ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ልባችንን እና አዕምሮአችንን በማንቃት ጸሎታችንን ሳናቋርጥ ማቅረብ ያስፈልጋል”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 11/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ለተገኙት ምእመናን የተለመደውን ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ አስተምሮአቸው ስንፍናን በማስወገድ፣ ልባችንን በማንቃት ጸሎታችንን በዕርጋታ መንፈስ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅታችን ተከታታዮች ከዚህ በታች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተከበራችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ሳምንታዊውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችንን በመቀጠል በዛሬው አስተምሮአችን በተግባር የተገለጠውን የጸሎት ልምድ በመመልከት በዚህ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለይተን በማወቅ እንዴትስ ማሸነፍ እንዳለብን እንመለከታለን።

ከችግሮቹ መካከል የመጀመሪያው እና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁ. 2729 ላይ እንደተገለጸው ፥ በጸሎት ጊዜ የሕሳብ መበታተን የሚል ነው። በእርግጥ የሰው ልጅ አዕምሮ በአንድ ሐሳብ ላይ ብቻ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይከብደዋል። ይህ ችግር በጸሎት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመኝታችንም ወቅትም በአእምሮ አችን ውስጥ እየተመላለሰ የሚያስጨንቀን ጉዳይ ነው። ይህ ታዲያ የአዕምሮን አለመረጋጋት የሚያስከትል በመሆኑ እንዲደጋገምብን አንፈልግም።

የተረጋጋ አዕምሮ እንዲኖረን ጥረት የምናደርገው በጸሎት ወቅት ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ዕለታዊ ተግባር በምናከናውንበት ሰዓት ነው። አዕምሮአችን የተረጋጋ ካልሆነ በምናከናውነው ሥራችን ውጤታማ ልንሆን አንችልም። ሯጮች በውድድራቸው ወቅት መልካም ውጤትን ለማግኘት የአካል ጥንካሬ ልምምዶችን ማድረግ ብቻ ሳይሆን በምን ላይ ማትኮር እንዳለባቸው የሚያግዝ የአእምሮ ብቃት እና መረጋጋት ሊኖራቸው ይገባል።

መዘናጋት ስህተት አይደለም፣ ነገር ግን ልንታገለው ይገባል። በእምነታችን ውስጥ ረስተን የምናልፋቸው ብዙ መልካም ተግባሮች አሉ። እነዚህን መልካም ተግባራት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። ይህም ‘የልብ ንቃት’ የምንለው ነው። ጸሎታችን ነቅተን እንድናቀርብ በትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ በቁ. 2730 ላይ በግልጽ ተቀምጦ እናገኘዋለን። በዚህ ቁጥር ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያስተምር እርሱ የሚመጣበት ጊዜ መጨረሻዋ ቀን በየዕለቱ ዛሬም ሊሆን እንደሚችል በጥብቅ ያሳስባል። ሙሽራው በእኩለ ሌሊትም ሊመጣ ስለሚችል መብራት መጥፋት እንደሌለበት፣ ጌታውም ከሄደበት የሚመለስበት ጊዜ ስለማይታወቅ በማለት ያስረዳል። ጌታ የሚመጣበት ቀን ሆነ ሰዓቱን ስለማናውቅ ውድ የሆነችውን እያንዳንዷ የሕይወታችን ደቂቃ በከንቱ መባከን እና ተዘንግታ መታለፍ የለባትም። ባልጠበቅነው ሰዓት የጌታ ድምጽ እንዲህ ይለናል፥ በዚያች ቀን ልባቸውን መልካም እና ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ላይ ያደረጉት የተባረኩ ናቸው። ምክንያቱም በሚመለከቱት ሁሉ ላይ ልባቸው እና አዕምሮአቸው ሳይረበሽ ወይም ሳይታለል፣ ትክክለኛውን መንገድ ለመጓዝ፣ ሥራቸውንም በተገቢ መልኩ ለማከናወን ጥረት አድረገዋልና።

