ፈልግ

የዓለም የውሃ ቀን በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ ተገለጸ! የዓለም የውሃ ቀን በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ ተገለጸ! 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ውሃን ማባከን፣ መበከል እና እንደ ሸቀጥ ማቅረብ ተገቢ አይደለም ማለታቸው ተገለ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለም የውሃ ቀን በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም በተከበረበር ወቅት ይህንን አመታዊ ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት ውሃ እንዳይበከል ወይም እንዳይባክን አስቸኳይ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ እንዲመጣ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ይህ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ለሁሉም ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእዚህ መልእክታቸው ለውሃ “እህት ውሃ” የሚል መጠሪያ ስም የሰጡ ሲሆን “እህት ውሃ” ን ለመጠቀም ሃላፊነት እና ጥንቃቄ እንዲደረግ መልእክት አስተላልፈዋል። አሁንም ቢሆን “ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለሁሉም ሰው ተደራሽ አይደለም፣ ውሃ ሸቀጥ አለመሆኑን እና ለእኛ የሚያስፈልገን መሰረታዊ የሆነ ነገር ነው፣ በፍጥነት “የተጠሙትን ለማጠጣት መጣር ይኖርብናል” ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት በእንግሊዜኛው ምጻረ ቃል (FAO) በብየነ መረብ አማካይነት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ በቫቲካን ዋና ጸኃፊ ካርዲናል ፒኤትሮ ፓሮሊን በኩል ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ይህንን እ.አ.አ በ 2021 ዓ.ም እየተከበረውን ዓለም አቀፍ የውሃ ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት ነበር ቅዱስነታቸው ይህንን መልእክታቸውን ያፋ ያደረጉት። እ.አ.አ ከ 1993 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ በመጋቢት 22 ቀን የሚከበረው የመታሰቢያ ቀን ውሃን ለማክበር እድል የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለሌላቸው 2.2 ቢሊዮን ህዝብ ውሃ ተደራሽ ይሆን ዘንድ ግንዛቤን ለመፍጠር ታስቦ የሚከበር ዓለም አቀፍ ቀን ነው።

ለውሃ ከፍተኛ ዋጋ መስጠት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለዚህ ዓመት የዓለም የውሃ ቀን የተመረጠውን መሪ ቃል በመጠቀም የውሃን ጥቅም ለማጉላት ያሰበ እና ውሃ በዋጋ ሊተመን የማይችል መሆኑን ለመግለጽ በማሰብ “ለውሃ ዋጋ እንስጥ” የሚለውን መሪ ቃል በድጋሚ ያስተጋቡ ሲሆን ፕላኔታችንን ለመጠበቅ በጣም መሠረታዊ የሆነውን ለእዚህ ንጥረ ነገር ጥበቃ ሊደረግለት እና አጠቃቀሙ ደግሞ የበለጠ በኃላፊነት መንገድ እንዲከናወን ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅረዋል።

“ውሃ ባይኖር ኖሮ ሕይወት አይኖርም ነበር ፣ የከተማ ማዕከላትም ባልነበሩ ነበር፣ ግብርናም አይኖርም ፣ የደን ልማትም ሆነ የከብት እርባታ አይኖርም ነበር” በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ይህ ሀብት በሚገባው መጠን ጥበቃና እንክብካቤ አልተደረገም ብለዋል።

“ውሃን ማባከን ፣ ችላ ማለት ወይም መበከል እስከዛሬም ድረስ አሁንም ቢሆን የሚደጋገም ግድፈት ነው” ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በእድገታችን እና በቴክኖሎጂ ግስጋሴያችን ዘመን “ንፁህ ፣ የሚጠጣ ውሃ ለሁሉም ሰው ተደራሽ ማደረግ ያስፈልጋል” የሚለውን ጉዳይ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አንስተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ እንደ ተናገሩት “ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ማደረግ መሠረታዊ እና ሁሉን አቀፍ ሰብአዊ መብት ነው ፣ […] ሌሎች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በቀዳሚነት የሚቀመጥ ሁኔታ” ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ሁሉም የሰው ልጆች ያለምንም ልዩነት የተከበረ ኑሮን እንዲመሩ ውሃ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ስለሆነም “ሊገረሰስ የማይችል ክብራቸውን የሚመጥን የመኖር መብትን ስለተነፈጉ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በሌላቸው ድሆች ላይ ዓለማችን ከባድ ማህበራዊ ዕዳ አለባት” ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች በውሃ ላይ

በዚህ አሳዛኝ እውነታ ላይ የተጨመሩ የአየር ንብረት ለውጥ ጎጂ ውጤቶች ጎርፍ ፣ ድርቅ ፣ የሙቀት መጠን መጨመር ፣ ድንገተኛ እና ያልታሰበ የዝናብ ፍሰት መጨመር፣ የበረዶ መቅለጥ፣ የወንዞች ፍሰት መቀነስ እና የከርሰ ምድር ውሃ መሟጠጥ በሰፊው እየተስተዋለ ነው ብለዋል።

እነዚህ ሁሉ ክስተቶች የውሃ ጥራትን የሚጎዱ ናቸው በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ለዚህ ሁኔታ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ክስተቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል ያሉት ሲሆን “በከፍተኛ መጠን የማባከን” ባህል መስፋፋት እና ግድየለሽነት በዓለም አቀፍ ደረጃ “የሰው ልጅ ተፈጥሮን የመበዝበዝ እና አሟጦ የመጠቀም ስልጣን እንዳለው እንዲሰማው የሚያደርግ” አሉታዊ ተግባር ነው ብለዋል።

