ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የኢራቅ ባለ ስልጣናት ከሕዝቡ ጋር ተባብረው አገራቸውን መልሰው እንዲገነቡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም ድረስ 33ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በኢራቅ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከተለያዩ መንግሥታዊ እና ሐይማኖታዊ መሪዎች ጋር በመገናኘት መልዕክት የሚያስተላልፉ መሆኑ ታውቋል። በዚህ መሠረት ቅዱስነታቸው በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ውስጥ በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ በመገኘት ለአገሪቱ መንግሥታዊ ባለስልጣናት፣ ሕዝባዊ መሪዎች እና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች ባደርጉት ንግግር፣ በኢራቅ ውስጥ አመጽ ቆሞ የኢራቅ ባለ ስልጣናት ከሕዝቡ ጋር ተባብረው አገራቸውን መልሰው እንዲገነቡ አሳስበዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፣ ከዚህ ቀጥሎ ቅዱስነታቸው በባግዳድ ውስጥ በፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ በመገኘት፣ ለአገሪቱ መንግሥታዊ ባለስልጣናት፣ ሕዝባዊ ተቋማት መሪዎች እና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች ያደረጉትን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋላን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ክቡር ፕሬዚዳንት፣ የተከበራችሁ የመንግሥት ተወካዮች፣ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች፣ ሕዝባዊ ማኅበራት ተወካዮች፣ ክቡራት እና ክቡራን፤

ለሰው ልጅ ሥልጣኔ ቅርበት ያለው የአብርሃም ምድር፣ የመዳን ታሪክ ባለቤት የሆኑ ነቢያት የኖሩባትን እና የአይሑድ፣ የክርስቲያን እና የሙስሊም እምነቶች የሚገኙባትን፣ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ልጎበኛት በምፈልጋት ኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝቴን እንዳደርግ ዕድል ስለ ሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ። የኢራቅ ፕሬዚዳንት ክቡር ሳሊ፣ ኢራቅን እንድጎበኝ መልካም ፈቃዳቸሁን ስለገለጹልኝ፣ በተወደደው የኢራቅ ሕዝብ ስም እና የመንግሥት ባለ ስልጣናት ስም መልካም አቀባበል ስላደረጉልኝ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ለውጭ አገራት ዲፕሎማቶች እና ለሕዝባዊ ተቋማት መሪዎች በሙሉ እንደዚሁ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ለብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ለመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ ልባዊ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ። ለሌሎች አብያተ ክርቲያናት ተወካዮች እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ ለእስልምና እምነት ተከታዮች እና ለሌሎች እምነቶች ተወካዮች በሙሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ወደ ኢራቅ መንፈሳዊ ጉዞ ወይም ንግደት ያደረግሁበት ዋና ዓላማ፣ የኢራቅ ምዕመናን በሕዝባቸው መካከል ለሚያቀርቡት የእምነት፣ የተሳፋ እና የፍቅር ምስክርነት ብርታትን ለመስጠት ነው። የእያንዳንዳችን ሐይማኖት በሚያስተምረት እውነተኛ አስተምህሮ በመመራት፣ እንደ ወንድም እና እህት፣ እርስ በእርስ ተግባብተን እና ተቻችለን በወንድማማችነት  መንፈስ በሰላም እና በኅብረት መጓዝ እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን። (ሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ፣ አቡ ዳቢ እ.አ.አ የካቲት 4/2019)

ሐዋርያዊ ጉብኝቴን በማድረግ ላይ የምገኘው፣ ዓለማችን ከገባበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ ለመውጣት ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት፣ የእያንዳንዱ ሰው ጤና ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ወደ ከፋ ደረጃ በመሄድ ላይ ባሉበት ወቅት ነው። አሁን የምንገኝበት ቀውስ ተጨባጭ ጥረቶችን በማድረግ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ፍትሃዊ የሆነ የክትባት መርሃ ግብሮችን ለእያንዳንዱ ሰው ለማድረስ አስፈላጊ እርምጃዎችን እንድንወስድ ይጠይቀናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን የምንገኝበት ቀውስ ከሁሉም በላይ የኑሮ ዜይቤአችንን እና የመኖር ትርጉምን በድጋሚ እንድናስብ ይጋብዘናል (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን ቁ. 33)። ይህ የፈተና ጊዜ፣ ከዚህ በፊት ከነበረን አካሄድ ወጥተን፣ ከሚለያየን ይልቅ አንድ የሚያደርገን በመያዝ፣ ሕይወታችንን ወደ መልካም አቅጣጭ እንድንመራ ይጠይቀናል።

