ፈልግ

ር. ሊ. ፍራንችስኮስ ከኢራቅ ሲመለሱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት ር. ሊ. ፍራንችስኮስ ከኢራቅ ሲመለሱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ጉዞአችን በበጎ አድራጎት፣ በፍቅር እና በወንድማማችነት ጎዳና መሆን አለበት”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ሲመለሱ ከዓለም አቀፍ ሚዲያ ጋዘጠኞች በኩል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መስል ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ታሪካዊ ነው በተባለው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በእስልምና ሐይማኖት ከሺአ እምነት መሪ ከሆኑት ታላቁ አያቶላ ሰይድ አሊ አል ሁሴን አል ሲስታኒ ጋር መገናኘታቸውን፣ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ጥቃተ የወደመውን የሞሱል ቤተክርስቲያንን፣ ልጇን ለገደሉባት አሸባሪዎች ይቅርታን ያደረገች ክርስቲያን እናት እና በሊባኖች ሊያደርጉት ያሰቡትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው ሰፋ ያሉ መልስን መስጠታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቅድስት መንበር መመለሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከጣሊያን ውጭ ከሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ ጉብኝቶች መካከል 33ኛው መሆኑ ታውቋል። አንድ የካቶሊካ ቤተክርስቱያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኢራቅ ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ፣ ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ታሪካዊ ነው ተብሏል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ውስጥ ወደ ልዩ ልዩ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሥፍራዎች በመሄድ ከተለያዩ የሐይማኖት መሪዎች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ ሮም የሚያደርጉትን ጉዞ ሲጀምሩ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሐዋርያዊ ጉብኝት አስተባባሪ ሆነው ላገለገሉት ለክቡር ሞንሲኞር ዲናኔ ዴተኑ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ አብረዋቸው ለተጓዙት ጋዜጠኞች ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ወደ ሮም የተመለሱበት ዕለት፣ “ማርች 8” ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መሆኑን በማስታወስ እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያደረጉትን የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም በመጓዝ ላይ እያሉ ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። “መጓዝ ያለብን ጎዳና የበጎ አድራጎት፣ የፍቅር እና የወንድማማችነት መሆን አለበት” እንደሆነ ቅዱስነታቸው ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

በአረብ ኤምሬቶች አቡ ዳቢ ከተማ እ. አ. አ. የካቲት 4/2019 ዓ. ም. የጸደቀውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ሰነዱን ከግብጹ ታላቁ ኢማም አል አዛር አህመድ አል ጣይብ ጋር ስድስት ወር የፈጀ እና ከፍተኛ ጥናት በማድረግ የተመለከቱት መሆኑን አስታውሰዋል። የ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ፣ ለሕዝቦች፣ ለሐይማኖቶች እና ለባሕሎች መቀራረብ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸው፣ ቀጥሎ የወጣውን እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አስታውሰዋል። የሐይማኖቶች መቀራረብን በማስመልከት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ጠቃሚ እርምጃዎች ማድረጉን ቅዱስነታቸው አስታውሰው በተለይም በሐይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይት ማድረግ አስፈላጊነትን በማስመልከት ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን ማቅረቡን አስታውሰዋል።

በኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በዋናነት እምነትን እና የምሕረት ልመናን የተመለከት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት በኢራቅ ውስጥ ከሺአ እስልምና እምነት መሪ ከሆኑት ታላቁ አያቶላ ሰይድ አሊ አል-ሁሴን አል-ሲስታኒ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ያስደሰታቸው መሆኑን አስረድተዋል። አል ሁሴን አል ሲስታኒ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በአሥር ዓመታት ውስጥ ስለ ሐይማኖት እንጂ ስለ ፖለቲካ የሚናገር እንግዳ ወደ እርሳቸው አለመምጣቱን ነግረውኛል ብለዋል። ከታላቁ አያቶላ ሰይድ አሊ አል ሁሴን አል ሲስታኒ በኩል የተሰጣቸው አክብሮት የሰብዓዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች መገለጫዎች እንደሆኑ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ከፍተኛ ሰብዓዊ እሴቶችን በልባችው የያዙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው እነዚህ ታዲያ እምነታቸውን በተግባር ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ፣ ከሁሉም ጋር የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ሕይወት መኖር የሚፈልጉ በመሆናቸው ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል ብለዋል።

