ፈልግ

“እግዚአብሔር እና መጪው ዓለም” በሚል ርዕሥ የታተመ መጽሐፍ የሽፋን ላይ ፎቶ “እግዚአብሔር እና መጪው ዓለም” በሚል ርዕሥ የታተመ መጽሐፍ የሽፋን ላይ ፎቶ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ነፍስን ከሞት ማትረፍ እንጂ ለሞት መዳረግ እንደማያስፈልግ አሳሰቡ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ላ ስታምፓ” የተሰኘ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ ከሆኑት ከአቶ ዶሜኒኮ አጋሶ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሰውን ሕይወት ከሞት አደጋ ማዳን እንጂ የጦር መሥሪያን በማምረት ለሞት መዳረግ እንደማያስፈልግ አሳስበዋል። “እግዚአብሔር እና መጪው ዓለም” በሚል ርዕሥ የታተመው መጽሐፍ ከቅዱስነታቸው ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ይዞ ማክሰኞ መጋቢት 7/2013 ዓ. ም. ለንባብ መብቃቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በሕይወት መካከል የጨለማ ወቅት አለ” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የጨለማ ወቅቱ እኛን ሳይሆን ሌሎችን ብቻ እንደሚያጋጥም፣ ሌሎች አገሮችን ወይም በሌላ አህጉር ብቻ እንደሚከሰት እናሳባለን ብለው፣ እንዲህ ማሰቡ ትክክል እንዳልሆነ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማረጋገጡን አስታውሰዋል። የደረሰብን ከፍተኛ ሕመም እና የጨለማ ጊዜ የእያንዳንዳችንን ቤት ማንኳኳቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ለሃሳባችን፣ ለምኞታችን እና ለዕቅዶቻችን እንቅፋት እንደፈጠረብን አስረድተዋል። ከዚህ ችግር ማንም ራሱን ነጻ ሊያደርግ እንደማይችል የገለጹት ቅዱስነታቸው ከዚህ ችግር በኋላ ዓለማችን ቀድሞ ከነበረበት የተለየ እነሚሆን አስረድተዋል። ኮቪድ-19 ካስከተለው ችግር ለመውጣት ጥረት ማድረግ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በጥልቅ በማሰብ፣ ለመላው የሰው ልጅ ሕይወት የሚበጅ ትክክለኛውን አቅጣጫ ለይቶ ማወቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።

“በሰዎች መካከል የሚታየውን የኑሮ አለመመጣጠን እና የአካባቢ ጸጥታ አለመረጋጋትን ከአሁን በኋላ መቀበል አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የሰውን ሕይወት ከአደጋ ማዳን የሚቻለው አዲስ የዕድገት እቅዶችን በመወጠን፣ ሕዝቦች እርስ በእርስ እና ከተፈጥሮ ጋር በሰላም የሚኖሩበትን አዲስ የጋራ ሕይወትን መመስረት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በግል የምናደርጋቸው ተግባራት በሌላ ሰው ሕይወት ተጽዕኖን ሊያስከትል እንደሚችል የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን እርስ በራሱ የተገናኘ እንጂ የተነጣጠለ እንዳልሆነ አስረድተዋል። በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ፣ በተለይም ሕጻናት በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ መሆኑን አስታውሰው፣ ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ፍትሃዊ ማድረግ እና የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ መብት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮችን ለማቃለል የተለያዩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣ ተቋማት እና ማኅበራት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ጥረታቸውን በተግባር መተርጎም የሚያስችል አዲስ አመለካከትን በማምጣት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። የጋራ  መኖሪያ ምድራችን የተፈጥሮ ሃብት ብዝበዛ የሚካሄድበት ሳይሆን ዘላቂነት ባለው ሁኔታ እንክብካቤ ፍቅር እና ክብር የሚያስፈልገው መሆኑንም አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ የጋራ ምድራችንን ከጥፋት ለመከላከል የኪያስችል ትክክለኛ ግላዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በጊዜ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ይህ ካልተደረገ የጋራ ምድራችን የሰው ሕይወት የማይኖርባት ልትሆን እንደምትችል አስረድተዋል።

የሕዝባዊ አስተዳደር መሪዎች እና የገንዘብ ተቋማት የበላይነትብ ስሜቶችን በማስወገድ ትክክለኛውን የእኩልነት መርሆችን ተከትለው በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን ማኅበራዊ ችግሮች መቀነስ እንደሚችሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነው ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣  በምርት ተቋማት የሚሳተፉ ባለሃብቶች የሥነ ምግባራዊ መርሆዎች ተከትለው ኃላፊነት በተመላበት መንገድ ምርታቸውን ማቅረብ ሲጀምሩ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሰላም መጎልበት የሚያግዝ ተግባር መፈጸም እንደሚችሉ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ለሰው ልጅ ሕይወት በተለይም የድሆችን ሕይወት የማይለውጡ፣ ለአካባቢ ደህንነት አስተዋጽዖን ለማያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ወይም የማምረቻ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ አስረድተው፣ የድሆችን ሕይወት ለመቀየር የማምረቻ ተቋማቱ መውሰድ ያለባቸው አራት እርምጃዎች እንዳሉ፣ እነርሱም ከኅብረተሰቡ የተገለሉትን በምርት ተግባር ላይ ማሳተፍ፣ የኑሮ ደረጃቸውን ማሳደግ፣ የጋራ እድገት ማምጣት እና ለተፈጥሮ ደህንነት ጥረት ማድረግ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