ኢራቅ ላለፉት አሥርት ዓመታት፣ ተከባብሮ በሰላም አብሮ መኖርን በማይፈልጉ ጎሰኞች፣ የሐይማኖት ቡድኖች፣ የተለዩ ሃሳቦችን እና ባሕሎን የሚያራምዱ ሰዎች በሚቀሰቀሱ ጦርነቶች፣ የሽብር ጥቃቶች እና መከፋፈል ከፍተኛ ውድመትን ያስከተሉ ጥቃቶች የደረሱባት አገር ናት። እነዚህ አደጋዎች ያስከተሉት የጥፋት መጠን ከቁሳዊ ውድመት ይልቅ ለመፈወስ በርካታ ዓመታትን የሚውስዱ ቁስሎች በእያንዳንዱ ግለ ሰብ እና ማኅበረሰብ ልብ ውስጥ መኖራቸውን እንገነዘባለን። መከራ እና ስቃይ ከደረሰባቸው መካከል፣ በእምነታቸው እና በማንነታቸው ምክንያት ጭካኔ የተሞላበት ግፍ የተፈጸመባቸውን ንጹሃን የያዚዲ ጎሳዎች አባላት ይገኛሉ። ልዩነታችንን አስወግደን የአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት መሆናችንን መማር ስንችል፣ ለመጭው ትውልድ ፍትሃዊ እና ምቹ ዓለምን መገንባት ወደምንችልበት ውጤታማና ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን። ይህን በተመለከተ የኢራቅን ሕዝብ ለሺህ ዓመታት ያህል በመልካም ጎዳና እንዲጓዝ የረዱ ሐይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና የዘር ልዩነቶች ውድ ሃብቶች በመሆናቸው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። የሐይማኖት፣ የባሕል እና የዘር ልዩነቶች አመጽን ሳይሆን በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሰላማዊ አንድነትን እንደሚያመጣ ዛሬ ኢራቅ ለእያንዳንዱ አገር በተለይም ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ምስክር ልትሆን ይገባል።

የወንድማማችነት ሕይወት፣ በፍትህ የታገዘ የሕግ ጥበቃ የሚደረግለት ትዕግስት እና ውይይት እንዲኖር ይጠይቃል። ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም፣ የአንዱ እግዚአብሔር ልጆች በመሆን፣ ጥላቻን እና ቅራኔን በማስወገድ በርትቶ መሥራትን ያስፈልጋል። (ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ፣ የክርስቲያኖች አንድነት ምክር ቤት ውሳኔ አንቀጽ 5) በዚህ መርህ መሠረት በሌሎች አገሮች እንደሚደረግ ሁሉ የኢራቅ ባለስልጣናት ለሐይማኖቶች እውቅናን እና ክብርን እንዲሰጡ፣ መብትን እንዲያስከብሩ እና ጥበቃን እንዲሰጧቸው በማለት ቅድስት መንበር ድምጿን ሳታቋርጥ በማሰማት ላይ ትገኛለች። በዚህ ዙሪያ እስካሁን ለተደርጉት ጥረቶች ምስጋናዬን እያቀርብኩ፣ በጎ ፈቃድ ካላቸው ሁሉ ጋር በመሆን ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳደግ ያላቸውን ጥረት እንዲቀጥሉበት ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ወንድማዊ አንድነትን ማምጣት የሚቻለው እርስ በእርስ ተጋግዞ የሚኖር ኅብረተሰብ ነው። ከሰዎች ጋር አንድነትን መፍጠር ከግል ሕይወት አልፎ ጎረቤትን እና የሕይወት አጋሮቻችንን በርህራሄ ዓይን እንድንመለከት ያግዛል (ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን፣ እ.አ.አ 2021)። አንድነት ከዚህም በተጨማሪ ለአደጋ የተጋለጡትን እና በጣም ለተቸገሩት ተጨባጭ እንክብካቤን እንድናደርግላቸው የሚያግዘን በጎ ስነ ምግባር ነው። በዚህ አጋጣሚ በአመጽ እና በሽብር ምክንያት የቤተሰብ አባላትን፣ ወዳጆቻቸውን እና ቤት ንብረታቸውን ያጡትን ማስታወስ እወዳለሁ። እንደዚሁም ሕይወታቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ሥራ አጥነት እና ድህነት ምክንያት በሕይወት ለመኖር በትግል ላይ የሚገኙትንም አስታውሳለሁ። ለሌሎች ሰዎች ደካማነት ሃላፊነት የሚሰማው ሕሊና ሲኖረን ተጨባጭ የሆኑ ዕድሎችን በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በትምህርት እና ለጋራ መኖሪያ ቤታችን ለሆነው ምድራችን የምንጨነቅበት ኃይል ይኖረናል። ከገባንበት ቅውስ ለመውጣት አገርን መልሶ መገንባት ብቻውን በቂ አይደለም። በሚገባ መልሰን በመገንባት፣ ሰብዓዊ ክብራችን ተጠብቆልን በደስታ መኖር መቻል አለብን። ከችግር በምንወጣበት ጊዜ ከዚህ በፊት በኖርነው መንገድ ሳይሆን፣ ኑሮአችን የተሻለ ወይም የባሰ ሆኖ እናገኘዋለን።

