ፈልግ

የወንጌል ደስታ የወንጌል ደስታ 

የወንጌል ደስታ

የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ለውጥ

ስብከተ ወንጌል የሚካሄደው ‹‹እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝሁአችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው›› (ማቴ.28፡19-20) ለሚለው የኢየሱስ የተልእኮ አደራ ታዛዥ ስንሆን ነው፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ከሞት የተነሣው ክርስቶስ በሁሉም ጊዜና በሁሉም ስፍራ ወንጌልን እንዲሰብኩና በእርሱም ላይ ያለው እምነት እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ እንዲደርስ ያደርጉ ዘንድ ተከታዮቹን እንዴት እንደላከ እናያለን፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

I.                  ወደፊት የምትሄድ ቤተክርስቲያን

 

እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን ‹‹ወደፊት እንዲሄዱ›› እንዴት እንደሚጠይቃቸው የእግዚአብሔር ቃል ያለማቋረጥ ይነግረናል፡፡ አብርሃም ወደ አዲስ ምድር እንዲሄድ ጥሪ ደረሰው (ንጽ.ዘፍጥ.12፡1-3)፡፡ ሙሴ ‹‹ሂድ፣ እልክሃለሁ›› (ዘጸ.3፡10) የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ሰማ፤ ሕዝቡንም ወደ ተስፋይቱ ምድር መራ (ንጽ.ዘፀ.3፡17)፡፡ እግዚአብሔር ኤርምያስን ‹‹ወደምልክህ ሁሉ ትሄዳለህ›› (ኤር.1፡7) አለው፡፡ በዘመናችንም ‹‹ሂዱና ደቀ መዛሙርቴ አድርጉአቸው››! የሚለው የኢየሱስ ትዕዛዝ በተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጡ በመጡ የቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ተልእኮ አዳዲስ ተግዳሮቶች ውስጥ ያስተጋባል፡፡ እኛም ሁላችን በዚህ አዲስ የ‹‹ሂዱ›› ተልእኮ እንድንሳተፍ ተጠርተናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንና ማህበረሰብ ጌታ የሚያሳየውን መንገድ ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን፣ ሁላችንም የወንጌልን ብርሃን ፍለጋ ከራሳችን ምቹ አካባቢ ተነሥተን ወደ ‹‹ዳርቻ›› ሁሉ እንድንሄድ የሚጠይቀንን የእርሱን ትዕዛዝ ማክበር አለብን፡፡

የደቀ መዛሙርት ማኅበርን የሚያደምቀው የወንጌል ደስታ የተልእኮ ደስታ ነው፡፡ ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተልእኮአቸው በተመለሱ ጊዜ የተሰማቸው ይኸው ነው (ንጽ.ሉቃ.10፡17)፡፡ ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ  ሐሴት አድርጎ ራሱን ለድሆችና ለሕፃናት የገለጸውን አብን ባመሰገነ ጊዜ የተሰማው ይኸው ነው (ንጽ. ሉቃ.10፡21)፡፡ በጴንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያት ‹‹በገዛ ቋንቋቸው›› (የሐዋ.2.6) ሲናገሩ የሰሙ የመጀመሪያዎቹ ምእመናን የተሰማቸው ይኸው ነበር፡፡ ይህ ደስታ ወንጌል ለመሰበኩና ፍሬ ለማፍራቱ ምልክት ነው፡፡ ሆኖም የመሄድና የመስጠት፣ ከራሳችን ወጥተን የመሄድ፣ መልካም ፍሬ መዝራት የመቀጠላችን ተነሣሽነት ምን ጊዜም አይቋረጥም፡፡ ጌታ ‹‹ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና››  (ማር.1፡38) አለ፡፡ በአንድ ስፍራ አንዴ ዘሩ ከተዘራ በኋላ ኢየሱስ ነገሮችን ለማብራራት ወይም ተጨማሪ ተአምራት ለማድረግ ሲል ወደ ኋላ አልቀረም፤ ወደ ሌሎች መንደሮችም እንዲሄድ መንፈስ ገፋፋው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ኃይል አስቀድሞ አይታወቅም፡፡ ወንጌል ገበሬው ተኝቶ ሳለ እንኳ አንዴ ከተዘራ በኋላ በራሱ ስለሚያድግ ዘር ይናገራል (ማር.4፡26-29)፡፡ ቤተክርስቲያንም ከእኛ ግምትና አስተሳሰብ በላይ በሆኑ መንገዶች የፈለገውን ማድረግ የሚችለውን የዚህን ቃል ፍጹም ነጻነት አውቃ መቀበል አለባት፡፡

ቤተክርስቲያን ለኢየሱስ ያላት ቅርበት የጋራ ጉዞ አካል ነው፤ ‹‹አንድነትና ተልእኮ በመሠረቱ እርስ በርስ የተቆራኙ ናቸውና››[1]፡፡ የጌታዋን አብነት በታማኝነት በመከተል ቤተክርስቲያን ዛሬ ሄዳ ወንጌልን ለሁሉ፣ በሁሉ ቦታ፣ በሁሉም አጋጣሚ፣ ያለ ማመንታት፣ ያለ ማወላወል ወይም ያለ ፍርሃት መስበክ እጅግ ያስፈልጋታል፡፡ የወንጌል ደስታ ለሁሉም ሕዝብ ነው፤ ከእርሱ የሚቀር ማንም የለም፡፡ ‹‹አትፍሩ፣ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ›› (ሉቃ.2፡10) በማለት መልአኩ ለቤተልሔም እረኞች የተናገረው ይህንን ነው፡፡ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ‹‹በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ ስለሚሰበከው የዘላለም ወንጌል›› (ራእይ.14፡6) ይናገራል፡፡

