ፈልግ

የእውቁ ጣሊያናዊ ደራሲ ዳንቴ ምስል  (13X18 cm) የእውቁ ጣሊያናዊ ደራሲ ዳንቴ ምስል (13X18 cm) 

እውቁ ጣሊያናዊ የሥነ-ጥበብ ሰው ዳንቴ፣ የተስፋ ነቢይ እና የምሕረት ገጣሚ ነበር ተባለ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የታላቁ ጣሊያናዊ ገጣሚ ዳንቴ አሊጊዬሪ ሕልፈት 700 ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ሐዋርያዊ መልዕክት ልከዋል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት፣ ከታላቁ ገጣሚ ዳንቴ አሊጊዬሪ ድንቅ ሥራዎች መካከል “መለኮታዊ ኮሜዲ” የተሰኘ ሥራው ተገቢነት ያለው፣ የጊዜ እና የእምነት ጥልቀት የሚያጎላ ነበር በማለት ገልጸውታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እ. አ. አ 1321 ዓ. ም በጣሊያን ውስጥ ከሚወዳት ፍሎረንስ የትውልድ ከተማ ወደ ራቬና የተሰደደው እውቁ ገጣሚ ዳንቴ በድርሰት ሥራዎቹ ዛሬም ይናገረናል። ሰዎች በሙሉ ድንቅ ሥራዎቹን በማንበብ እና በማጥናት ብቻ ሳይሆን በማድመጥ እና በተግባር በመኖር ወደር ከሌለው ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ፍቅር በመታገዝ ወደ እውነተኛ ደስታ እንድንደርስ ይጠይቀናል። ይህን ጥበብ ለመግለጽ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ "Candor lucis aeternae” ወይም “የዘላለም ብርሃን ግርማ” በሚል ርዕሥ መጋቢት 16/2013 ዓ. ም. ሐዋርያዊ መልዕክታቸው መጻፋቸው ታውቋል። በዚህ ዕለት ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ለመጻፍ የወደዱት በአጋጣሚ ሳይሆን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ሥጋ የሆነበት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሙሉ ተቀባይነት ያገኘበት መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ይህም የዳንቴ ግጥሞ እውነተኛ ልብ እና መነሳሳትን በማግኘት፣ እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በመግባት የሰው ልጅ እውነተኛ ደስታን ያገኘበት ዕለት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት እና ዳንቴ
ዘጠኝ አንቀጾች ያሉት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት የሚጀምረው ከዚህ በፊት የነበሩት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ እውቁ ገጣሚ ዳንቴ ያላቸውን አስተያየት በመግለጽ ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የእውቁ ገጣሚ ዳንቴን ሕይወት በመመርመር "በጊዜ ያልተገደበ፣ አስፈላጊነት" ያለው የ“ሰዎች ሕይወት ምሳሌ” በማለት ለጥበብ ሥራዎቹ አፅንዖትን ሰጥተዋል። የእውቁ ገጣሚ ዳንቴን ሥራዎች በእውነቱ “የባህላችን ወሳኝ ክፍል ነው” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የዳንቴ ሥራዎች “ወደ አውሮፓ እና ምዕራቡ ዓለም የክርስትና መሠረቶች እንድንሄድ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፣ ቤተክርስቲያን እና ሲቪል ማህበራት አሁንም ድረስ የሚያቀርቡትን መሠረታዊ እሴቶችን ያቀፈ፣ ሁሉም ሰው ሌሎችን እንደ ወንድም እና እህት አድርጎ እንዲመለከት የሚደርግ ማህበራዊ መሠረት ያለው ነው ብለዋል።

