ፈልግ

ቅዱስ ዮሴፍ ከሕጻኑ ኢየሱስ ጋር ቅዱስ ዮሴፍ ከሕጻኑ ኢየሱስ ጋር 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔር ምልክቶችን የተረዳ ልባም የሆነ አባት ነው” አሉ!

የቤልጂዬም ጳጳሳዊ ኮሌጅ ተወካይ ካህናት በመጋቢት 09/2013 ዓ.ም በቫቲካን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር መገናኘታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት የአባትነትን ጥበብ ለመማር ወደ ማርያም እጮኛ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ መመልከት ይገባል ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህም መሰረት እንደ እግዚአብሔር እቅዶች መንጋውን የመጠበቅ እና አሻግሮ የማየት ችሎታ ያላቸው እረኞች እንድንሆን ቅዱስ ዮሴፍ ያሳስበናል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቅዱስ ዮሴፍ ለካህናት ትልቅ ምሳሌ ነው

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ መጋቢት 09/2013 ዓ.ም በሮማ ከተማ ከሚገኘው የቤልጂየም ጳጳሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ካህናት ተወካዮች በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት እውነተኛ የሆኑ ካህናት በአደራ እንዲከባከቡ የተሰጣቸውን መንጋ መንከባከብ ይችሉ ዘንድ ከቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት መኮረጅ እንደ ሚገባቸው የገለጹ ሲሆን በእዚህም መሰረት ማንኛውም ካህን የቅዱስ ዮሴፍ አባትነት ላይ አስተንትኖ ማደረግ ይኖርበታል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካህናቱ በአደራ የተሰጣቸውን መንጋ መልካም ነገሮችን ብቻ የሚሚመኝ እረኛ በመሆን የአባትነትን ጥበብ ከቅዱስ ዮሴፍ እንዲማሩ አሳስበዋል። በሮም ከተማ ውስጥ ለሚማሩ ከቤልጅየም የመጡ ካህናት ማረፊያ በሆነው የቤልጂየም ጳጳሳዊ ኮሌጅ ልዑካን ሐሙስ ቀን ከቅዱስነታቸው ጋር ተገናኝተው ነበር። የኮሌጁ የ 175 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማደረግ ነበር ካህናቱ ከቅዱስነታቸው ጋር የተገናኙት፣ በእዚህ የቤልጅየም ጳጳሳዊ ኮሌጅ ውስጥ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ ከ 1946 እስከ1948 ዓ.ም ድረስ እንደ ተማሪ ቄስ እዚያ ኮሌጅ ውስጥ ኑረው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው በነግግራቸው አስታውሰዋል።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 10/2013 ዓ.ም በሚከበረው የቅዱስ ዮሴፍ አመታዊ በዓል ዋዜማ ላይ ለካህናቱ ቅዱስነታቸው ባደረጉት ንግግር ቅዱስ ዮሴፍ የቤልጅየም ጳጳሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠብቂ ቅዱስ መሆኑን አስታውሰው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ካህናት የኮሌጃቸው የበላይ ጠባቂ የሆነውን የቅዱስ ዮሴፍ አርአያ መከተል እንደ ሚገባቸው ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።  “እራሳችሁን እና ጥሪዎቻችሁን በእራሱ ከለላ ስር ብታስቀምጡ እና በቅርብ ጊዜ በማህበረሰቦቻችሁ ውስጥ በአደራ በሚሰጣችሁ የአገልግሎትና የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ውስጥ ይህንን ተግባራዊ ማደረግ እንድትለማመዱ የሚረዳችሁን የአባትነት ጥበብ ከእሱ ከቅዱስ ዮሴፍ ለመማር ሞክሩ” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለተወካይ ካህናቱ ተናግረዋል።

