ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እውነተኛ የክርስቲያን ሕይወት ስለ ክርስቶስ ይመሰክራል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በእለቱ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት በሚያዝያ 24/2013 ዓ.ም ቅዱስነታቸው በቫቲክን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ መእመናን ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል 15፡1-8 ላይ ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን እውነተኛ የክርስቲያን ሕይወት ስለ ክርስቶስ ይመሰክራል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ በፋሲካ አምስተኛው እለተ ሰንበት (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ማለታቸው ነው) ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ. 15 1-8) ውስጥ ጌታ ራሱን እንደ እውነተኛ የወይን ተክል አድርጎ ያቀርባል ፣ እናም እኛ ቅርንጫፎች በመሆናችን የተነሳ ከእርሱ ጋር ካልተባበርን በስተቀር መኖር እንደማንችል ስለእኛ ይናገራል። እናም ስለዚህ እርሱ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎች ናችሁ” ይላል (ዮሐንስ 15፡5)። ያለ ቅርንጫፎች የወይን ግንድ ሊኖር አይችልም፣፣ እና በተቃራኒው ቅርንጫፍ ከሌለ የወይን ግንድ ሊኖር አይችልም። ቅርንጫፎቹ ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ አይደሉም ፣ ግን ሙሉ በሙሉ የሚመረኮዙት የህልውናቸው ምንጭ በሆነው የወይን ተክል ላይ ነው።

ኢየሱስ “በእኔ ኑሩ” የሚለውን ግስ አጥብቆ ይናገራል። በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ንባብ ውስጥ ሰባት ጊዜ የሚደጋገም ቃል ነው። ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እና ወደ አብ ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር አንድ ሆነው መኖር መቀጠላቸውን ሊያረጋግጥላቸው ይፈልጋል። እሱም “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ ውስጥ እኖራለሁ” (ዮሐንስ 15፡ 4) ይላለናል። ይህ በእኔ ኑሩ የሚለው ቃል በራሱ በሕይወት በመግባት ጌታ እንዲወደን በመፍቀድ በጌታ ውስጥ “አንቀላፍቶ” ዝም ብሎ የመኖር ጥያቄ አይደለም። ይህ አይደለም። በእርሱ ውስጥ መኖር ማለት እርሱ ለእኛ በሚያቀርብልን መሰረት በኢየሱስ ውስጥ መኖር፣ በንቃት መኖር ማለት ነው፣ እንዲሁም ደግሞ በምላሹ እርሱ በእኛ ውስጥ እንዲኖር መፍቀድ ማለት ነው። ለምን? ያለ ወይኑ ቅርንጫፎች ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ለማደግ እና ፍሬ ለማፍራት የሕይወት ምንጭ ያስፈልጋቸዋል፣ ዛፍ ግንዱ ላይ ፍሬ የማያበቅል በመሆኑ የተነሳ ወይኑም ቅርንጫፎቹን ይፈልጋል። እሱ እርስ በእርሱ የመደጋገፍ ፍላጎት ነው ፣ ፍሬ ለማፍራቱ ደግሞ እርስ በእርስ የመተዛዘን ጥያቄ ነው። እኛ በኢየሱስ እንኖራለን ኢየሱስም በእኛ ውስጥ ይኖራል።

በመጀመሪያ ለእኛ እርሱ ያስፈልገናል። ጌታ ትእዛዛቱን ከማክበራችን በፊት፣ ብሩክ ከመሆናችን በፊት፣ የምሕረት ተግባራትን ከመፈጸማችን በፊት፣ ከእርሱ ጋር አንድ መሆን ፣ በእርሱ ውስጥ መቆየት አስፈላጊ መሆኑን ሊነግረን ይፈልጋል። በኢየሱስ ውስጥ ገብተን መኖር ካልቻልን ጥሩ ክርስቲያን መሆን አንችልም። በእርሱ በኩል በምትኩ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን (ፊል 4፡13)። በእርሱ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን ፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ እንኳን እኛን ይፈልጋል ፣ እንደ ወይኑ ከቅርንጫፎቹ እርሱ ከእኛ ጋር መሆን ይፈልጋል።  ምናልባት ይህ ማለት ለእኛ ድፍረት ይመስላል ፣ እናም እኛ እራሳችንን እንጠይቃለን-ኢየሱስ በምን መልኩ ነው እኛን የሚፈልገው? እርሱ የእኛን ምስክርነት ይፈልጋል። ልክ እንደ ቅርንጫፎቹ መስጠት ያለብን ፍሬ እንደ ክርስቲያኖች በሕይወታችን ስለ እርሱ መመስከር ይገባናል። ኢየሱስ ወደ አብ ካረገ በኋላ የደቀመዛሙርቱ ተግባር - የእኛ ተግባር ነው - በቃላት እና በተግባር ወንጌልን ማወጅ መቀጠል ነው። ደቀ መዛሙርቱም - እኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት - ይህን የምናደርገው ስለ ፍቅሩ በመመስከር ነው-ፍሬ ማፍራት ፍቅር ነው ከክርስቶስ ጋር ተያይዘን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች እንቀበላለን እናም በዚህ መንገድ ለባልንጀሮቻችን መልካም ማድረግ ፣ ለህብረተሰቡ እና ለቤተክርስቲያን መልካም ማድረግ እንችላለን። ዛፉ በፍሬው ይታወቃል። እውነተኛ የክርስቲያን ሕይወት ስለ ክርስቶስ ይመሰክራል።

እናም ይህንን ለመፈጸም እና ለማሳካት እንዴት እንችላለን? ኢየሱስ እንዲህ ይለናል-“በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም” (ዮሐንስ 15፡7)። ይህ ደግሞ ደፋር የሆነ ሐስተሳሰብ ሊመስል ይችላል፣ የምንለምነው ነገር እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። የሕይወታችን ፍሬያማነት በጸሎት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ እርሱ ለማሰብ ፣ እሱን ለመምሰል ፣ ዓለምን እና ነገሮችን በኢየሱስ ዓይኖች ለመመልከት መጠየቅ እንችላለን። እናም በዚህ መንገድ ከድሆች እና በጣም ከሚሰቃዩት ጀምሮ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን መውደድ ፣ በልቡም መውደድ እና የመልካምነትን ፣ የበጎ ፍሬ ፣ የሰላም ፍሬዎችን ለዓለም ማምጣት እንችላለን።

ለድንግል ማርያም አማላጅነት እራሳችንን በአደራ እንስጥ። እሷ ሁል ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሙሉ በሙሉ አንድነትን በመፍጠር ብዙ ፍሬ አፍርታለች። ከሙታን የተነሳውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለም ውስጥ መመስከር እንችል ዘንድ በክርስቶስ ፣ በፍቅሩ ፣ በቃሉ እንድንኖር እርሷ ሁላችንንም በአማላጅነቷ ትርዳን።

02 May 2021, 11:47