ሌላው በጸሎት ወቅት ሊያጋጥመን የሚችል ችግር ልባችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ጭራሹኑ መራቅ ነው። ትምህርተ ክርስቶስም በቁ. 2731 ይህንኑን ያረጋግጥልናል። ስለ እግዚአብሔር ምንም ዓይነት ሃሳብ፣ ስሜት እና መንፈሳዊ ጥማት አለመኖር ማለት ነው። ይህ ወቅት ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥቃይ እና መቃብር ጋር በታማኝነት እና በእምነት የምንጣበቅበት ጊዜ ነው። ልባችን ባዶ የሚሆንበት ምክንያት ማወቅ አንችልም። በእኛ ምክንያት ሊሆን የሚችል ቢሆንም ይህን የመሳሰሉ ነገሮች በውጫዊው እና ውስጣዊው ሕይወታችን እንዲከሰቱ የሚፈቅድ እግዚአብሔር ብቻ ነው። መንፈሳዊ መምህራኖቻቸን ይህን የእምነት ልምድ ቀጣይነት ያለው የመጽናናት እና የጥፋት ጊዜያት መለዋወጥ በማለት ይገልጹታል። በሕይወታችን ውስጥ ሁሉ ነገር ቀላል እና የተስተካከለ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ከባድ የሚሆንበት ጊዜ አለ።

ስንፍና፣ በጸሎት ወቅት ፈተና የሚሆንብን ሌላው ችግራችን ነው። በተለይም በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ ትልቁ ፈተና የሚሆንብን ስንፍና ነው። ስንፍና የክርስትና ሕይወታችን ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ፣ ነቅተን እንዳንቆይ የሚያደርገን እና በልባችን ውስጥ ግድ የለሽነትን የሚፈጥር እንቅፋት እንደሆነ በትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2733 ላይ ተገልጾ እንገኘዋለን። ስንፍና ወደ ሞት ከሚያደርሱን ሰባቱ ኃጢአቶች መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም ከትዕቢት የተነሳ የነፍስ ሞትን ያስከትላል።

ታዲያ በዚህ ተከታታይ የጋለ ስሜት ወቅት እና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ምን ማድረግ እንችላለን? ምንም ዓይነት እንቅፋት እና ችግር ቢያጋጥመን ተስፋን ሳንቆርጥ ወደ ፊት መጓዝን መማር ያስፈልጋል። በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ እድገት የሚገኘው ደስታን በመጨመር ሳይሆን በመከራ እና አስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ ጸንተን መቆም በመቻላችን ነው። ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስለ እውነተኛ እና ትክክለኛ ደስታ የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት። የአንድ ወንድም ሕይወት የሚለካው ከሰማይ በወረደለት የመጨረሻ ዕድል ሳይሆን ሕይወቱን ጠንክሮ በመጓዝ፣ በሌሎች ዘንድ የተረሳ እና በደል እንኳ ሲደርስበት እና አስቀድሞ የነበረው ስሜት ሲደርቅ እና ከእርሱ በሚርቅበት ጊዜ ሁሉ ግራ ቀኛ ሳይል ጸንቶ መጓዝ ሲችል ነው። ቅዱሳን በሙሉ ይህን የመሰለ የጨለማ ሕይወት ኖረዋል፣ የሕይወት ታሪካቸውን በምናነብበት ጊዜ የምሽት ጸሎታቸውን ያለ ማስተዋል ማቅረባቸውን መረዳት ስለምንችል እንግዳ ነገር ሊሆንብን አይገባም። ጸሎት በምናደርስበት ጊዜ “አምላኬ ሆይ በአንተ ማመን እንዳቆም ለማድረግ፣ ሁሉም ነገር እንዲሆን ያንተ ፈቃድ እንዲሆን የምታደርግ ብትመስልም አሁንም ደግሞ ወደ አንተ መጸለይን አላቋርጥም” ማለት ያስፈልጋል። አማኞች መጸለይን ፈጽሞ አያቁርጡም። አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን “እግዚአብሔር ቅጣትን ልኮብኛል፣ ጸሎቴንም ሊቀበለኝም አይፈልግም፣ ወደ ፍርድ አሳልፎ ሰጥቶኛል የሚለውን የኢዮብን ጸሎት ሊመስል ይችላል።

ከኢዮብ ይልቅ ለቅድስና እጅግ ርቀን የምንገኝ እኛም ብንሆን፣ ብዙን ጊዜ ፊታችንን ወደ ሰማይ አቅንተን፣ አምላክ ሆይ! ይህ ለምን ሆነ በማለት ጥያቄዎቻችንን ወደ እግዚአብሔር ስናቀርብ፣ እርሱ መልስ ሊሰጠን ይችላል። የእኛን ከባድ እና መራራ ስሜቶቻችንን እንኳ በአባታዊ ፍቅሩ ይቀበልልናል። እንደ እምነት እርምጃ በመመልከት እንደ ጸሎትም ይቆጥርልናል፤ አመሰግናለሁ።      

19 May 2021, 16:34