እንደ መንግሥት መሪዎች እና ዲፕሎማቶች፣ ወንድማዊ የአንድነት መንፈስን ለማሳደግ ተጠርታችኋል። ይህ አስፈላጊ ቢሆንም በቂ አይደለም። ሙስናን፣ ስልጣን ያለ አግባብ መጠቀምን እና የሕግ ጥሰቶችን መዋጋት ያስፈልጋል። ከዚህም ጋር ፍትህን፣ ታማኝነትን፣ ግልጽነትን እና እነዚህን ርዕሠ ጉዳዮች የሚከታተሉ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል። ይህ ሲመቻች በቁጥር ከፍተኛ የሆነው ወጣቱ ትውልድ ለወደ ፊት ሕይወቱ እርግጠኛ የሚሆንበት፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ያለበት እና ዕርዳታን የሚያደርግ ጤናማ የፖለቲካ ሥርዓትን ማሳደግ ይቻላል።

ክቡር ፕሬዚዳንት፣ የተከበራችሁ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ውድ ወዳጆቼ! እኔ ወደ ኢራቅ የመጣሁት በዚህች አገር ለተፈጸሙት ውድመቶች እና ጭካኔአዊ ተግባራት ይቅርታን ለመለመን፣ በዚህ መንፈሳዊ ጉዞ አማካይነት የሰላም ንጉሥ ከሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን ለመለመን ነው። ባለፉት ዓመታት ውስጥ ለኢራቅ ሰላም ብዙ ጸልየናል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለኢራቅ ሰላም ሲሉ ብዙ ጥረቶችን አድርገዋል። ይህን በማሰብ ብዙ ጸሎት አቅርበዋል፣ ተሰቃይተዋልም። እግዚአብሔር የሚለምኑትን ሁል ጊዜ ይሰማል። እኛ እግዚአብሔርን በማድመጥ በእርሱ መንገድ መራመድ ይኖርብናል። በጦር መሣሪያ የሚታገዝ አመጽ ይቁም! የጦር መሣሪያ ዝውውር በዚህ አገር ይሁን በሌላም አገር ይገታ! ለአከባቢው ነዋሪዎች ሕይወት ግድ የማይሉ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ይቁም! የሰላም አስከባሪዎች ድምጽ ይሰማ! በሰላም መሥራት እና መጸለይ የሚፈልጉ የትሁታን እና የድሆች ድምጽ ተደማጭነትን ያግኝ!  አመጽ፣ ጽንፈኝነት እና በተለያዩ ወገኖች የሚታይ አለመቻቻል ይብቃ!

