ፈልግ

ር. ሊ. ጳ በባግዳድ ስቴዲየም ውስጥ ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ር. ሊ. ጳ በባግዳድ ስቴዲየም ውስጥ ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ 

ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክቶች ተግባራዊነት መዘጋጀት ያስፈልጋል ተባለ

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አቶ ክላውዲዮ ዲሬሮ፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሰላም እና የወንድማማችነት መልዕክቶች ለኢራቅ ሕዝብ እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለኢራቅ ሕዝብ የአንድነት እና የወንድማማችነት መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ በሚገኙበት በዚህ ጊዜ፣ በኢራቅ ውስጥ የተለያዩ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በማበርከት ላይ የሚገኙ በርካታ ድርጅቶች ሰላምን በማምጣት ኢራቅን መልሶ ለመገንባት መነሳሳታቸውን አቶ ክላውዲዮ አስረድተዋል። የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበር በባግዳድ ውስጥ እ. አ. አ ከ2015 ዓ. ም. ጀምሮ የአካል ጉዳተኞች ራሳቸውን በመቻል ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲያስጠብቁ ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆኑ ታውቋል። የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው እ. አ. አ. በ1968 ዓ. ም. አባ ኦሬስቴ ቤንዚ በተባሉ ካህን ብርታት ሲሆን፣ ማኅበሩ በኅብረተሰቡ መካከል መገለልን እና ድህነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ ውሳኔን አድርጎ የተነሳ መሆኑ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው ከጥቂት ቀናት በፊት፣ የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበርን ጨምሮ በኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን ለማምጣት፣ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ቁስሎችን ለመፈወስ እና ኢራቅን መልሶ በመገንባት ለሕዝቡ መልካም ሕይወትን ለማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን በጋራ አረጋግጠው በተግባር ለመተርጎም ቃል መግባታቸው ታውቋል። ይህን አስመልክተው የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አቶ ክላውዲዮ ዲሬሮ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ማኅበራቸው በኢራቅ ውስጥ የሚገኙትን የአካል ጉዳተኞች በማቋቋም፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የሰላም እና የወንድማማችነት መልዕክት በተግባር መግለጽ ቀዳሚ ዓላማቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የአካል ጉዳተኞችን ማገዝ

የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበር በኢራቅ ውስጥ ከሚያበረክታቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ እና ዋናው የአካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ምክንያት ከኅብረተሰቡ መካከል የተገለሉ፣ በተለይም ከሙስሊም ቤተሰብ ለሚወለዱ ሕጻናት የትምህርት ዕድልን ማመቻቸት መሆኑን አቶ ክላውዲዮ ገልጸው፣ ከዚህም ጋር በማያያዝ ማኅበራቸው ባሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የአካል ጉዳተኛ ሕጻናትን ተቀብሎ የማስተማር አቅሙ ውስን መሆኑን አስረድተዋል። ማኅበራቸው በአካባቢው ድሃ እና የአካል ጉዳተኛ ሕጻናትን በመርዳት ላይ ከሚገኙ ከእናት ተሬዛ ማኅበር እህቶች ጋርም የሚተባበር መሆኑን ገልጸዋል። “ሕይወታችንን ከእነዚህ ሕጻናት ጋር እንጋራለን” ያሉት አቶ ክላውዲዮ፣ ቀኑን ሙሉ ከእነርሱ ጋር በጨዋታ እና አንዳንድ ዕለታዊ የትምህርት ቤት ሥራዎችን እያገዙ የሚውሉ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ምቹ ሥፍራ ሲሆኑ የሌሎች ፍቅር የሚሰማቸው የአካል ጉዳተኛ ሕጻናት፣ ደግነትን እና ቸርነትን የሚማሩ መሆኑን አስረድተው፣ በዚህ መልኩ ክርስቲያን እና ሙስሊም ማኅበረሰብም እንደዚሁ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የወንድማማችነት መልዕክት መሠረት በማድረግ እርስ በእርስ መልካም አቀባበልን ማድረግ እንደሚገባ መገንዘብ ይችላሉ ብለዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ጉብኝት

የኢራቅ ሕዝብ፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት በደስታ የተቀበለው፣ ቅዱስነታቸው በአመጽ እና በጦርነት ምክንያት ስቃይ ከደረሰበት የኢራቅ ሕዝብ ጋራ ያላቸውን አንድነት በተግባር በመግለጻቸው ምክንያት መሆኑን አቶ ክላውዲዮ አስረደዋል። ቅዱስነታቸውን ለመቀበል ወደ አደባባይ ከወጡት የአገሪቱ ሕዝብ መካከል አብዛኛው በኮቪድ-19 ምክንያት ከቤታቸው ሆነው ሥነ-ሥርዓቱን በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ክላውዲዮ፣ ቅዱስነታቸው ለኢራቅ ሕዝብ ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ ወደ ኢራቅ መጥተው ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ የወንድማማችነት እና የፍቅር ሐዋርያዊ መልዕክቶቻቸው እጅግ ጠቃሚዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት በእግዚአብሔር ስም ጥቃት የሚያደርሱ ወገኖች ከጥቃታቸው እንዲቆጠቡ ትምህርት ይሆናቸዋል ብለው፣ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ እንጂ የጥላቻ አምላክ አይደለም በማለት ከቫቲካ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

08 March 2021, 13:17