ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከግድ የለሽነት ህሊና መውጣት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጣሊያን፣ ፊሬንሴ ከተማ የሚገኝ የፍራንችስካዊያን ወንድሞች የዕርዳታ ማዕከል በጎ ፈቃደኞችን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው ታውቋል። እ. አ. አ በ1983 ዓ. ም. የተቋቋመው የዕርዳታ ማዕከሉ ለድሃ ቤተሰቦች፣ ለአረጋዊያን እና ለአካል ጉዳተኞች ዕርዳታን ለማዳረስ የተቋቋመ ሲሆን፣ ቅዱስነታቸው የማዕከሉን በጎ ፈቃደኞች በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣ በጎ ፈደኞቹ የትህትና ምሳሌ በመሆን፣ በርኅራሄ ልብ “በችግር ውስጥ የወደቁትን ለመርዳት መጠራታቸውን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለበጎ ፈቃደኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ድሆችን፣ አቅመ ደካማ አረጋዊያንን እና የአካል ጉዳተኞችን ከመከራ እንዲያድኗቸው አሳስበው፣ የእግዚአብሔር በአፍቃሪ ልቡ ልጆቹን በመውደድ፣ በመንከባከብ እና ክብራቸውን የሚጠብቅ መሆኑን አስረድተዋል። ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለተቀበሏቸው የፊሬንሴ ፍራንችስካዊያን ዕርዳታ ማዕከል በጎ ፈቃደኞች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ዘርፈ ብዙ የዕርዳታ ማዕከል ነው

እ.አ.አ በ1983 ዓ. ም. በፍራችስካዊያን ሦስተኛ ማኅበር ሥር በሚገኙ ምዕመናን የሚመራ የዕርዳታ ማዕከሉ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከመሰረቷቸው የተለያዩ ማኅበራት የተወጣጡ ሲሆን፣ ዓላማውም ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ችግር የደረሰባቸውን የማኅበረሰብ ክፍል ለመርዳት የተቋቋመ መሆኑ ታውቋል። ማዕከሉ ባሁኑ ጊዜ የታረዙትን በማልበስ፣ ችግራቸውን በማድመጥ የማበረታቻ ምክሮችን በመስጠት፣ አረጋዊያንን እና የአካል ጉዳተኞችን የሚረዳ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለፍራንችስካዊያን በጎ ፈቃደኞች ባደረጉት ንግግር ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግር ወስጥ የሚገኙትን ማድመጥ እና አጋርነትን መግለጽ በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸው፣ በማኅበረሰባችን ውስጥ በርካታ ቤተሰቦች ለችግር መጋለጣቸውን አስታውሰው፣ እነዚህ ችግረኛ ቤተሰቦች የዘወትር ዕርዳታን እና የሕዝቡ ቀረቤታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ማንም ሰብዓዊ መብቱን መነፈግ የለበትም

ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደ ቆሰሉት ሰዎች በርኅራሄ መቅረቡን ያታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከድሆች፣ ከተናቁት፣ ከተገለሉት እና ከተጨቆኑት ጋር መሆንን እንደመረጠ ገልጸው፣ ሌሎችም እንደ እርሱ እንዲያደርጉ፣ የታረዙትን እንዲያለብሱ፣ የተራቡትን እንዲያበሉ፣ የተጠሙትን እንዲያጠጡ የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። እግዚአብሔር በፍቅሩ ብዛት የተነሳ ልጆቹ ችግር እንዳይደርስባቸው፣ እንዳይራቡ፣ እንዳይጠሙ፣ ከኅብረተሰብ መካከል እንዳይገለሉ፣ ብቸኝነት እንዳይሰማቸው እና ክብራቸውም እንዲጠበቅላቸው የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።

የቅዱስ ፍርስንችስኮስን ምሳሌ መከተል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለፍራንችስካዊያን ማዕከል በጎ ፈቃደኞች ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ የዕርዳታ ማዕከላቸው የሚያበረክታቸው መልካም ተግባራት የአሲስው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ካሳያቸው የወንድማማችነት ምሳሌ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸው፣ ሁላችንም ወንድማማቾች ነን የሚለውን ቃለ ምዕዳናቸውን በማስታወስ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ቦታን ሳይለይ በሁሉ ስፍራ በሚገኙ ድሆች፣ በተናቁት፣ በተገለሉት እና በተረሱት መካከል ሰላምን መፍጠሩን አስታውሰዋል። ላለፉት አርባ ዓመታት ድሆችን በመርዳት የሚታወቀው የፍራንችስካዊያን ማኅበር የዕርዳታ ማዕከል፣ ዛሬ ላይ ጠንካራ የተስፋ ምልክት መሆኑ ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ማዕከሉ ሰዎች ከግድ የለሽነት አስተሳሰብ ወጥቶ በችግር ለቆሰሉት ሰዎች ርኅራሄን እንዳናሳይ የሚያደርግ እና በማድረግ ትህትና ራስን ዝቅ እንድናደርግ የሚያደርግ የፍቅር ምልክት መሆኑን አስረድተዋል።

ምስኪኑን ወንድማችን ስለ መከተል

በሦስት ቃላት ላይ ትኩረት በመስጠት የተናገሩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለፍራንችስካዊያን በጎ ፈቃደኞች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ድሆችን እንደቀረበ፣ እንደራራላቸው እና እንደወደዳቸው ሁሉ፣ የዕርዳታ ማዕከሉ በጎ ፈቃደኞችም ተመሳሳይ ተግባር እንድያደርጉ በማለት አሳስበው፣ የዋህ ልባችን እና ጉልበታችን በቂ ባለመሆኑ በጸሎት አማካይነት የእግዚአብሔርን ድጋፍ መለመን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

02 March 2021, 22:03