ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የሕጻናት ተስፍ በፍኖተ መስቀል ጸሎት ማዕከል ውስጥ ይገኛል ማለታቸው ተገለጸ!

የጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ያካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት ወቅት የዐብይ ጾም መገባደጃ ላይ በሚገኘው የሕማማት ሳምንት ላይ ሲሆን በመጋቢት 24/2013 ዓ.ም ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራውን የተቀበለበት፣ የተገረፈበት እና ተስቅሎ የሞተበት የስቅለተ ዓርብ ቀን ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ስቅለተ አርብ የንስሐ ፣ የጾም ፣ የጸሎት ቀን ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት እና በስርዓተ አምልኮ በሚደረጉ ጸሎቶች ፣ ቤዛ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን  ሥቃይ እና ሞት ለማስታወስ እኛም ብንሆን በቀራንዮ እንደሆንን አድርገን እንሰበስባለን። በአምልኮ ሥርዓቱ ከፍተኛነት ፣ በስርዓተ አምልኮ አከባበር በኩል ፣ በመስቀሉ እንድናመልከው ቀርቦልናል። ክቡር የሆነውን መስቀሉን በምናከብርበት ወቅት ለድነታችን የተሰዋውን ንጹዕ የሆነውን በግ ጉዞ በሕይወት እንኖራለን ፡፡ እኛ የታመሙትን ፣ ድሆችን ፣ በእዚህ ዓለም ውስጥ የተጣሉትን የሚሰቃዩ ሰዎችን በአእምሯችን እና በልባችን ውስጥ እንሸከማለን ፣ “የተሠውትን በጎች” ፣ በጦርነት ፣ በአምባገነናዊ አገዛዞች ፣ በዕለት ተዕለት ዓመፅ ፣ ፅንስ በማስወረድ ሰላባ የሆኑ ንፁሃን ሰዎችን እናስባለን።  በተሰቀለው የእግዚአብሔር አምሳል ፊት እኛ በኛ ውስጥ የተሰቀሉትን ብዙዎችን በጸሎት እናስታውሳቸውለን፣ በመከራቸው ውስጥ መጽናናትን እና ትርጉምን የሚቀበሉት በእርሱ ብቻ ነው፣ እናም በአሁኑ ጊዜ በዘመናችን እነዚህን የመሰሉ ብዙዎች አሉ ፣ በዘመናችን እየተሰቀሉ የሚገኙ ሰዎችን መርሳት አይገባንም፣ እነሱም የተሰቀለው የኢየሱስ አምሳል ናቸው፣ እናም ኢየሱስ በውስጣቸው እንዳለ ልናምን ይገባል። 

ይህ የስቅለተ ዓርብ ቀን በመጋቢት 24/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመስቀል መንገድ ጸሎት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን የሕጻናት ልጆች ተስፋ ማዕከሉን ያደርገው በመስቀል መንገድ ጽሎት ውስጥ ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ አመት የመስቀል መንገድ ጸሎት የተካሄደው ቀድም ሲል እንደ ተጠቀሰው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም እየተከሰተ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ይህንን ታላቅ የጸሎት ምሽት የታደሙት በቁጥር አንስተኛ የሆኑ ምዕመናን እንደ ነበሩም ተገልጿል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ብቸኝነት እና መገለል፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከወዳጆቻቸው ጋር የተቆራረጡ ሰዎች፣ ሥራቸውን እና ኑሯቸውን የተነፈጉ ፣ ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው እርግጠኛ ያልሆነ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸው እየኖሩ የሚገኙ ሰዎች “የመስቀል መንገድ ጸሎት” ወሳኝ እና ተስፋ ፈንጣቂ እንደ ሆነም ተገልጿል።

በተከታታይ ለሁለት ዓመታት ያህል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የጣሊያን መንግሥት ባስቀመጠው እገዳ ምክንያት ባዶ በሆነው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእየዓመቱ በዓብይ ጾም ወቅት ዘወትር ዓርብ እለት የሚደርገውን የመስቀል መንገድ ጽሎት ከጥቂት ምዕመናን ጋር ብቻ ጋር ሆነው ለመጸለይ ተገደዋል።

በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ፊት ለፊት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከጥቂት ልጆች እና ወላጆቻቸው፣ ካታኪስቶች እና መምህራን በተገኙበት በጋራ በመሆን ነበር የጸሎት ስነስርዓቱን ያከናወኑት።

በስፍራው የተገኙ ጥቂ ምዕመናን በጨለማ በተዋጠው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ መስቀሉን በየተራ ይዘው እና ችቦ ለኩሰው የመስቀል መንገድ ጸሎቱን ማከናወናቸው ተገልጿል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በእውነቱ በዚህ ዓመት ለህፃናት እና ለወጣቶች የተስፋ እና የወደፊት መልካም ምልክቶችን የሚያንጸባርቁ የመስቀል መንገድ ጸሎት አስተንትኖ እንዲደረግ መወሰናቸው ይታወሳል።

የፍኖተ መስቀል ጸሎት

“ፍኖተ መስቀል ወይም የመስቀል መንገድ” ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል ተሰቅሎ ለመሞት መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ያደረገውን የጭንቅ መንገድ የሚያሳስብ ጸሎት ነው። በዚህ ጸሎት ውስጥ ምእመናን ብዙ የነፍስ ጥቅም ያገኙበታል፤ ሙሉ ሥርየት ኃጢአት የሚገኝበት ጸሎት ነው። በ14ቱ ምስሎች ላይ የተመለከቱትን የኢየሱስ ክርሰቶስን ሕማማትና የደረሰበትን መከራና ጭንቅ በማሰብ እያዘኑ ካንዱ ምስል ወዳንዱ ምስል እየተዘዋወሩ የሚያደርጉት ጸሎት ነው።

02 April 2021, 11:05