ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ ኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ ኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉትን 33ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም 33ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማደረግ ወደ ኢራቅ ዛሬ የካቲት 26/2013 ዓ.ም ጉዞ መጀመራቸው ይታወቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሰባት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ከጣሊያን ውጭ አሁን በኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጨምሮ 33 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከሚገኙት ከኬኒያ፣ ከሁጋንዳ እና ከመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ አንስቶ በኩባ፣ በአሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ በምስራቅ አውሮፓ እና በኤሽያ አህጉር በመጓዝ የሰላም እና የአንድነት መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

900 የካቶሊክ ምዕመናን ብቻ የሚገኙባትን እና አብዛኛው ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍል የሚኖሩባትን አዛረበጃንን ጨምሮ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች የሚኖሩባቸውን ባንግላዲሽ እና ማያን ማር (የቀድሞ ስሟ በርማ) ድረስ በመሄድ የሰላም እና የአንድነት መልእክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

እንደ ተለመደው ቅዱስነታቸው ማንኛውንም ሐዋሪያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት እና ማነኛውንም ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሮም ከተማ በሚመለሱበት ወቅት በሮም ከተማ እንብርት ላይ በሚገኘው በማሪያም ስም ከተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በአውሮፓ አህጉር በትልቅነቱ እና በጥንታዊነቱ በሚታወቀው ሳንታ ማሪያ ማጆሬ በመባል በሚታወቀው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝተው፣ በዚያው በሳናታ ማርያ ማጆሬ ባዚሊካ ውስጥ በሚገኘው ባላቲን ቋንቋ “Salus Populi Romani” በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም የሮም ከተማ ሕዝቦች አዳኝ ወይም ጠባቂ በመባል የሚታወቀው እና በአብዛኞቹ  የሮም ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ሕጻኑን ኢየሱስን በእጆቹዋ ላይ አቅፋ መያዙዋን የሚያሳየው ምስል ስር በመገኘት ይህ በኢራቅ የሚያደርጉት 33ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሳካ ይሆን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትረዳቸው ዘንድ የመማጸኛ ጸሎት  ማቀረባቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

ቅዱስነታቸው ባሳንታ ማሪያ ማጆሬ ባዚሊካ ተገኝተው ጸሎት ካደርሱ ቡኃላ በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 03፡30 ላይ በሮም ከተማ ከሚገኘው እና በ15ኛው ክፍለ ዘመን በኖረው የጌታን የመጨረሻ እራት እና ሞናሊዛን በመሳሰሉ ድንቅ በሆኑ ስዕሎቹ በሚታወቀው በሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ስም ከተሰየመው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማርፊያ በመነሳት ጉዞዋቸውን ጀምረው 2947 ኪሎ መትሮችን በአየር ላይ ተጉዘው የጣሊያንን፣ የግሪክን፣ የሲፕረስን፣ የፍልስጤምን እና የእስራኤልን የአየር የበረራ ክልሎችን አቋርጠው 04፡30 ደቂቃ ጉዞ ካደረጉ ቡኃላ በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 08፡00 የኢራቅ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሰለም እንደ ሚደርሱ ይጠበቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደ ደረሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አቀባበል እንደ ሚያደርጉላቸው ተገልጿል።

05 March 2021, 10:38