ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለኢራቅ ቀሳውስት ዓመፅ እና ጥላቻ ከሃይማኖት ጋር የማይጣጣሙ ነገሮች ናቸው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም 33ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማደረግ ወደ ኢራቅ በየካቲት 26/2013 ዓ.ም ጉዞ መጀመራቸው ይታወቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሰባት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ከጣሊያን ውጭ አሁን በኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጨምሮ 33 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደ ደረሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አቀባበል እንደ አደረጉላቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 14፡10 በባግዳድ አየር ማረፊያ የቪአይፒ አዳራሽ ውስጥ ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን በሮም የሰዓት አቆጣጠር 15፡00 ላይ ይፋዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ሥነ ስርዓት በባግዳድ በፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግስት ውስጥ ተከናውኗል።

በመቀጠልም በሮም የሰዓት አቆጣጠር 15፡15 ላይ በባግዳድ በሚገኘው የኢራቅ ሪፖብሊክ በፕሬዝዳንታዊው የግል ቢሮ ውስጥ ከሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን በሮም የሰዓት አቆጣጠር 15:45 በባግዳድ ውስጥ በፕሬዝዳንታዊው አዳራሽ ውስጥ ከባለስልጣናት ፣ ከሲቪል ማኅበራት እና ከዲፕሎማቲክ አካላት ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ቅዱስነታቸው ተካፍለው ባደረጉት ንግግር የኢራቅ ባለሥልጣናት በወንድማማች አንድነት ላይ ህብረተሰቡ እንዲገነባ የራሳቸውን ጥረት ያደርጉ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።

በመቀጠልም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሮም ሰዓት አቆጣጠር 16፡ 40 ላይ በኢራቅ ከሚገኙ ብጽዕን ጳጳሳት፣ ከካህናት ፣ ከገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ ከዘረዓ ክህነት ተማሪዎች፣ ካታኪስቶች ጋር “የመዳኛ እመቤታችን” ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል  በሚባለው ቤተክርስቲያን ውስጥ ተገናኝተው የነበረ ሲሆን ቀሳውስት ዓመፅ እና ጥላቻ ከሃይማኖት ጋር የማይጣጣሙ ነገሮች መሆናቸውን ተገንዝበው በኢራቅ ሰላምን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ተሳተፊ ይሆኑ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባግዳድ በሚገኘው የመዳን የእመቤታችን ካቴድራል ውስጥ ከጳጳሳት ፣ ቀሳውስት እና የሃይማኖት አባቶች ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የእርቅን ዘር መዝራት ሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል በተስፋ ዳግም እንዲወለድ ሊያደርግ እንደ ሚችል የተናገሩ ሲሆን የወንድማማችነት መንፈስ በመገንባት አብሮ የመኖር አስፈላጊነትን አስገንዝበዋል።

እ.ኤ.አ በ 2010 ዓ.ም በባግዳድ ውስጥ በሚገኘው የመዳኛ እመቤታችን የሲሮ-ካቶሊክ ካቴድራል ውስጥ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት ሴቶችን እና ህፃናትን ጨምሮ 48 ምዕመናንና ሁለት ወጣት ካህናት መገደላቸው ይታወሳል። ያ ዘግናኝ ክስተት ከተፈጸመ ከአስር ዓመት በላይ ከሆነው በኋላ ነበር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ ቀን አርብ ወደዚህ አምልኮ ስፍራ የሄዱት ።

እዚያም ከጳጳሳት ፣ ቀሳውስት ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ ገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ የዘረዐ ክህነት ተማሪዎች፣ ካቴክስቶች እና የምዕመናን ተወካዮች ጋር የተገናኙ ሲሆን “እዚህ የመዳኛ እመቤታችን ካቴድራል ውስጥ መሰብሰባችን እዚህ የታማኝነታቸውን የመጨረሻ ዋጋ በከፈሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደም ተቀድሰናል” ብለዋል።

የተስፋ መቁረጥ ቫይረስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በስብሰባው ላይ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት የዕለት ተዕለት ተግዳሮቶች ሲያጋጥሟቸው ሐዋርያዊ አገልግሎቶቻቸውን በጭራሽ እንዳያቋርጡ የተናገሩ ሲሆን በተለይም ይህ ወረርሽኝ በተከሰተበት በእዚህ ወቅት ምንም ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ መግባት እንደ ሌለባቸው ቅዱስነታቸው አበክረው ገልጸዋል።

