ፈልግ

ካህን ራስን የርኅራሄ ሰው መሆኑን ካህን ራስን የርኅራሄ ሰው መሆኑን  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ካህን ራስን ከፍ የሚያደርግ ሳይሆን የርኅራሄ ሰው መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 20/2013 ዓ. ም. በሮም ከተማ የሚገኝ የሜክሲካዊያን ጳጳሳዊ ኮሌጅ ካህናትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድረገውላቸዋል። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን አስመልክተው ባሰሙት ንግግር፣ ካህን ራስን ከፍ የሚያደርግ ሳይሆን ለሌሎች የሚራራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መሆኑን አስረድተዋል። ካህን በመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በማሸነፍ፣ በችግር ውስጥ የሚገኙትን መርዳት የሚያስችል የእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝበት ልብ እንዲኖረው ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደሚያስብልን ሁሉ ካህንም በአመፅ፣ በኑሮ አለመመጣጠን እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት ማህበረሰባችን ርኅራሄን፣ እርቅን እና ወንድማማችነትን በተግባር የሚገልጽ መሆን እንዳለበት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ርኅራሄ፣ እርቅ እና ወንድማማችነት” በሚሉት ሦስት ቃላት ላይ ትኩረት በማድረግ በሮም ከተማ ለሚገኝ ሜክሲካዊያን ጳጳሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ለበጎቹ የሚጨነቅ መልካም እረኛን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በእያንዳንዱ ካህን ውስጥ ላሉትም ሆነ ለጠፉት በጎቹ የሚጨነቅ እውነተኛ የርኅራሄ ልብ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የቅዱስነታቸው መልዕክት የሰውን ጉድለቶች ለማረም እና ዓለማዊ ፈተናዎችን አቅልሎ ላለመመልከት የሚያግዝ ማሳሰቢያ መሆኑ ታውቋል።

ወረርሽኙ ያስከተላቸው ተግዳሮቶች

በሮም ከተማ እ. አ. አ በ1967 ዓ. ም. የተቋቋመው የሜክሲካዊያን ጳጳሳዊ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዓመታቱ እንደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ቀጥሎም ከሜክሲኮ የተለያዩ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ቀጣይነት ያለውን የወንጌል ተልዕኮ ከፍተኛ ትምህርቶችን ለካህናት ለመስጠት፣ ወደ ሮም የሚላኩ ካህናትን እንዲቀበል መደረጉ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መጀመሪያ ላይ ኮሌጁ በቀዳሚነት በሜክሲኮ እና በመላው ላቲን አሜሪካ አገሮች የወንጌል አገልግሎትን ለማሳደግ በተጨማሪም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የደረሰውን ማኅበራዊ ችግር ለማቃለል ብሎ ለሚያደርገው ጥረት የኮሌጁ ዳይሬክተር ለሆኑት ለክቡር አባ ቪክቶር ኡሊሴስ ቫስኬዝ ሞሬኖ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች ካህናት በሚያካሂዱት ቀጣይነት ባለውን ተልዕኮ ላይም ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸው ተነግሯል።  

ራስን ከኃላፊነት ማሸሽ አይገባም

ከዚህ አንጻር ትምህርትን፣ መንፈሳዊነትን፣ ሰብዓዊን እና ሐዋርያዊ አገልግሎትን ቀጣይነት ካለው ስልጠና ጋር ማጣጣም አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው፣ የግል እና ማኅበርራዊ ጉድለቶች መኖራቸውን በመገንዘብ፣ በሕይወታችን ውስጥ ልናስተካክላቸው ስለሚገባን ቸልተኝነት እና ጉድለቶች ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ከብዙ ኃላፊነቶች እንድናመልጥ የሚያደርጉን ዓለማዊ ፈተናዎችን አቅልሎ መመልከት እንደማይገባ ገልጸው፣ ደ ሉባክን በመጥቀስ “መንፈሳዊ ዓለማዊነት በቤተክርስቲያን ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ ክፋቶች ሁሉ የከፋ እንደሆነ እና፣ ዓለማዊነት ወደ ሙስና የሚያስገባ በር ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ማንም ከሐዋርያዊ አገልግሎት እንዳይገለል

በተለይ በወጣትነት እና በሙስና መካከል እንደ ተስፋ ማጣት ያሉ የዛሬ ችግሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነት ርህራሄዋ "ሁሉንም የሚቀበል" የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድታሳየን በማለት ልመናቸውን አቅርበዋል። ይህን ጸጋ ለማግኘት እራሳችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመስል መፍቀድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ሐዋርያዊ ቸርነትን በማሳደግ ለሁሉም ጸሎት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት መጨነቅ ያስፈልጋል

ካህናት በሕዝብ መካከል እርቅን ለማውረድ የተጠሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እርስ በእርስ መከባበር ያለበት መልካም ግንኙነትን በሰዎች መካከል መመስረት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው የተለያዩ ባህሎችን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህ ሲደረግ በትውልድ ሐረጋቸው እና በእምነታቸው ምክንያት ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ ለተደረጉት ሰዎች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለው፣ አክለውም ሁሉም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቅ እና ፍትህን ለማምጣት እራስን ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።  

ወንድማማችነትን መፍጠር

“በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ አሁኑ የምንገኝበት ጊዜ ይጠይቀናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ማኅበራዊ አውታረ መረቦች እና የመገናኛ ብዙኃን ዓለማችን ከምን ጊዜም በላይ እንዲቀራረብ ምቹ አጋጣሚዎች በመፍጠሩ “የአንድነት ራዕይ” ያስፈልገናል ብለው፣ ይህም ወንድማማችነትን እንድንፈጥር የሚገፋፋን ሲሆን በተጨማሪም በባህሎች እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጉላት ያስችለናል ብለዋል። ምእመናን ከሁሉም ጋር በመተባበር የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እና አዲሲቱን ዓለም ለመገንባት መበርታት አለብን ብለዋል።

የጉዋዳሉፔ እመቤታችን ድንግል ማርያም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ለሚገኝ የሜክሲካዊያን ጳጳሳዊ ኮሌጅ ካህናት ያደረጉትን ንግግር ባጠቃለሉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ወንጌልን ከባሕል ጋር በማዛመድ የተትረፈረፈ ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማቅረብ የእምነትን መሠረት ማጠንከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው እ. አ. አ 2016 ዓ. ም. በሜክሲኮ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስታውሰው፣ የጉዋዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልበ ሙሉነት እንዲከተሏት የምትጋብዝ መሆኗን ገልጸው፣ እርሷ እና ቅዱስ ዮሴፍ ከሜክሲኮ የመጡት ካህናት እና የጳጳሳዊ ኮሌጁ ማህበረሰብን ሁሉ እንዲንከባከቡ በጸሎት ከጠየቁ በኋላ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

30 March 2021, 16:42