ፈልግ

በኢንዶኔዢያ የተከስተው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በኢንዶኔዢያ የተከስተው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኢንዶኔዥያና በምስራቅ ቲሞር በጎርፍ ለተጎዱ ሰዎች ጸሎት እንደ ሚያደርጉ ገለጹ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ እና በምስራቅ ቲሞር የሚገኙ የደሴቶችን ስብስብ ያጥለቀለቀ አውዳሚ የጎርፍ አደጋ እና የመሬት መንሸራተት ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ጸሎት እያደረጉ እንደ ሆነ ተግልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ረቡዕ ዕለት መጋቢት 29/2013 ዓ.ም ባደረጉት ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማብቂያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት “ባለፉት ቀናት በኢንዶኔዥያ እና በምስራቅ ቲሞር በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን በጸሎቴ እንደ ማስባቸው ለማረጋገጥ እወዳለሁ” ብለዋል።

ሴሮጃ በመባል በሚታወቅ አውሎ ነፋስ በተነሳው የጎርፍ አደጋ በኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ደሴቶች ላይ ቢያንስ 119 ሰዎችን እንዲሁም በአጎራባች ምስራቅ ቲሞር ደግሞ 27 ሰዎችን ገድሏል። በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ የነፍስ አድን ስራዎችን እያደናቀፈ በመሆኑ አሁንም ብዙ ሰዎች እጣ ፈንታቸው ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደ ሆነ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው ጌታ “የሞቱትን በመንግሥቱ እንዲቀበላቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያጽናና እና ቤት ንብረቶቻቸውን ላጡ ደግሞ እገዛ ይደረግላቸው ዘንድ” ጸሎት እንደ ሚያደርጉ እና የሚመለከታቸው ባለስልጣናት የተቻላቸውን እገዛ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

እሁድ እለት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የፋሲካ በዓል በሚከበርበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ በኢንዶኔዢያ እና በምስራቅ ቲሞር መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን ይህ አደጋ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ፣ ወታደሮች እና ነዋሪዎቹ በደለል ውስጥ የተቀበሩትን በመፈለግ ላይ እንደ ሚገኙ ተገልጿል። በአደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአየር ንብረቱ ባስከተለው ጫና ምክንያት የተፈናቀሉ ሲሆን አውሎ ነፋሱ ወደ ደቡብ አውስትራሊያ ተዛውሮ ቢያንስ እስከ መጪው አርብ ድረስ በእዚህ መልኩ ጉዳት ማድረሱን ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

ስፖርት ለልማት እና ለሰላም

ከእዚህ የተፈጥሮ አደጋ ወጣ ስንል ደግሞ በወቅቱ ማለትም በመጋቢት 29/2013 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልእክት አክለው እንደ ገለጹት በተባበሩት መንግስታት የተቋቋመውን ዓለም አቀፍ የስፖርት፣ የልማት እና የሰላም ቀን ባለፈው ሰኞ በመጋቢት 27/2013 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በተለያዩ ባህሎች እና ህዝቦች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ለማበረታታት ይህ እንደ አንድ የስፖርት ክስተት፣ የስፖርት ልምዶችን እንደገና በእንቅስቃሴ ሊጀምር ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ እናም በዚያ እይታ “የቫቲካን አትሌቲክስ በስፖርቱ ዓለም ውስጥ ወንድማዊ ባህልን ለማዳረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉ በደስታ አበረታታለሁ፣ በዚህም አቅመ ደካሞች ላይ ትኩረት በማድረግ የሰላም ምስክሮች ይሆናሉ የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

ቅድስት መንበር በኢጣሊያን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተቀባይነት ካገኘች በኋላ ኦፊሴላዊውን የአትሌቲክስ ቡድን እ.አ.አ በጥር 2019 ዓ.ም መቀላቀሏ ይታወሳል። የአትሌቶቹ ቡድን መነኮሳት ፣ ካህናት ፣ በቅድስት መንበር የስዊዝ የክቡር ዘበኛ አባላት፣ የሙዚየም ሠራተኞች ፣ አናጢዎች እና የጥገና ሠራተኞችን ያጠቃልላል።

07 April 2021, 11:01