የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ጉብኝት የሰላም እና አብሮ የመኖርን ባሕልን የሚያሳድግ መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የኢራቅ ቤተክርስቲያን ታሪክ፣ እድገት እና ተልዕኮ” በሚል አርዕስት፣ እ. አ. አ. 2015 ዓ. ም. ያሳተሙትን መጽሐፋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ በዚህ መጻፋቸው አማካይነት የኢራቅን ታሪክ ለመረዳት የሚያግዙ አንዳንድ ጠቃሚ መልዕክቶችን ማካፈላቸውን ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ ወደ ኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ አንድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርግ በታሪክ የመጀመሪያ መሆኑንም ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ወደ ኢራቅ የሚጓዙ መሆኑ ታውቋል።
እንደገና የመወለድ መንፈስ
ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ በኢራቅ ስለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን በጻፉት መጽሐፋቸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ውድ እና ጥንታዊነት ያለው የአምልኮ ስርዓት፣ የክርስቲያን ማኅበረሰቡ የእምነት ጽናት እና የሕዝቡን ባሕል በስፋት ያብራሩበት መሆኑ ታውቋል። በኢራቅ ስብከተ ወንጌል የተጀመረው በሚሲዮናዊያን ሳይሆን የአገሩ ነዋሪ በነበረው በቅዱስ ቶማስ መሆኑንም ካርዲናል ፊሎኒ በመጽሐፋቸው ገልጸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢራቅ ሕዝብ ቋንቋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚናገረው ቋንቋ ጋር የሚመስሰል መሆኑንም ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እና የምዕራቡ ዓለም ከኢራቅ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር ወንድማዊ ግንኙነት እንዳለው መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በኢራቅ ውስጥ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በኩል የተዘራው አመጽ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ጥቃት ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ማድረሱን በመጽሐፋቸው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ ከዚህ ሁሉ ችግር በኋላ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተው አክለውም በኢራቅ የሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም የመላዋ ቤተ ክርስቲያን አካል በመሆኑ በቁጥር ማነሱ መታየት የለበትም ብለዋል።
በወንድማማችነት ጎዳና ላይ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሩ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ብርታትን ከመስጠት በተጨማሪ ከሐይማኖት ተቋማት ጋር ያለውን የጋራ ውይይትን እና ወንድማዊ ግንኙነትን፣ በተለይም በእስልምና እምነት ከታቀፉ የሺአ እና ሱኒ እምነቶች ጋር በመቀራረብ ወዳጅነትን ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሁሉም የሐይማኖት ተቋማት ጋር የጀመሩትን የወንድማማችነት ጎዳናን እያጠናከሩ መምጣታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ ሕዝቦች ተቀራርበው በሰላም አብሮ የመኖር ባሕልን ማሳደግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናገረዋል። የኢራቅ መንግሥትም በበኩሉ በአገሪቱ የሚታየውን አለመረጋጋት እና ልዩነት በማስወገድ፣ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችን በማቀራረብ በጋራ በመወያየት ለጋራ እድገት እና ብልጽግና መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሕልም እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መላው ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚሰቃይበት ወቅት መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝትን ለማድረግ ምቹ ጊዜን መጠበቅ አስፈላጊ እንዳልሆነ አስረድተው፣ ቅዱስነታቸው ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ አገር ያደረጉትን አስፈሪ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ እ. አ. አ 2000 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በኢራቅ የአብርሃም ምድር ወደ ሆነችው ኡር ሊያደርጉት የተመኙት ሐዋርያዊ ጉብኝት በወቅቱ በነበረው የአገሪቱ አለመረጋጋት ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን አስታውሰዋል። በኢየሩሳሌም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ተንከባካቢ ታላቅ መምህር እና አስቀድመው በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ንግግራቸውን ሲደመደሙት እንደተናገሩት፣ በኢራቅ ወስጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው የመከራ እና የስደት ዓመት አልፎ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ሲመኙት የነበረው ሐዋርያዊ ጉብኝት በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሰላም እንደሚከናወን የኢራቅ ሕዝብ በታላቅ ደስታ እና ናፍቆት የሚጠባበቅ መሆኑን ገልጸዋል።