ሁሉን በመልካም መንፈስ የሚቀበል አባት ሁኑ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ “በመጀመሪያ ቅዱስ ዮሴፍ ሁሉን ተቀባይ የሆነ አባት ነበር” በማለት ትክክለኛ የግል እቅዶቹን ትቶ ማርያምን እና ኢየሱስን በእምነት እና በፍቅር ተቀበላቸው፣ ከእዚህ ቀደም ሊኖሩት ካቀዱት በጣም በሚለይ የቤተሰብ ሕይወት ራዕይ ውስጥ መኖር እንደ ጀመረ” የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸሶስ በዚህ ረገድ እርሱ በሕይወት ውስጥ የሚከሰተውን ነገር የሚቀበል የመንፈሳዊ ሕይወት እና የማስተዋል ጥበብ የተካነ ሰው መሆን ችሎ ነበር ብለዋል። አንድ ካህን ሀሳቦቹን እና የግል እቅዶቹን በምዕመኑ ላይ ከመጫን ይልቅ ወደ አዲስ ቁምስና ተመድቦ የሚሄድ ካህን በመጀመሪያ ማህበረሰቡን በነፃነት መውደድ አለበት ያሉ ሲሆን ቀስ በቀስ እነሱን በመውደድ እና በፍቅር በመመልከት ምዕመኑን በጥልቀት በማወቅ ሕዝቡን በአዲስ ጎዳናዎች ላይ ይራመዱ ዘንድ ለመርዳት ይችላል ብለዋል።

ተንከባካቢ እና አሳዳጊ አባት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳሉት ቅዱስ ዮሴፍ ተንከባካቢ እና አሳዳጊ አባት የመሆን ጥሪውን እና ተልእኮውን በጥንቃቄ ፣ በትህትና ፣ በዝምታ እና ለእግዚአብሄር እቅዶች በሙሉ ታማኝ በመሆን እንደ ኖረ ቅዱስነታቸው አክለው የገለጹ ሲሆን ስለሆነም በአደራ የተሰጡትን ሰዎች መልካም እና ደስታ ብቻ የሚፈልግ ጥሩ እና ታማኝ አገልጋይ ለመሆን ችሏል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳብራሩት ይህ የዮሴፍ ሞግዚትነት በጥንቃቄ እና በትጋት በልግስና ፣ መቼ መራቅ እና መቼ መቅረብ እንዳለብን ማወቅ ፣ በተጨማሪም ሁል ጊዜ ንቁ ፣ በትኩረት እና በጸሎት የተሞላ ልብን ይጠብቃል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ አንደ እረኛ ካህን ሁል ጊዜ ከመንጋዎቹ ጋር መቀመጥ ይኖርበታል፣ አንዳንድ ጊዜ መንገዱን ለመክፈት ፊት ለፊት መሄድ ይኖርበታል፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመንጋው መካከል በመሆን ማበረታታት ይጠበቅበታል፣ ወይም አንዳንድ ጊዜ ወደ ኋላ የቀሩትን ለመሰብሰብ ከኋላቸው ሆኖ ሊጓዝ ይገባዋል ብለዋል። አንድ ካህን በፍጹም ግትር ሊሆን እንደ ማይገባው በአጽኖት የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ካህን ግትር የሆነ ሰው ሳይሆኑ ነገር ግን ትኩረት የሚሰጥ ሞግዚት፣ ሁኔታዎች በሚፈለጉት ሁኔታ ውስጥ ለመገኘት ዝግጁ የሆነ፣ ሁል ጊዜም የመንጋውን ፍላጎቶች በመረዳት በተቃራኒ የበላይነትን እና ግድየለሽነትን የሚመለከቱ ፈተናዎችን በማስወገድ ሊኖር እንደ ሚገባው ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

“ህልም አላሚ”

ቅዱስ ዮሴፍም ሕልምን የሚያልም አባት ነበር እንጂ በተቃራኒው አእምሮውን በደመናዎች ውስጥ በማስገባት ከእውነታው ርቆ የነበረ አባት አልነበረም በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው በትንቢታዊ እይታ ፣ ዮሴፍ ከሚያየው በላይ ለመመልከት እና የእግዚአብሔርን እቅድ እንዴት እንደሚገነዘብ የሚያውቅ ሰው ነበር ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕፃኑን ኢየሱስ እና እናቱን ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ በመጠበቅ ቅዱስ ዮሴፍ በዝምታ፣ በለጋስነት እና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በድብቅ የእግዚአብሔርን እቅድ እውን ለማድረግ መሣሪያ የሆነ ቅዱስ ነው ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው በልእክታቸውን አጠናቀዋል።

18 March 2021, 16:56