ፈልግ

እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ 

እህት አሌሳንድራ፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የሰው ልጅ ዕድገት ቢሮ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሳሊዥያን፣ ዶን ቦስኮ ደናግል ማኅበር አባል የሆኑትን እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ለእምነት እና ልማት ዘርፍ ዋና ጸሐፊ አድርገው መሰየማቸው ታውቋል። ለዚህ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊነት የተሾሙት እህት አሌሳንድራ፣ የምጣኔ ሃብት ባለ ሞያ ሲሆኑ፣ በአገልግሎታቸው መካከል ቅዱስ ወንጌልን እና የምጣኔ ሀብትን የማጣመር አስፈላጊነትን በመግለጽ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከደረሰብን ቀውስ ለመውጣት ቅድስት መንበር አፅንዖትን በመስጠት እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እህት አሌሳንድራ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ አዲስ በተቋቋመው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ በመሆን በተባባሪነት የሚሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያላቸውን የሥራ ተልዕኮን እንደወደዱት እና ወደ መላው ዓለም ሊደርስ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህ የሥራ ሃላፊነት የጠሯቸውን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አመስግነው፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሐላፊ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን እና ሌሎች የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እህት አሌሳንድራ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እስካሁን ከትምህርት ዕኣለም የቀሰሙት ዕውቀት በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ለሚያበረክቱት አገልግሎት የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም በእምነት እና ልማት ክፍል ውስጥ ለየአገራቱ አብያተ ክርስቲያናት የሚቀርቡ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ውጤታማ ለማድረግ ቅዱስ ወንጌልን እና የምጣኔ ሀብትን ለማጣመር ከተቀሩት የጽሕፈት ቤቱ ሰራተኞች ጋር በኅብረት የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሥራቸውን በሚያካሂዱበት አዲስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ቢሮ ውስጥ ያገኟቸው ትንታኔዎች እና ሀሳቦች በተግባር በሚብራሩበት ጊዜ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ በመልካም መንገድ ለመውጣት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። የመጀመሪያው እና ዋንው የየአገራትን ተጨባጭ ሁኔታ እና በዚህ ቀውስ ምክንያት የሚከሰቱትን ችግሮች፣ በተለይም ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑትን ፣ ድሆችን እና ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን ሰዎችን በቅርበት ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ እህት አሌሳንድራ ተናግረዋል።እንደ ቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅብን መደማመጥ እና አንዱ ሌላውን መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ሰዎችን ፣ የተለያዩ ተቋማትን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቅረብ ውይይት የማድረግ ችሎታ ሊኖር ያስፈልጋል ብለዋል። ዓለምን በአንድ ዓይን ብቻ ማየት አንችልም ያሉት እህት አሌሳንድራ፣ መተባበር ማለት ከሁሉም በፊት በእውነታው ላይ ብዙ ቁጥር ያላቸው እይታዎችን ማካተት ያስፈልጋል ብለዋል።

እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፣ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ስለሆነም ይህ ማለት ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር ምሳሌ ናቸው፣ የቃል ኪዳን እና የመተጋገዝ ጥሪ በቤተሰብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕይወት ዘርፎች፣ በሥራ ቦታም ቢሆን መከናወን አለበት። በቅድስት መንበር ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ጽሕፈት ቤቶችም የአምላካችንን የብልጽግና የዕድገት እቅዶችን በተሻለ ሁኔታ ለመግለጽ ተደጋጋፊነት ሊኖር እንድሚገባ አምናለሁ በማለት እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

25 March 2021, 15:43