንድፎች ለሁለተኛው ሰነድ ዝግጅት ወደ ጠቅላላ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የሚላኩ መሆኑ ታውቋል።

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ደረጃ

ቅዱስ አባታችን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተመኙት አዲስ የመላው ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉባኤ በጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚፈጸም መሆኑን የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

22 May 2021, 15:48