“አንዳንድ ጊዜ በዙሪያችን የሚዛመት በሚመስለው በተስፋ መቁረጥ ቫይረስ መበከል ምን ያህል ቀላል እንደሆነ እናውቃለን፣ ሆኖም ጌታ ከዚያ መጥፎ ቫይረስ ጋር ውጤታማ የሆነ ክትባት ሰጥቶናል። በጽናት በጸሎት እና በየቀኑ ከሐዋሪያዊ ተግባራችን ታማኝነት የተወለደ ተስፋ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል በዚህ ክትባት “እኛ ሚስዮናዊ ደቀመዛሙርት የሆንን የወንጌልን ደስታ እና የእግዚአብሔር የቅድስና፣ የፍትህ እና የሰላም መንግሥት መኖር ሕያው ምልክቶች በመሆናችን በታደሰ ኃይል ልንወጣ እንችላለን” ብለዋል።

በችግር መካከል ጽናት

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በርካታ ኢራቃውያን አማኞች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በንግግራቸው አጉልተው ገልጸዋል። ስለ ጦርነት እና ስደት ውጤቶች ፣ ስለ መሰረታዊ መሰረተ ልማቶች ደካማነት እና ቀጣይነት ያለው ውስጣዊ መፈናቀሎች እና ክርስትያኖችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ወደ ሌሎች የአለም ክፍሎች እንዲሰደዱ ምክንያት የሆነው ቀጣይ የኢኮኖሚ እና የግል ደህንነት ችግሮች ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም “ወንድሞቻቸው የሆኑት ጳጳሳት እና ካህናት” ለህዝባቸው ቅርብ በመሆናቸው አመስግነዋል። እናም የኢራቅ የካቶሊክ ማህበረሰብ ምንም እንኳን የሰናፍጭ ዘር ቢመስልም በአጠቃላይ የህብረተሰቡን ህይወት ማበልፀጉን እንዲቀጥል በእነዚህ ጥረቶች እንዲፀኑ አበረታቷቸዋል ፡፡

ወንድማዊ አንድነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የክርስቶስ ፍቅር እያንዳንዱን የራስ ወዳድነት ስሜት ወይም ፉክክር ወደ ጎን እንድንተው ይጠራናል፣ ወደ ሁለንተናዊ ኅብረት እንድንሄድ ያስገድደናል እንዲሁም እርስ በርሳችን የምንቀባበል እና የሚተሳሰቡ ወንድሞች እና እህቶች ማኅበረሰብ ለመመስረት ይገፋፋናል ብለዋል።

“ብዙውን ጊዜ በተበታተነ እና የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ያለው ይህ የወንድማማች ማኅበር ምስክር ምን ያህል አስፈላጊ ነው” ብለዋል ፡፡ በቤተክርስትያን ፣ በሰበካ እና በሀገረ ስብከት ማህበረሰቦች እና ተቋማት መካከል ድልድዮችን ለመገንባት የተደረገው ጥረት ሁሉ በኢራቅ ውስጥ ባለው ቤተክርስቲያን እንደ ትንቢታዊ ምልክት እና ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ለኢየሱስ ጸሎት ፍሬያማ ምላሽ ይሆናል ብለዋል።

የማይፈቱ ቋጠሮዎች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ወቅት አንዳንድ ጊዜ “አለመግባባቶች ሊፈጠሩ እና የተወሰኑ ውጥረቶች ሊያጋጥሙን ይችላሉ ፤ የወንድማማችነ መንፈስ የተፈተለበት ሽመና የሚያደናቅፉ እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል “እኛ በውስጣችን የምንሸከማቸው ቋጠሮዎች አሉ፣ ደግሞም ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን ፡፡ ሆኖም እነዚህ ቋጠሮዎች በታላቅ ፍቅር በጸጋ ሊፈቱ ይችላሉ ፤ እርስ በእርሳችን በትዕግስት፣ እርስ በእርስ በመሸካከም እና በፈተና እና በችግር ጊዜያት እርስ በእርስ በመበረታታት በይቅርታ መድሃኒት እና በወንድማማችነት መነፈስ በሚደረግ ውይይት ሊፈቱ ይችላሉ” በማለት አክለው ገልጸዋል።

እውነተኛ አባቶች ሁኑ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለወንድሞቻቸው ኤጵስ ቆጶሳት የተመለከተ ባደረጉት ልዩ ንግግር በተለይ ለካህናቶቻቸው ቅርብ እንዲሆኑ አሳስበዋል። “እንደ አስተዳዳሪ ወይም እንደ ሥራ አስኪያጅ ብቻ አድርገው ካህናቶቻችሁ እናንተን እንዲመለከቱ አታድርጉ፣ ነገር ግን እንደ እውነተኛ አባቶች ፣ ለደህንነታቸው የምትጨነቁ፣ በተከፈተ ልብ ድጋፍ እና ማበረታቻ ለመስጠት ዝግጁ” መሆን ይኖርባችኋል ብለዋል።