በቅንነት እና ገንቢ በሆነ ውይይት በመመስረት ተባብረው ይህችን አገር መገንባት ለሚፈልጉ ዜጎች በሙሉ ቦታ ሊሰጥ ይገባል። ዜጎች እርቅን እና የጋራ ጥቅምን ለማስከበር የተዘጋጁ ይሁኑ። ኢራቅ ባለፉት ዓመታት ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ መሠረት ለመጣል ብዙ ጥረት አድርጋለች። በመሆኑም በዚህ ጥረት መካከል የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የሐይማኖት ወገኖችን በማሳተፍ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶችን ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህች አገር ማንም እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቆጠር የለበትም። በዚህ ሂደት እስካሁን የተከናወኑትን እርምጃዎች በማበረታታት፣ በአገሪቱ ውስጥ መረጋጋትን እና ስምምነትን እንደሚያጠናክሩ እምነት አለኝ።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢራቅ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሰላምን የማምጣት ከፍተኛ ሚና አለው። አሥር ዓመታትን ያስቆጠረው የአጎራባች አገር ሶርያ አመጽ በዓለማችን ሰብዓዊ ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ፈተናዎችን እንዳስከተለ እንመለከተዋለን። በእነዚህ አገሮች ኤኮኖሚያዊ አለመመጣጠን እና አካባቢያዊ ውጥረት መኖሩን ለማሳወቅ ጥረት እንዲደርግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪውን በማቅረብ ላይ ይገኛል። በኢራቅ ውስጥ በተካሄዱት ጦርነቶች እና አመጾች ምክንያት የተፈናቀሉትን መልሶ በማቋቋም፣ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያን እና የጤና አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ ሰላም እና እርቅን ለማውረድ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ አገሮችን እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን አመሰግናለሁ። ከዚህም ጋር ለብዙ ዓመታት ያህል የዚህን አገር ሕዝቦች ለመርዳት የቆሙ የካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶችን ማስታወስ እፈልጋለሁ። የወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ዕለታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚደረግ የቸርነት እና የፍትህ ሥራ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ይጠቅማል። በመሆኑም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከኢራቅ ሕዝብ የዕርዳታ እጁን ሳያቋርጥ እንዲዘረጋ፣ የፖለቲካ እና የርዕዮተ ዓለም ፍላጎት ሳይጫኑባቸው፣ ከአካባቢ ባለ ሥልጣናት ጋር የጋራ ሃላፊነትን እንዲወስዱ በጸሎት ተስፋን አደርጋለሁ።

ሐይምኖት በመሠረቱ ሰላምን እና ወንድማማችመትን ለማገልገል የቆመ መሆን አለበት። የእግዚአብሔር ስም ግድያን ለመፈጸም፣ ለስደት፣ ለአሸባሪነት እና ለብዝበዛ መጠቀሚያ መንገድ መሆን የለበትም (የአቡ ዳቢ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ፣ እ.አ.አ. የካቲት 4/2019ዓ. ም.)። በተቃራኒው፣ ለሁሉ ሰው እኩል ክብር እና መብት በመስጠት የፈጠረ እግዚአብሔር የፍቅርን ታላቅነት፣ መልካም ፈቃድን እና ስምምነትን ለሌሎች እንድንመሰክር ይጠይቀናል። በኢራቅ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አማካይነት ገንቢ የሆነ ኅብረትን በመመስረት ሰላምን መፍጠር ትፈልጋለች። በዚህ አገር ዘመናትን ያስቆጠረው እና ለማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ አስተዋጽኦን ሲያበረክቱ የኖሩት የክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ ሀብታም ቅርሱን በመጠቀም ሁሉንም ኅብረተሰብ እያገለገሉ ለመቀጠል ፍላጎት አላቸው። እንደ ዜጋ የተሟላ መብት፣ ነጻነት እና ሃላፊነት የሚሰጣቸው የሐይማኖት ብዝሃነት፣ የዘር እና የባሕል ተሳትፎ፣ ለአገር ዕድገት እና ማኅበራዊ መግባባት የሚያደርጉት አስተዋጽዖ ከፈተኛ መሆኑን እንመሰክራለን።

ውድ ወዳጆቼ ሆይ! አሁንም በድጋሚ በዚህች አገር ወንድማዊ ኅብረትን፣ አንድነትን እና መግባባትን በማምጣት ሕብረትሰብን ለመገንባት ላደረጋችሁ እና በማድረግ ላይ ላላችሁ ጥረት ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ለጋራ ጥቅም ብላችሁ የምታቀርቡት አገልግሎት ክብር የሚሰጠው ነው። ሃላፊነታችሁ ዘላቂነት እንዲኖረው፣ በጥበብ፣ በፍትህ እና በእውነት እንዲመራችሁ ወደ እግዚአብሔር ጸሎቴን አቀርባለሁ። በእያንዳንዳችሁ፣ በቤተሰባችሁ፣ በምትወዷቸው ሰዎች ሁሉ እና በመላው የኢራቅ ሕዝብ የእግዚአብሔር በረከት በሙላት እንዲወርድ እለምናለሁ። አመሰግናለሁ"። 

06 March 2021, 11:22