ተፈጥሮአዊ የደስታ ፍላጎት
በእውቁ ገጣሚ ዳንቴ “መለኮታዊ ኮሜዲዎች” ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ዓምዶች መኖራቸውን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እነርሱም “በሰው ልብ ውስጥ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ፍላጎት” እና “ፍቅር በሆነው በእግዚአብሔር ዕቅድ የሚፈጸም ደስታ ነው” ብለዋል። ገጣሚው ዳንቴ “የተስፋ ነቢይ” የተባለበት ዋናው ምክንያት ሥራዎቹ የሰው ልጅ ራሱን ጨለማ ከነገሰበት ከኃጢአት በረሃ በመውጣት በሕይወት ታሪክ ውስጥ እርካታን ወደሚያገኝበት ወደ ዘለዓለማዊው እግዚአብሔር ጎዳና እንዲደርስ ስለሚያሳስብ ነው ብለዋል።

በዳንቴ የተወደሱ ሴቶች
በ”መለኮታዊ ኮሜዲ” ውስጥ ለተጠቀሱት ሦስት ሴቶች ትኩረትን የሰጠው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊው መልዕክት እነርሱም፣ የቸርነት ምሳሌ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ተስፋን የምትወክል ቤያቲሪስ እና እምነትን የምትወክል ቅድስት ሉሲ መሆናቸውን አስታውቋል። ስነ-መለኮታዊ ባሕርያትን የተላበሱት እነዚህ ሦስቱ ሴቶች፣ የሌሎች ሰዎች እገዛ ካልታከለበት በቀር የሰው ልጅ ብቻውን ሆኖ ራሱን ማዳን እንደማይችል ለዳንቴ ሥራዎች መሠረት መሆናቸውን ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መልዕክታቸው አስረድተዋል።

ዳንቴ እና የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ
ቅዱስ ፍራንችስኮስን ባስታወሱበት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ የዳንቴ ሥራ፣ የ“ብሩክ ሰው ነጭ ጽጌረዳ” በሚል አርዕስት መገለጹን ገልጸዋል። በዚህ የዳንቴ ሥራ ውስጥ በአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና በገጣሚው ዳንቴ ሥራ መካከል ተመሳሳይነት መኖሩን የተረዱት ቅዱስነታቸው፣ የመጀመሪያ ወደ ሕዝብ መካከል መሄድን እንደመረጠ እና ሁለተኛው ከላቲን ቋንቋ ይልቅ በሕዝብ መካከል በስፋት የሚነገር ቋንቋን መናገር የመረጠ መሆኑን አስታውሰው፣ ሁለቱም የፈጣሪው መልክ በግልጽ የሚታይበት ተፈጥሮ ራሳቸውን ክፍት ያደረጉበት አጋጣሚ መኖሩን አስረድተዋል።

ለሁሉም የሚሆን መልዕክት
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በእውቁ ጣሊያናዊ ገጣሚ በሆነው በዳንቴ መልዕክቶ ውስጥ የሚገኙ ባሕላዊ፣ ሐይማኖታዊ እና ሞራላዊ እሴቶችን ለሌሎች በማስተማር ላይ የሚገኙት መምህራንን አመስግነው፣ ይህ “ቅርስ” በክፍል ውስጥ እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብቻ ተዘግቶ እንዳይቀር ፣ ነገር ግን በሌሎች ዘንድ እንዲታወቅ እና እንዲስፋፋ፣ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና ባህላዊ ማህበራት በቁርጠኝነት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ለሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች ባቀረቡት ጥሪ "ለዳንቴ ግጥሞች ድምፅን ፣ መልክን፣ ልብን ፣ ቅርፅን ፣ ቀለምን እና ድምፅ በመስጠት፣ በብልሃት የተጓዘበትን የውበት ጎዳና በመከተል "የሰላም ፣ የነፃነት እና የወንድማማችነት መልእክት እንዲያሰራጩ ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መልዕክታቸው መደምደሚያ ላይ፣ የታላቁ ገጣሚ ዳንቴ ሥራዎች ልባችን እውነተኛ ሰላም እና ደስታ እስኪያገኝ ድረስ፣ ወደ መጨረሻ ግባችን እስከምንደርስ ድረስ እያንዳንዳችን በተጠራንበት የሕይወት ጉዞ እና እምነት ላይ በእርጋታ እና በድፍረት እንድንራመድ ይረዳን ብለዋል።
 

27 March 2021, 18:10