ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ኤርቢል ፣ ሞሱል እና ቃራቆሽ የሚባሉ የኢራቅ ከተሞችን ጎበኙ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም ደረስ 33ኛውን ሐዋርያዊ ግጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢራቅ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በእዚያው የነበራቸውን የሶስተኛውን ቀን ጉብኝት በየካቲት 28/2013 ዓ.ም ሲጀምሩ ወደ ኤርቢል በመጓዝ ሲሆን በእዚያው ከኢራቅ ኩርዲስታን ራስ ገዝ ክልል ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የተገናኙ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእዚያው ተመሳሳይ ቀን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሞሱል እና ቃራቆሽ የተባሉትን የኢርቅ ከተሞችን እንደ ሚያካትት ተገልጿል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
እሁድ የካቲት 28/2013 ዓ.ም በኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሶስተኛውን ቀን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የጀመሩት ከባግዳድ ወደ ኤርቢል በመብረር እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን እዚያም ኤርቢል ሲደርሱም የኢራቅ ኩርዲስታን ግዛት አስተናዳሪ በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር እና እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፣ በተጨማሪም የሲቪል እና የተለያዩ የሐይማኖት መሪዎች በስፍራው ተገኝተው ለቅዱስነታቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል ከኢራቅ ኩርዲስታን የራስ ገዝ ክልል ፕሬዝዳንት ከሆኑት ከነሺርቫን ባርዛኒ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መስሮር ባርዛኒ ጋር በአሮፕላን ጣቢያው ውስጥ በሚገኘው ፕሬዝዳንታዊ የቪአይፒ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወስጥ ተገኝተው መወያየታቸው ተገልጿል።
ከእዚያም በመቀጠል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሞሱልን ለመጎብኘት ቀጠሮ የተያዙ ሱሆን በጦርነቱ ለተጎዱት እና ከፍተኛ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር የሚገናኙ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በሆሹ አል ቢያአ (የቤተክርስቲያን አደባባይ) ላይ ጸሎት ያደርጋሉ። ከዚያ ወደ ቃራቆሽ በመሄድ የቃራቆሽ ማኅበረሰብ የሚጎበኙ ሲሆን በእዚያም “ያለ አዳም ኃጢአት የተጸነሰች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” ቤተክርስቲያን ውስጥ ከምዕመኑ ጋር ይገናኛሉ። ከዚያ በኋላ ወደ ኤርቢል የሚመለሱ ሲሆን ቅዱስ አባታችን በኤርቢል በሚገኘው “ፍራንሶ ሀሪሪ” ስታዲየም መስዋዕተ ቅዳሴ ያሳርጋሉ፣ ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ስብከት ያሰማሉ። ከዚያም አመሻሹ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ ባግዳድ ይመለሳሉ።
የኤርቢል ከተማ
በአረብኛ እና በኩርድኛ ቋንቋዎች አርቡል በመባልም የሚታወቀው ኤርቢል ዋና ከተማ እና የኢራቅ ኩርዲስታን የራስ ገዝ ክልል ትልቁ ከተማ ናት። ይህ ቦታ ከሞሱል በስተ ምሥራቅ 88 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሶሪያ ድንበር ከ 300 ኪ.ሜ ያህል ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት።
በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ እንደሆነች የሚታሰብው ኤርብል ከተማዋ በመጀመሪያ የተቆረቆረችው ከክርስቶስ ልደት በፊት 2300 ዓመት በፊት እንደ ነበረ ከታሪክ ለመረዳት ይቻላል። ባለፉት ክፍለ ዘመናት የሰማራዊያን፣ አሦራውያን ፣ ባቢሎናውያን ፣ ሜዶኖችን ፣ ሮማውያንን፣ አባሲድስን እና ኦቶማን ጨምሮ ብዙ ሕዝቦች በዚህች ጥንታዊት ከተማ ግንብ ውስጥ ይኖሩ ነበር።
ታዋቂው የኤርቢል ግንብ እ.አ.አ በ 2014 ዓ.ም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን ወደ 110,000 ካሬ ሜትር አካባቢ ይሸፍናል፣ እናም ከቅርብ አከባቢው 30 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው። በውስጡ ታላቁ መስጊድ እና የኩርድ የጨርቃጨርቅ ሙዚየም ይገኛል። የከተማዋ ጉልህ መዘክሮች - የኤርቢል ስልጣኔ ሙዚየም እና የሲሪያክ ቅርስ ሙዚየም - ከአከባቢው የመጡ በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ።
ሌሎች በኤርቢል ውስጥ ትኩረት የሚሹ ቦታዎች በ 12 ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውን እና የጥንት መስጊድ ቀሪ አካል ነው ተብሎ የሚታሰበው ሙዳፋሪያ ሚናሬት (ቾሊ ሚናሬት) ይገኙበታል። የጃሊል ካያት መስጊድ - በከተማ ውስጥ ትልቁ መስጊድ ሲሆን ግንባታው እ.አ.አ በ 2007 ዓ.ም የተጠናቀቀው ፣ የሚናሬት እና የሻንዳር ቤተ መዘክሮች የሚገኙበት ስፍራ ነው። በተጨማሪም የ 12 ኛው ክፍለ ዘመን የቄሳሪ ባዛር እንዲሁም የሚናሬ ፣ የሻንዳር እና የሳሚ አብዱልራህማን የመናፈሻ ስፍራዎች የገኙበታል።
በተጨማሪም በኤርቢል የሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ አንካዋ የከለዳውያን ካቴድራል በእዚያ ስፍራ የሚገኝ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ ካሉት ትላልቅ የክርስቲያን አከባቢዎች መካከል አንዱ የኒዎ-አራማይክ ቋንቋዎችን የሚናገሩ በዋነኝነት የአሦራውያን ክርስቲያኖችን ያቀፈ ስፍራ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኤርቢል እስላማዊ መንግስት እየተባለ በሚጠራው አገዛዝ ወቅት ህይወታቸውን ለማትረፍ የተሰደዱ በአብዛኛው ከቃራቆሽ እና ሞሱል የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መኖሪያ ሆኗል። ከተማዋ ከሌሎች የሶሪያ ስደተኞች በተጨማሪ በግምት ወደ 540,000 የሚሆኑ ኢራቃዊያን ስደተኞችን በክልሉ በሚገኙ የስደተኛ መጠሊያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደ ሚገኙም ተገልጿል።
የኢራቅ ኩርዲስታን የራስ ገዝ ክልል
በሰሜን ምስራቅ የሚገኘው የኢራቅ ኩርዲስታን የራስ ገዝ ክልል እ.አ.አ. በ 2005 ዓ.ም ህገ-መንግስት ካጸደቁ በኋላ በይፋ እውቅና የተሰጠው በአራት የዶሁክ (ዲሆክ) ግዛቶች ፣ ኤርቢል (ሄውልል) ፣ ሀላብጃ (ሄልብቼ) እና ሱለይማንያህ ( ሲሊማኒ) ክልሎችን ያቀፈ የራስ ገዝ ክልል በምስራቅ ከኢራን ፣ በሰሜን ከቱርክ እና በምዕራብ ከሶሪያ ጋር ትዋሰናለች።