በዚህ ላይ አሁን ያለው የጤና ቀውስ  “አሁን ያሉት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችን አስፋፍቷል ፣ ይህም በጣም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች መካከል የውሃ አገልግሎት መቋረጥ ወይም አለመጣጣም የሚያስከትለውን ጉዳት ያሳያል” ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ መትጋት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ጊዜ እንደ ውሃ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር የጎደላቸውን እና እንዲሁም እኛን የሚተኩ ትውልዶችን እንድናስብ ሁላችንን በእዚህ መልእክታቸው የጋበዙ ሲሆን እናም የባህር እና የወንዞች ብክለት እንዲቆም ሁሉም የበኩሉኑ አስተዋጾ ያበረክት ዘንድ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን  የከርሰ ምድር እና የውሃ ምንጮችን በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዓለም የውሃ ቀን በመጋቢት 13/2013 ዓ.ም በተከበረበት ወቅት ያስተላለፉትን መልእክት በቀጠሉበት ወቅት የቀድሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በላቲን ቋንቋ (Centesimus Annus) ከተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት በመጥቀስ ይህ በአኗኗራችን ላይ ለውጥ እንዲኖር ፣ ለጥሩነት ፣ ለእውነት ፣ ለውበት እና ከሌሎች ጋር ኅብረት ለመፍጠር በሚያስችል የትምህርት ጥረት አማካይነት ሊከናወን ይችላል ብለዋል። እነዚህ የፍጆታን፣ የቁጠባን እና የኢንቬስትሜንት ምርጫዎችን የሚወስኑ አቀራረቦች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ውሃን በአስተዋይነት መጠቀም ይገባል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ለእዚህ አመት የዓለም የውሃ ቀን የተመረጠው መሪ ቃል “ለውሃ ውጋ እንስጥ” የሚልው መሪ ቃል እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን ይህ መሪ ቃል ደግሞ የራሳችንን ቋንቋ እንድንለውጥ ይጠይቀናል . . . ስለ ፍጆታው ከመናገር ይልቅ በእውነተኛ ፍላጎታችን እና ለሌሎች ፍላጎት አክብሮት በመስጠት ውሃን በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን በመረዳት “አጠቃቀሙን ”ማመልከት አለብን ብለዋል።

በጎ ፈቃድ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡት ቅዱስነታቸው በመመዘኛዎቻቸው መካከል አጋርነትን በማስቀመጥ ውሃው ያለምንም ጥቅም በከንቱ ሳያባክን በምክንያታዊነት ጥቅም ላይ እንዲውል እና “በጣም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ማካፈል እንችላለን” ብለዋል።

ይህ ረግረጋማ ቦታዎችን ለመጠበቅ ፣ የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ፣ አነስተኛ ባለሃብቶች የመስኖ ሥራን እንዲሰሩ እና የውሃ አቅርቦቱ በጣም ተጋላጭ በሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ማህበረሰቦች በገጠር አካባቢዎች የመቋቋም አቅምን ያሻሽላል ብለዋል።

በምግብ ዋስትና እና በውሃ ጥራት መካከል ያለው ትስስር

“ለውሃ ዋጋ መስጠት” በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን እና የውሃ ጥራትን በጣም የተቆራኙ መሆናቸውን መገንዘብ ማለት ሊሆን ይችላል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ውሃ በሁሉም የምግብ ስርዓቶች ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ሲሆን የንጹህ ውሃ አቅርቦት እና በቂ የንፅህና አጠባበቅ በምግብ መበከል እና በሰዎች የአመጋገብ ሁኔታ እና በጤንነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ተላላፊ በሽታዎች ስርጭትን እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

የውሃ ብክነትን መቀነስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የውሃ ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሳንዘገይ እርምጃ መውሰድ ፣ የውሃን ብክነት፣ ብክለት እና ውሃን እንደ ሸቀጥ አድርጎ ማቅርብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ተግቶ መሥራት እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው የገለጹ ሲሆን በክልሎች እና በሀገራት መካከል የተሻለ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፣ አክለውም የመንግስት እና የግል ዘርፎች የራሳቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል። እንዲሁም በመንግስታዊ ድርጅቶች የበለጠ ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው “የመጠጥ ውሃ በሁሉም የፕላኔቷ ክፍሎች በብዛት እና በጥራት መዳረሱን ለማረጋገጥ” አስገዳጅ የህግ ሽፋን እና ስልታዊ እና ውጤታማ ድጋፍ መስጠትም በተመሳሳይ አስቸኳይ ነገር ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ በማስተላለፍ መልእክታቸውን አጠናቀዋል “ስለሆነም ለተጠሙ ሰዎች የመጠጥ ውሃ ለመስጠት እንጣደፍ። እንዳናባክን ወይም እንዳይበከል አኗኗራችንን እናስተካክል። የአዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ በጣም ትሑት፣ ውድ እና ንፁህ የሆነች እህት ብሎ የገለጻትን ውሃ ዋጋ በመስጠት የዚያ መልካምነት ተዋናዮች እንሁን!! ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

22 March 2021, 19:17