አንዳንድ አገሮች ከደረሰባቸው ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሃላፊነታቸውን በትክክል በመወጣት፣ ለሰዎች የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት፣ ለሠራተኞች ቋሚ ደመወዝን በማረጋገጥ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ የሃላፊነት ድርሻን መወጣት እንደሚያስፈልግ ገለጸዋል። በዚህ ረገድ ሃላፊነትን መውሰድ ያለበት መንግሥት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል በመካከሉ የሚታየውን ግድየለሽነትን ፣ ሙስናን እና ወንጀልን ማጥፋት ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

ባሁኑ ጊዜ በማኅበረሰብ መካከል የሚታዩ የተለያዩ ችግሮች ዓይናችንን እንድንገልጥ ያግዙናል በማለት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን እና መገለል ማስወገድ፣ ለሰብዓዊ ወንድማማችነት እንደሚያዘጋጅነን እና ያለ አንድነት እና ኅብረት ማንም ሰው የተሻለ ሕይወትን መኖር የማይችል መሆኑን አስረድተዋል። ይህን ሃሳብ ውጤታማ ለማድረግ የአገራት መሪዎች ከማኅበራዊ ተቋማት መሪዎች ጋር በመተባበር የምድራችንን ነዋሪዎች በሙሉ ወደ ወንድማማችንት ሕይወት ማድረስ ይችላሉ ብለው፣ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እርስ በእርስ በመወያየት የተሻለ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ዕቅዶችን መዘርጋት የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ መማር የምንችላቸው በርካታ መልካም ነገሮች መኖራቸውን ገልጸው፣ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲወጡ ወደ መልካም ወይም ካልሆነ ወደ ባሰ ሕይወት መድረስ የሚችል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ከደረሰብን ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግር መውጣት እንድንችል ልባችንን መክፈት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጉልበተኝነትን ፣ ድህነትን እና ሙስናን በማጥፋት ፣ ሁሉም በአንድነት፣ እያንዳንዱ የራሱን ድርሻ በመወጣት፣ የጋራ ኃላፊነትን በመውሰድ፣ አዲስ ሥርዓትን በማዋቀር፣ ኢ-ፍትሃዊ ተግባራትን ማስወገድ የሚቻል መሆኑን አስረድተው፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክትባት አገልግሎትን ያለ ልዩነት ለሁሉም እንዲሰጥ በማስተባበር ከደረሰብን የጤና ቀውስ እንደገና መነሳት እንችላለን ብለዋል።

ማኅበራዊ ሕይወትን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ፣ ለታመሙት በቂ የሕክምና እርዳታን በመስጠት ከሞት ማትረፍ የሚቻልበትን የገንዘብ አቅም ለጦርነት መሣሪያ ግዥ ማዋል ተጋቢ እንዳልሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጦር መሣሪያዎች የታገዙ አመጾችን መቀስቀስ፣ ድህነት እንዲስፋፋ ማድረግ፣ በግድ የለሽነት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚፈጸመውን ብዝበዛ በዝምታ መመልከት የማይቻል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ይህ ግድ የለሽነት አመጽ እንዲስፋፋ፣ ሰብዓዊ መብት እንዲጣስ እና ዘላቂ ዕድገት እንዳይኖር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሴቶች ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ እናቶች በክፍያ እና በሞያዊ ስልጠና ላይ አድልዎ እንደሚደረግባቸው ገልጸው፣ ሴቶች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ የአገልግሎት ዘርፍን በማሳደግ እና በማዘመን ሂደት ቀዳሚ ሚናን የሚጫወቱ መሆኑን አስረድተው በማከልም ሴቶችን በማኅበራዊ ሕይወት በሙላት በማሳተፍ ሁሉ አቀውፍ ዓለምን መገንባት እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታችው አሳስበዋል።

በልጆች እና በወላጆች መካከል ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ሲሆኑ የሕይወት ትርጉምን የሚያስረዱ በርካታ እሴቶችን መማር እንደሚችሉ፣ በራስ የመተማመን ፍላጎትን በማሳደግ፣ የጊዜ ትርጉምን በሚገባ በማወቅ ራስን ከጎጂ አመሎች ማራቅ የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል። ልጆች ለወላጆቻቸው ማበርከት የሚችሉት ሁለት ነገሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ለጊዜ ከፍተኛ ዋጋን መስጠት እና ትሁት ሆኖ መገኘት እንደሆነ አስረድተዋል።

15 March 2021, 14:52