የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የይቅርታ አባት መሆናቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አሊ አጃ የተባለ ታጣቂ ግንቦት 5/2013 ዓ. ም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ላይ የግድያ ሙከራ በፈጸመበት ዕለት አጠገባቸው እንደነበሩ ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት አስታውሰዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሚገኘው በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መካነ መቃብር ስፍራ በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ መገኘታቸው ታውቋል።
ሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመቃወማቸው ምክንያት
የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቅርብ ረዳት እና ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገው በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ድምጽ በማሰማታቸው እና በተለይም ሕዝቦች የሚጫን አምባ ገነናዊ ሥርዓትን በቁርጠኝነት በመቃወማቸው ምክንያት መሆኑን አስረተው፣ ይህም በጊዜው በመንግሥት ስልጣን ላይ ለተቀመጡት መሪዎች ምቾትን የማይሰጥ መሆኑን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመሪነት ለማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ አንስተው በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ግፍ እና ጭቆና እንዲያበቃ ድምጽ ሲያሰሙ መቆየታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው አስታውሰው፣ በቅዱስነታቸው ትውልድ አገር ፖላንድም በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዘረጋው የናዚ እና ኮሚኒስት ሥርዓቶችም በዜጎች ላይ ከፍተኛ ስቃይ ሲያደርሱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ሥርዓቱ አምባ ገነናዊ፣ የግለሰቦችን ነጻነት እና ማሕበራዊ ጥቅምን የሚቃረን መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወቅቱ በሚገባ መገንዘባቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ቅዱስነታቸው በየጊዜ በሚያስተላለፉት መልዕክታቸው የሰው ልጅ መብት እንዲከበር መጠየቃቸውን፣ ይህም ከፍተኛ መስዋዕትነትን ቢያስከፍላቸውም ከተልዕኮዋቸው ያገዳቸው አለመሆኑን አስረድተዋል።
ለእመቤታችን ማርያም አደራ መስጠት
የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ሊተርፉ የቻሉት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእናትነት ዕርዳታ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ግንቦት 5 ቀን በሚከበር የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓልን ባለ ማቋረጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲያከብሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በግድያ ሙከራ ወቅት ከፍተኛ የሕመም ስቃይ ቢሰማቸውም፣ ጥቃቱን ላደረሱት በሙሉ ይቅርታን በማድረግ የደህንነታቸው ዋስትናን ለእግዚአብሔር አብ እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃ አደራ መስጠታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው አክለው አስታውሰዋል።
ለሚያሰቃዩት ይቅርታን ማድረግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ በ1983 ዓ. ም. በተከበረው የብርሃነ ልደቱ በዓል ወቅት በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ለሚገኝ አሊ አጃ የተባለን ወንጀለኛ በጎበኙበት ወቅት ይቅርታ ማድረጋቸውን ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው አስታውሰው፣ ከወንጀለኛው ጋር አጭር ቆይታን በማድረግ መነጋገራቸውንም አስታውሰዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጠላቶች አመጽ ቢያስነሱም ያልተሳካላቸው መሆኑን ገልጸው ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ተልዕኮዋቸውን የጀመሩት እስከ መጨረሻው ረዳታቸው እና ጠባቂያቸው ለሆነው እግዚአብሔር አደራ በመስጠታቸው መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ስታኒስሎው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መካነ መቃብር ዙሪያ ካሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በኋላ ወደ አደባባዩ ወርደው የግድያ ሙከራ በተፈጸመበት ሥፍራ አበባ በማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱን ደምድመዋል።