መንጋዎቻችሁን ተንከባከቡ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ በስፍራው የነበሩ ካህናት ፣ ገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ ካቴክስቶች እና የዘረዐ ክህነት ተማሪዎች ከመንጋው መካከል ወጥተው በተለይም ወደኋላ ቀርተው ለተለያዩ ነገሮች ተጋላጭ የሆኑ እንደ ወጣት ፣ አዛውንቶች ፣ ህመምተኞች እና ድሆች ያሉ ሰዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የጋበዙ ሲሆን እኛ እንደ የመንግስት ሰራተኞች ሳንሆን እንደ እረኞች በመሆን የሕዝብ አገልጋይ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኃይል ጥቃት ሰለባዎች

ከአሥር ዓመታት በፊት በዚህ ካቴድራል በሽብር ጥቃት ለሞቱት እና ለአራት ዓመታት ያህል ይህ ገድላቸው ለቅድስና የሚያበቃቸው እንደ ሆነ ጥናት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ ወደ እነዚያ ወንድሞችና እህቶች እንደገና ሀሳባቸውን በማዞር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አፅንዖት ሰጥተው እንደ ተናገሩት “የእነሱ ሞት ጦርነት መቀስቀስ ፣ የጥላቻ አመለካከቶች ማራመድ ፣ አመጽ ወይም ደም ማፍሰስ ከእውነተኛ የሃይማኖት ትምህርቶች ጋር የማይጣጣም መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

የየትኛውም የሃይማኖት ቡድን ወይም ተቋም ምንም ይሁን ምን የኃይል ጥቃት እና የስደት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ ማስታወስ እና ማገዝ ይኖርብናል ብለዋል።

ሰላም ፈጣሪዎች የተባረኩ ናቸው

በዚህ ሰፊ ካቴድራል ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተሰበሰቡ ሁሉ ሰላም ለመፍጠር ፣ በአካባቢያቸው እና ከሌሎች ሃይማኖት ተቋማት አማኞች ጋር በመሆን “የእርቅን ዘር በመዝራት እና ለሁሉም ተስፋ ወደ ተሃድሶ ሊመራ በሚችል መልኩ በወንድማምችነት መንፈስ  አብሮ መኖር በመቻላቸው” ምስጋና አቅርበዋል ፡፡

በተጨማሪም እርሳቸው “የተስፋ እና የተስፋ ምልክት” ያሏቸውን ወጣቶች በተለይም ለዚህች ሀገር ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጾ ማደረጋቸውን ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

የእግዚአብሔር ተስፋ ምስክሮች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ “ወንድሞች እና እህቶች፣ አዲስ የወደፊት ተስፋን ለመገንባት ስትጥሩ ስለ እግዚአብሔር የማይፈርሱ ተስፋዎች በታማኝነት የሚትመሰክሩ ሰዎች ሁኑ” ማለታቸው ተገልጿል።  አክለውም ምስክርነታችው በልዩነታችሁ ውስጥ ጎልምሶ እና በሰማዕታት ደም ጥንክሮ በኢራቅ እና ከኢራቅ ባሻገር የጌታ ታላቅነትን ለማወጅ እና የዚህ ህዝብ መንፈስ በእግዚአብሔር እንዲደሰት ለማድረግ የእዚህ ጉዳይ "ምስክሮች ሁኑ” ክርስቶስ ሁሌም አዳኝ ነው፣ የሚለውን ሁሌም መስክሩ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በካቴድራሉ ውስጥ ያደረጉትን ንግግር አጠናቀው ከመሄዳቸው በፊት የክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ የሚከተለውን መልእክት አስፍረዋል . . .

“ንስሐ እንደ ሚገባ ሰው እና የኢራቅ የእምነት እና የሰላም ተጓዥ በመሆን ለእነዚህ ሰዎች በድንግል ማርያም አማላጅነት አገሪቱ በወንድማማችነት ማኅበር መንፈስ እንድትገነባ ብርታት እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን እጠይቃለሁ” የሚል ጹሑፍ ካሰፈሩ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ ከሚገኙ ብጽዕን ጳጳሳት፣ ከካህናት ፣ ከገዳማዊያን/ገዳማዊያት ጋር “የመዳኛ እመቤታችን” ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ቤተክርስቲያን ውስጥ በተገናኙበት ወቅት
05 March 2021, 21:48