 

እርምጃ መውሰድ፣ መሳተፍ፣ መደገፍ፣  ፍሬ ማፍራትና ሐሤት ማድረግ

‹‹ወደ ፊት የምትራመድ›› ቤተክርስቲያን የመጀመሪያ እርምጃ የሚወስዱ፣ የሚሳተፉና የሚደግፉ፣ ፍሬ የሚያፈሩና ሐሤት የሚያደርጉ የወንጌል ልዑካን ማኅበር ናት፡፡ ወንጌልን የምትሰብክ ማኅበር ጌታ ተነሣሽነቱን እንደወሰደ አስቀድሞ እንደወደደን (ንጽ.1ዮሐ.4፡19)፣ እኛም ወደ ፊት መራመድ፣ በድፍረት መነሣሣት፣ ወደ ሌሎች ዘንድ መሄድ፣ የወደቁትን መፈለግ፣ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መቆምና የተጠሉትን በደስታ መቀበል እንደምንችል ታውቃለች፡፡ ይህች ማኅበር ምሕረት የማድረግ የማያቋርጥ ፍላጎት አላት፤ ይህም ከራስዋ ተሞክሮ የምታውቀው ከአብ የማያልቅ የምሕረት ኃይል የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያ እርምጃ ለመራመድና ተሳታፊ ለመሆን ተጨማሪ ጥረት እናድርግ፡፡ ኢየሱስ የደቀመዛሙርቱን እግሮች አጠበ፡፡ ጌታ እግራቸውን ለማጠብ በተንበረከከ ጊዜ ራሱን አሳተፈ፣ የራሱ የሆኑትንም አሳተፈ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ሲናገር ‹‹ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ›› (ዮሐ.13፡17) አላቸው፡፡ ወንጌልን የምትሰብክ ማኅበር በቃልም በሥራም በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ትሳተፋለች፣ መራራቅን ታስወግዳለች፣ አስፈላጊ ከሆነ ራስዋን ዝቅ ለማድረግ ዝግጁ ናት፣ የሰውን ሕይወት ትቀበላለች፤ በሌሎች ውስጥ የክርስቶስን ቁስል ትዳስሳለች፡፡ ስለዚህ፣ የወንጌል ሰባኪያን ‹‹የበጎችን ሽታ›› ያሸታሉ፣ በጎቹም ድምጻቸውን መስማት ይወዳሉ፡፡

የሰባኪያን ማኅበር ደጋፊም ናት፤ ምንም ያህል ከባድ ወይም ሩቅ ቢሆን፣ በመንገድ ላይ ከሕዝቡ ጎን ትቆማለች፡፡ ወንጌልን መስበክ በአብዛኛው ትዕግሥትንና ለጊዜ መጣበብ ትኩረት አለመስጠትን ያካትታል፡፡ ስለዚህ ለጌታ ጸጋም ታማኝ ናት፣ ፍሬም ታፈራለች፡፡ ጌታ ፍሬያማ እንድትሆን ስለሚፈልግ ወንጌል ሰባኪዋ ማኅበር ምን ጊዜም ስለ ፍሬ ታስባለች፡፡ ሰብሉን ትንከባከባለች እንጂ በእንክርዳዱ አትበሳጭም፡፡ ዘሪው በሰብሉ መካከል እንክርዳዱ ሲበቅል ቢያይ አያጉረመርምም፣ ወይም አይበሳጭም፡፡ ምንም ያህል ጉድለት ቢኖርበት ወይም የተሟላ ባይመስል እንኳ በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ ቃል ሥጋ የሚለብስበትንና የአዲስ ሕይወት ፍሬ የሚያፈራበትን መንገድ ይፈልጋል እንጂ፡፡ ደቀ መዝሙር ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር በመሆን፣ ሰማዕትነትን እስከ መቀበል ድረስ፣ መላ ሕይወቱን ያዘጋጃል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ግቡ ጠላቶችን ለማፍራት ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ተቀባይነት እንዲኖረውና ነጻ የማውጣትና የማደስ ኃይል እንዳለው ለመግለጥ ነው፡፡ በመጨረሻም፣ ወንጌል ሰባኪዋ ማኅበር በደስታ የተሞላች ናት፤ ሁልጊዜ እንዴት እንደምትደሰት ታውቃለች፡፡ በስብከተ ወንጌል ሥራ በየደረጃው በተገኘው አነስተኛ ድል ሁሉ ደስ ይላታል፡፡ በደስታ ወንጌልን መስበክ በሥርዓተ አምልኮ ውስጥ ውበትና መልካም ማድረግ ዕለታዊ ሥራችን አካል ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያን ወንጌልን ትሰብካለች፣ የስብከተ ወንጌል ሥራ አከባበርና በአዲስ መልክ ራስዋን የመስጠት ምንጭ በሆነው በሥርዓተ አምልኮ ውበት አማካይነት እርስዋም ወንጌል ይሰበክላታል።

ምንጭ፡ የወንጌል ደስታ በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ

ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 19-24

 

 

06 May 2021, 11:45