ፈልግ

ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በመሻገር ላይ በነበሩበት ወቅት ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በመሻገር ላይ በነበሩበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በባሕር ላይ ሆነው የእርዳታ ጥሪ የሚያቀርቡ ሰዎች ርዳታ ሊነፈጋቸው አይገባም አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 17/2013 ዓ.ም ከቫቲካን ሆነው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ እና “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የተሰኘውን የማርያም ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ ለዓለም ባስተላለፉት መልእክት በቅርቡ ከሊቢያ ተነስተው ወደ ጣሊያን በባሕር ላይ በመጓዝ በነበሩበት ወቅት በጀልባቸው ላይ በደረሰው አደጋ ሰምጠው የሞቱ ሰዎችን በጸሎት ያስታወሱ ሲሆን በባሕር ላይ በጀልባ የሚጓዙ ስደተኞች በፍጹም እርዳታ ሊነፈጋቸው አይገባም ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብርቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን ሲቀጥሉ “ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ባለፈው አርብ ጓቲማላ ውስጥ በሳንታ ክሩዝ ደ ኪቼ ውስጥ ሆሴ ማሪያ ግራን ሲሬራ እና ዘጠኝ ሰማዕት አጋሮቹ የብጽዕና ማረግ እንደ ተሰጣቸው” ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን ከእነዚህ መሃል ሶስት ካህናት እና ሰባት ምዕመናን የኢየሱስ ቅዱስ ልብ የወንጌል ሰባኪዎች ማሕበር አባላት የሆኑ ድሆችን ለመከላከል ቆርጠው በመነሳታቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደ ቻሉ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።  

በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ በነበረው ከፍተኛ ስደት ምክንያት እ.አ.አ ከ1980 እስከ 1991 ዓ.ም ባሉት ዓመታት መካከል የተገደሉ ሰማዕታት እንደ ነበሩም አክለው ገልጸዋል። በክርስቶስ ሕያው እምነት ፣ የፍትህና የፍቅር ጀግኖች ምስክሮች ነበሩ። የእነሱ ምሳሌ በወንጌል ለመኖር የበለጠ ለጋስ እና ደፋር እንድንሆን ያደርገናል ብለዋል።

የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት ጉዳት እና ችግር ላይ የወደቁትን የቅዱስ ቪንሰንት ደሴቶች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች  ለእነርሱ ጸሎቴን የማቀርብ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህን ሕዝቦች ለመርዳት ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ሰዎችን በሙሉ ቡራኬዬ ይድረሳችሁ ብለዋል።

በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን በማከም ላይ በሚገኘው ሆስፒታል ውስጥ በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት የእዚህ አደጋ ሰለባዎ ለሆኑ ሰዎች በጸሎት አስባለሁ በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው እስከ አሁን ድረስ በእዚህ የእሳት አደጋ የሞቱ 82 ሰዎች መሆናቸውን ገልጸው ሁላችንም ስለሁሉም ሰዎች ነፍስ እንጸልይ ብለዋል።

በድጋሜ በሜድትራንያን ባህር ውስጥ በደረሰው የጀልባ መገልበጥ አደጋ ሕይወታቸው ባለፈው በርካታ ስደተኞች እጅግ እንዳዘንኩ መናገር እፈልጋለሁ ያሉት ቅዱስነታቸው በአደጋው አንድ መቶ ሠላሳ ስደተኞች  መሞታቸውን ገልጸው እነሱም የሰው ልጅ ናቸው ለሁለት ቀናት ሙሉ የድረሱልን የእርዳታ ጥሪ እያቀረቡ ነበሩ፣ ነገር ግን ማንም እርዳታ ሊያቀርብላቸው ባለመቻሉ ሕይወታቸው በባሕር ውስጥ ሰለባ ሆኗል ብለዋል። ወንድሞች እና እህቶች ሁላችንም ስለዚህ አስከፊ አደጋ እራሳችንን እንጠይቅ፣ በጣም አሳፋሪ የሆነ ነገር ነው የተፈጸመው፣ አሳፋሪ ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለዋል። ለእነዚህ ወንድሞች እና እህቶች፣ በእነዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ባሕር አቋርጠው ወደ አውሮፓ አህጉር ለመግባት ለሚሞክሩ ሰዎች ሁሉ እንጸልይላቸው ብለዋል። በተጨማሪም እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች ለመርዳት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች እንጸልይ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የእለቱን መልእክት አጠናቀዋል።

25 April 2021, 10:47