ፈልግ

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት እንዲታወስ ጥሪ አቀረቡ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ ከአርባ ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ በክብር ያረገበት የዕርገት በዓል ግንቦት 08/2013 ዓ. ም ተከብሯል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከምዕመና ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከሰኞ ግንቦት 9/2013 ዓ. ም ጀምሮ ባሉት የሳምንቱ ቀናት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት፣ መላው ምዕመናን በስቃይ ላይ የምትገኘውን የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እና በድህነት የሚሰቃየውን የዓለማች ሕዝብ በማስታወስ መልካም ተግባራትን በመፈጸም እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት ዝግጅቶችን ያስተባበረውን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን እና በርካታ ተባባሪ ድርጅቶችን አመስግነዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት መልዕክታቸው የዓለማችን ሕዝብ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚያደርገውን የእንክብካቤ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሳድግ አደራ ብለው በዚህ ሳምንት ውስጥ እንዲከናወን በቀረቡት ዝግጅቶች እንዲሳተፉ አደራ ብለዋል።

በሳምንቱ ውስጥ የሚከናወኑ ዝግጅቶች

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የአየር ንብረት ለውጥ የሚከታተል እንቅስቃሴ፣ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት የበላይ አለቆች፣ የኢየሱሳዊያን ማኅበር እና የፍራንችስካዊያን ወንድሞች ማኅበር በጋራ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመመራት የመላውን ዓለም ካቶሊካዊ ምዕመናን በማስተባበር የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል የአካባቢ ጥበቃን እና እንክብካቤን ሲያድረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በመተባበር ግንቦት 8/2013 ዓ. ም ባስታወቀው መርሐ ግብር አንድ ሳምንት የሚቆይ “ውዳሴ ላንት ይሁን” ሳምንት እንዲከበር መውሰኑ ታውቋል። ዘንድሮ የተዘጋጀው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት በዓመቱ ውስጥ የተወሰዱ እርምጃዎች ያመጧቸው ውጤት የሚታዩበት ልዩ ዓመት መሆኑ ታውቋል። ዓመቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በርካታ እንቅፋቶችን ያስከተለበት በመሆኑ በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመታገዝ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል የሚረዱ የአሥር ዓመት መርሐ ግብሮችን ማውጣት የሚያስፈልግ መሆኑ ታውቋል።

ወንጌልን መሠረት ያደረገ የተፈጥሮ እንክብካቤ

ከሰኞ ግንቦት 9/2013 ዓ. ም ጀምሮ በተግባር እንዲውሉ የሚደረጉ ዕቅዶች በሚቀጥሉት ጊዜያት ለሚከናወኑ ተግባራት አቅጣጫን የሚያመላክቱ መመሪያዎች መሆናቸው ታውቋል። መመሪያዎቹም www.laudatosi.va በሚለው የቫቲካን ድረ-ገጽ ላይ የሚገኙ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ትናንት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ባቀረቡት ጸሎት መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከምትገኝበት ስቃይ እንድትወጣ የሚያደርገው ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ እንድታስገኝልን በጸሎታቸው ጠይቀዋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከሌሎች በቁጥር 150 ከሚሆኑ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ለማስተካከል የሚጥሩ ካቶሊካዊ ተቋማትን የሚያስተባብር መሆኑ ታውቋል።

የ2013 ዓ. ም የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት መርሐ ግብር

ለዘንድሮ የቀረቡት የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት መርሐ ግብር ርዕሶች በአውታረ መረብ በኩል ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን በውይይቱ ወቅት ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ ምስክርነቶች የሚደመጡ መሆናቸው ታውቋል። ዛሬ ሰኞ ግንቦት 9/2013 ዓ. ም. በተጀመረው ውይይት እና በሚቀጥሉ ቀናት በሚቀርቡ የመወያያ ርዕሶች ሥር የተባበሩት መንግሥታት ከዚህ በፊት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የመከረባቸው ርዕሠ ጉዳዮች እና በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጭብጥ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ተቋማት የሚቀርቡ ጥናታዊ ሥራዎች የሚቀርቡ መሆናቸው ታውቋል።

የውይይት እና የጸሎት ፕሮግራሞች ተካትተዋል

መጭው ዓርብ ግንቦት 13/2013 ዓ. ም ዓለም አቀፍ የተግባር መርሐ ግብር ቀን የሚታወጅበት እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች ዓለማችንን ከጉዳት ለማትረፍ የሚያስችሉ ገንቢ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ጥሪ የሚቀርብበት ቀን እንደሚሆን ይጠበቃል። እሑድ ግንቦት 15/2013 ዓ. ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በሮም እና በአሲዚ ከተሞች “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ የሆነበት ስድስተኛ ዓመት መዝጊያን ምክንያት በማድረግ የጸሎት ስነ ስርዓቶች የሚፈጸሙ መሆኑ ታውቋል። የጸሎት ስነ ስርዓቱ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ የሚመራ መሆኑ ታውቋል። ሰኞ ግንቦት 16/2013 ዓ. ም በሮም አቆጣጠር ከምሽቱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን የሚሳተፉበት የንጹሕ ውሃ አቅርቦት እና የጤና አጠባበቅ የሚመለከት ውይይት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። 

17 May 2021, 16:03