ፈልግ

“ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ” “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ”  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የጸሎት ቀንን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲያበቃ ጸሎት የሚደረግበትን ቀን ምክንያት በማድረግ የቪዲዮ መልዕክት አስተላለፉ። ቅዱስነታቸው የሰዎች ዝውውርን በመቃወም ሰኞ የካቲት 1/2013 ዓ. ም. በበይነ መረብ አማካይነት የሚደረገውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚካፈሉ መሆኑ ታውቋል። ሥነ-ሥርዓቱን ያዘጋጀው “ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ.አ.አ 2015 ዓ. ም. ለዘጠኝ ዓመታት አስከፊ የባርነት ሕይወት ከኖረች በኋላ ነጻ የወጣች የቅድስት ባኪታ መታሰቢያ ቀንን በመሠረቱበት ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የዘመናችን ማኅበረሰብ ቁስል መሆኑን ማስገንዘባቸው ይታወሳል። ዘንድሮ የሚከበረው ጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን የሚከበረው ሰኞ የካቲት 1/2013 ዓ. ም. ሲሆን፣ ሥነ-ሥርዓቱ ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ (www.youtube.com/c/preghieracontrotratta) አማካይነት እንደ ተለመደው በአምስት ቋንቋዎች በቀጥታ የሚተላለፍ መሆኑ ታውቋል። ሥነ-ሥርዓቱ በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጸም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ በማስተንተን፣ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ በሆነው ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ በመወያየት እና ግንዛቤዎችን በመስጠት የሚከናወን ሲሆን መሪ ቃሉም “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ” እንደሚል ታውቋል።

አማራጭ መንገዶች           

ሰኞ የካቲት 1/2013 ዓ. ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከአርባ ጀምሮ በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልክታቸውን በቀጥታ የሚያስተላልፉ መሆኑ ታውቋል። “ታሊታ ኩም” በተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት አስተባባሪ የሆኑት እህት ገብርኤላ ቦታኒ ዕለቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በዛሬው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስርዓት ውስጥ አማራጭ መንገዶችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ጋብዘው፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርም ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚንጸባረቅበት፣ ትክክለኛ የገበያ ስርዓትን የሚያወድም፣ በሰብዓዊ ክብር ላይ የተመሠረተውን የማኅበራዊ ሕይወት እሴት ከመሸርሸሩ በላይ የአካባቢ ጥበቃንም አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ኅብረት ዋና ጥረት፣ የሰውን ልጅ ሕይወት የሚያሳድግ ኢኮኖሚን ​​መገንባት እና የሚያስከብር ሥራን ለሁሉ መፍጠር መሆኑ ታውቋል።  

“ታሊታ ኩም” ኅብረት

ጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን አዘጋጅ ኮሚቴ የተዋቀረው በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሥር በሚገኘው የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት ውስጥ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ማኅበራት የበላይ አለቆች ጥምረት ሲሆን፣ በዚህ ጥምረት ውስጥ ካሪታስ ኢንተርናሽናል፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊክ ሴቶች ኅብረት፣ የፎኮላሬ እንቅቃሴ እና ሌሎች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የተዋቀሩ በርካታ እንቅስቃሴዎች መጠቃለላቸው ይታወቃል።

ዘንድሮ ሰኞ የካቲት 1/2013 ዓ. ም. የሚከበረው የጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን ሥነ-ሥርዓት፣ እኩለ ቀን ላይ የኦሺኒያ አገሮች በሚያቀርቡት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚጀምር ሲሆን በመቀጠልም ኤዥያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች፣ አፍሪካ እና አውሮፓ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን የሚያቀርቡ መሆኑ ታውቋል። በመቀጠልም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ በላቲን አሜሪካ እና በሰሜን አሜሪካ ባዘጋጁት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚጠቃለል መሆኑ ታውቋል። ዓለም አቀፍ ጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀንን በማኅበራዊ አውታረመረቦች “#PrayAgainstTrafficking” በሚለው ሃሽታግ በኩል መደገፍ የሚቻል መሆኑን አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል።  

06 February 2021, 13:27