ኔልሰን ካስትሮ ከተባለ ከሚያውቁት ጋዜጠኛ እና ሐኪም በኩል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በላቲን አሜሪካ፣ የአርጄንቲና ተወላጅ ቢሆኑም፣ ለሚቀጥሉት ዓመታት በሙሉ ሀገረ ስብከታቸው በሆነው በሮም ከተማ ለመኖር መወሰናቸውን ገልጸቃል። በትውልድ አገራቸው አርጄንቲና ለ76 ዓመታት ያህል መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ያህል ዓመታት በአርጄንቲና መኖር ለእኔ በቂ ነው በማለት መልሰዋል። ወደ ላቲን አሜሪካ አገሮች ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ምኞት እንዳላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህንን እና ሌሎች ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ለማድረግ ከመወሰኔ በፊት የአማካሪዎቼን ሃሳብ ማድመጥ ይኖርብኛል ብለው፣ ሐዋርያዊ ጉብኝቶቼን ከማድረጌ በፊት ማስተንተን እና መጸለይ ይኖርብኛል የመጨረሻ ውሳኔ የሚመጣው ከልብ ውስጥ ነው ብለዋል።

አንድ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመደረግ በፊት ጊዜን ወስዶ ማሰብ እና መጸለይ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ወደ ኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያስታውሱ፣ ይህን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከማድረጋቸው አስቀድመው ብዙ ያስተነተኑበት እና የጸለዩበት መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በውስጣቸው ኃይልን በመጨመር ለውሳኔው ያገዛቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን ያሳተፈ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ለማካሄድ ሃሳብ እንዳለቸው የተጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን የሚያሳትፍ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ለማካሄድ ሃሳብ ባይኖራቸውም ሌሎች በርካታ ሐዋርያዊ ተግባራትን ለመፈጸም ሃሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የክርስቲያኖች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ ቀጣና ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ የያዚዲ ጎሳዎችን ጨምሮ በርካታ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከችግሮቹ መካከል አንዱ የነዋሪዎች መፈናቀል እና መሰደድ እንደሆነ አስረድተዋል። የሰዎች ከቦታ ቦታ መሰደድ ሁለት መብቶችን ያካተተ እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ መሰደድም አለ መሰደድም የሰዎች መብት ነው ብለው፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የሁለቱም መብቶች ባለቤት አይደሉም ብለዋል። ያለመሰደዳቸው ምክንያት እንዴት እና ወደ የት መሰደድ እንዳለባቸው ካለማወቃቸው የተነሳ ነው ብለው፣  መሰደድ ወይም የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከቦታ ቦታ መጓዝ ከአብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ መሆኑን ብዙ ሰዎች አልተገነዘቡትም ብለዋል። ሰዎች ከቦታ ቦታ በመጓዛቸው ጥቅም ሊገኝበት ይችላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሰዎች ተሰድደው በሚሄዱባቸው አገራት የሚኖሩበት ማኅበረሰብ በብዙ መልኩ እንደሚያግዙ አስረድተው፣ በቤልጄም ውስጥ ከአንድ ስደተኛ ቤተሰብ የምትወለድ ልጅ እስከ ሚኒስትርነት ደረጃ መድረሷን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል፣ እንደ ሊባኖስ እና ዮርዳኖስ የመሳሰሉ አገሮችን ጨምሮ ሌሎችም ስደተኞችን ተቀብለው ዕርዳታ ለሚያደርጉ አገራት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል ወደ ሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ እንደሚኣስቡ እና ቃል መግባታቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ላለፉት አሥር ዓመታት በከፍተኛ ጦርነት ውስጥ በምትገኝ አገር ሶርያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ባያስቡም በጸሎት እንደሚያስታውሷት ገልጸዋል።

በኢራቅ ጉብኝታቸው ወቅት መስጊዶችን ጨምሮ በርካታ ቤተክርስቲያኖች መጎዳታቸውን ወይም መውደማቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህም በሕዝቦች መካከል አለ መግባባት መኖሩን እና የጭካኔ ተግባራት መስፋፋታቸውን ያረጋግጣል ብለዋል። እስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በአካባቢው ከፍተኛ ጥፋት አድርሰዋል ያሉት ቅዱስነታችው፣ ለእነዚህ ታጣቂዎች የጦር መሣሪያን የሚሸጥ፣ የሚያስታጥቃቸው ማን ነው? በማለት ጠይቀዋል።

09 March 2021, 15:42